በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 5 (ከመስከረም 2015 እስከ የካቲት 2016)

የዎርዊክ ፎቶ ጋለሪ 5 (ከመስከረም 2015 እስከ የካቲት 2016)

ይህ የፎቶ ጋለሪ ከመስከረም 2015 እስከ የካቲት 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በአዲሱ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የተከናወነውን ግንባታ እንዲሁም ፈቃደኛ ሠራተኞች ለግንባታው ያደረጉትን ድጋፍ ያሳያል።

የዎርዊክ ግንባታ ሲጠናቀቅ ምን መልክ እንደሚኖረው የሚያሳይ ምስል። ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ፦

  1. የተሽከርካሪዎች ጥገና ሕንፃ

  2. የጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ

  3. የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

  4. መኖሪያ ሕንፃ ለ

  5. መኖሪያ ሕንፃ መ

  6. መኖሪያ ሕንፃ ሐ

  7. መኖሪያ ሕንፃ ሀ

  8. ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ጥቅምት 7, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

በረግረጋማ ቦታ ላይ የሚዘረጋው ድልድይ ቅስት ሲጓጓዝ። ቅስቱ ከጭነት መኪናው እንደወረደ ጎማዎች ላይ ተቀምጦ ነበር። ድልድዩ ረግረጋማ ቦታዎቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይከላከላል።

ጥቅምት 13, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ሴደም ተብሎ በሚጠራ የተክል ዓይነት የተሸፈነው ጣሪያ፤ ይህ ተክል ክረምት ከመግባቱ በፊት ቀለሙን ይቀይራል። በጣሪያው ላይ አሥራ ስድስት ዓይነት የሴደም ዝርያዎች ተተክለዋል። ተክል የተተከለባቸው ጣሪያዎች ጎርፍን በመቀነስ አካባቢውን ለመጠበቅ ይረዳሉ፤ ኃይል ለማመንጨት የሚጠይቀውን ወጪ ይቀንሳሉ፤ እንዲሁም ተክሎቹ ጤናማ እንዲሆኑ የሚያስፈልጋቸው አረሙን ማጥፋት ብቻ ነው።

ጥቅምት 13, 2015— መኖሪያ ሕንፃ መ

አንድ የእንጨት ሥራ ባለሙያ በመኖሪያ ክፍል ኩሽና ውስጥ የዕቃ መደርደሪያ ሲገጥም። የእንጨት ሥራ ክፍሉ፣ በኩሽናዎቹ ውስጥ ከሚኖሩት የዕቃ መደርደሪያዎች 60 በመቶውን እስከ የካቲት 2016 ድረስ ገጥሞ አጠናቋል።

ጥቅምት 16, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የኤሌክትሪክ ባለሙያዎች በማማው ላይ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ አርማ ላይ LED አምፖሎች ሲገጥሙ።

ጥቅምት 21, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

ማማውንና የእንግዳ መቀበያውን የያዘው የቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ ምሽት ላይ ያበራል። ማማው ጎብኚዎች የዎርዊክን የግንባታ ቦታና አካባቢውን ማየት እንዲችሉ ያስችላል።

ጥቅምት 22, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

የግንባታ ሠራተኞች ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም እርዳታ የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙባቸውን መንገዶች ሲሠሩ። በዙሪያው የተደረገው ጊዜያዊ ሽፋን፣ በግንባታ ወቅት አፈሩ እንዳይሸረሸር ይረዳል።

ኅዳር 9, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

የግንባታ ሠራተኞች ከአሳንሰር መጠበቂያው በላይ አስቀድሞ የተዘጋጀ፣ ብርሃን የሚያሳልፍ መስኮት ሲገጥሙ። በቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃው ውስጥ የተገጠሙት አሥራ አንድ ብርሃን የሚያሳልፉ መስኮቶች የፀሐይ ብርሃን ወደ ሕንፃው እንዲገባ ያስችላሉ።

ኅዳር 16, 2015—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

አንድ የብየዳ ባለሙያ በኦክሲጅን አሴታይሊን መቁረጫ ተጠቅሞ ለሕንፃው ማቀዝቀዣ የሚያገለግል ቧንቧ ሲቆርጥ።

ኅዳር 30, 2015—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንዲት የእንጨት ሥራ ባለሙያ የመስኮቱ ደፍ የሚያርፍበትን ቦታ ስታዘጋጅ። ይህ ሥራ እንዳለቀ አስቀድሞ የተዘጋጀው የመስኮት ደፍ ይገጠማል።

ታኅሣሥ 17, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

በፋብሪካ የተዘጋጁ የመንገድ ንጣፎች በዝናባማ ቀን ሲደረደሩ። በስተቀኝ እንደሚታየው የፈሰሰው ጠጠር በሚገባ ይደለደላል። ፊት ለፊት የሚታየው የፎቶው ክፍል አንድ ከባድ ተሽከርካሪ የተዘጋጀውን የድንጋይ ንጣፍ በቦታው ሲያስቀምጠው ያሳያል። አፈሩ እንዳይሸረሸር ደግሞ በስተግራ በኩል እንደሚታየው በፕላስቲክ ይሸፈናል።

ታኅሣሥ 24, 2015—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

ሠራተኞች መለስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተላልፍ ሽቦ ሲዘረጉ፤ የዎርዊክ የግንባታ ቦታ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ከዚህ ነው።

ጥር 5, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

አንድ የግንባታ ሠራተኛ ከጎብኚዎች የመኪና ማቆሚያ ወደ ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ የሚወስደውን የእግረኛ መንገድ ጣሪያ ሲሠራ። ጣሪያው ዝናብና በረዶ ጎብኚዎችን እንዳይመታቸው ይከላከላል።

ጥር 5, 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

አንድ ቴክኒሽያን የማሞቂያ መቆጣጠሪያውን ሲያስተካክል። በዎርዊክ የግንባታ ቦታ የሚገኙት አራቱም ማሞቂያዎች ተገጥመዋል።

የካቲት 8, 2016—ቢሮዎች እና የአገልግሎት መስጫ ሕንፃ

መካኒኮች በልብስ ማጠቢያ ክፍል ውስጥ ማድረቂያዎችን ሲገጥሙ። ማድረቂያዎቹ ከ6 እስከ 45 ኪሎ ግራም ልብስ ድረስ የማድረቅ አቅም አላቸው። በስተግራ በኩል ባለው ግድግዳ ላይ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ይገጠማሉ።

የካቲት 8, 2016—የተክሲዶ የግንባታ ቦታ

የበላይ አካል አባል የሆነው ጌሪት ሎሽ የቤቴል ቤተሰብን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ሲመራ። ፕሮግራሙ የዎርዊክ ሠራተኞች በሚኖሩባቸው ሌሎች ቦታዎችም ይተላለፋል።

የካቲት 19, 2016—መኖሪያ ሕንፃ ሀ

የሕንፃዎቹን የውስጥ ክፍሎች የሚሠሩ ወንድሞች ወደ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ምንጣፍ ሲወስዱ። ለዎርዊክ ሕንፃዎች የሚሆኑ ከ65,000 ካሬ ሜትር በላይ የሚሆኑ ምንጣፎች ታዘዋል።

የካቲት 22, 2016—የዎርዊክ የግንባታ ቦታ

ከመስከረም 2015 እስከ የካቲት 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ መኖሪያ ሕንፃ ሐ እና መኖሪያ ሕንፃ መ ለመኖሪያነት ብቁ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ምሥክር ወረቀት በመሰጠቱ አንዳንድ ሠራተኞች በዚያ መኖር ጀምረዋል። የሕንፃዎቹ አሳንሰሮች በሙሉ ተገጥመዋል። የመኖሪያ ሕንፃዎቹ መንገዶች ሥራ ተጠናቋል። ክረምቱ ብዙም ከባድ ስላልነበር አካባቢውን የማሳመሩ ሥራ ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ እየተጠናቀቀ ነው።

የካቲት 24, 2016—የጥገና ሕንፃ እና የነዋሪዎች የመኪና ማቆሚያ

ኮርኒስ የምትሠራ አንዲት ሴት ኮርኒሱ የሚያርፍበትን ብረት ለመግጠም ከፍ ባለ መቆሚያ ላይ ስትራመድ። ከግድግዳና ከጣሪያው ጋር የተያያዙ ነገሮችን የሚሠራው ክፍል ያለበት ኃላፊነት፣ ፍሬም መሥራትን፣ ሙቀት እንዳያስተላልፉ ሽፋኖችን ማልበስ፣ ግድግዳዎችን መግጠምንና የማጠናቀቂያ ሥራ መሥራትን፣ ክፍተቶቹን መሙላትን፣ እንዲሁም ግድግዳዎቹ ላይ በተዘጋጁ ቦታዎች ላይ የእሳት አደጋ መከላከያ መሣሪያዎችን መግጠምን ያካትታል።