ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት
የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ሞባይል ስልክ ባሉ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ላይ የሚጫን መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የሚረዳ JW Library (JW ቤተ መጻሕፍት) የተባለ ፕሮግራም ጥቅምት 7 ቀን 2013 ኢንተርኔት ላይ ለቅቀዋል። ይህ በነፃ የሚገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮግራም ኪንግ ጄምስ ቨርዥንን እና በ2013 ተሻሽሎ የተዘጋጀውን አዲስ ዓለም ትርጉም ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ይዟል። a
የተዘጋጀው ለምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሥራም ሆነ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ዘመናዊ ስልኮችን፣ ታብሌቶችን ወይም ሌሎች ተመሳሳይ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ለጥናት የሚያገለግሉ ጽሑፎችን ቀድሞውኑም ከjw.org ላይ ማግኘት ይችሉ ነበር፤ ታዲያ JW Library የተዘጋጀው ለምንድን ነው?
አንደኛ፣ ፕሮግራሙ አንዴ ከተጫነ በኋላ ኢንተርኔት አይፈልግም፤ በመሆኑም የኢንተርኔት አገልግሎት ባይኖርም ፕሮግራሙን መጠቀም ይቻላል። ሁለተኛ፣ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው አንባቢዎች ጥቅሶችን በቀላሉ ማውጣት እንዲችሉና መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ በጥልቀት ማጥናት እንዲችሉ ታስቦ ነው። እንዴት?
ቤተ መጻሕፍቱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይረዳል
JW Library ሲከፈት መጀመሪያ የሚታየው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ዝርዝር ነው። ተጠቃሚው አንድ መጽሐፍ ሲመርጥ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉት ምዕራፎች በሙሉ ይታያሉ። ይህ ደግሞ ተጠቃሚው የሚፈልገውን ጥቅስ ወይም ሐሳብ ከመረጠው ምዕራፍ በጥቂት ሴኮንዶች ውስጥ እንዲያገኝ ይረዳዋል። ፕሮግራሙ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዱ ሌሎች ገጽታዎችም አሉት፤ ለምሳሌ፦
አማራጭ አተረጓጎም እንዲሁም ተጨማሪ መረጃ የያዙ የግርጌ ማስታወሻዎች
ተመሳሳይ ሐሳብ የያዙ ሌሎች ጥቅሶችን ለማውጣት የሚረዱ ማጣቀሻዎች
ተጠቃሚው የሚፈልገው ቃል ወይም ሐረግ የሚገኝበትን ቦታ ሁሉ የሚያሳይ የመፈለጊያ ዘዴ
በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ የመጽሐፉን ይዘት የሚያሳይ ክፍል
እያንዳንዱ መጽሐፍ የተጻፈው በማን እንደሆነ፣ የተጻፈበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም የሚሸፍነውን ጊዜ የሚያሳይ ሣጥን
ባለ ሙሉ ቀለም ካርታዎች፣ ሰንጠረዦች፣ የጊዜ ሰሌዳዎችና ሥዕላዊ መግለጫዎች
የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያዘጋጇቸው ሌሎች የሕትመት ውጤቶች ሁሉ ይህን ፕሮግራም ማግኘት የሚቻለው በነፃ ነው። ይህ በነፃ የሚገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮግራም የሚዘጋጀው በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች ነው፤ ይህ ፕሮግራም እስከ አሁን ከአንድ ሚሊዮን በሚበልጡ መሣሪያዎች አማካኝነት ወርዷል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ይህን ልዩ ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻሕፍት ለምን ራስህ አትሞክረውም?
a ጥር 2014 ፕሮግራሙ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸውን የዕለት ጥቅስና የመዝሙር መጽሐፍ እንዲይዝ ተደርጓል። ይህ ፕሮግራም በአሁኑ ጊዜ የሚገኘው በእንግሊዝኛ ብቻ ነው።