በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ቪዲዮዎች

በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ቪዲዮዎች

የይሖዋ ምሥክሮች በትርጉም ሥራቸው በብዙዎች ዘንድ የታወቁ ናቸው። እስከ ኅዳር 2014 ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን በ125 ቋንቋዎች የተረጎምን ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሌሎች ጽሑፎችን ደግሞ በ742 ቋንቋዎች ተርጉመናል። የትርጉም ሥራችን ቪዲዮዎችን ማዘጋጀትንም ይጨምራል። እስከ ጥር 2015 ድረስ በመንግሥት አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተባለው ቪዲዮ በ398 ቋንቋዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለው ቪዲዮ ደግሞ በ569 ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። ይህ ዝግጅት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የቻልነውስ እንዴት ነው?

በመጋቢት 2014 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማሩን ሥራ ለመደገፍ በተቻለ መጠን በብዙ ቋንቋዎች ቪዲዮዎችን እንዲያዘጋጁ መመሪያ ሰጥቶ ነበር።

ቪዲዮ የመተርጎም ሥራ የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። በመጀመሪያ፣ የትርጉም ቡድኑ የቪዲዮውን ጽሑፍ (ስክሪፕት) ይተርጉማል። ከዚያም እያንዳንዱን ድምፅ የሚጫወቱ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ይመረጣሉ። ቀጥሎም የኦዲዮ ቪዲዮ ሥራ የሚያከናውነው ቡድን የተተረጎመውን ጽሑፍ በድምፅ ይቀርጻል፤ የተቀዳውን ድምፅ ያርማል፤ እንዲሁም በቪዲዮው ላይ የሚታዩ ጽሑፎችን ያዘጋጃል። በመጨረሻም ድምፁ፣ ጽሑፉና ፊልሙ አንድ ላይ ከተቀናበረ በኋላ ቪዲዮው ድረ ገጹ ላይ ይወጣል።

አንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የድምፅ ቀረጻ ስቱዲዮ እና ለሥራው የሠለጠኑ ሰዎች አሏቸው። ገለልተኛ በሆኑ አካባቢዎች የሚነገሩ ቋንቋዎችስ?

በዓለም ዙሪያ የድምፅ ቀረጻ የሚያከናውኑ ቴክኒሽያኖች ተንቀሳቃሽ የመቅረጫ መሣሪያዎችን መጠቀም ጀምረዋል። ቴክኒሽያኑ የድምፅ ማጉያ መሣሪያ እና የድምፅ መቅረጫ ሶፍትዌር ያለው ላፕቶፕ ኮምፒውተር በመጠቀም በቢሮ፣ በመንግሥት አዳራሽ ወይም በመኖሪያ ቤት ውስጥ ጊዜያዊ ስቱዲዮ ያዘጋጃል። የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ጽሑፉን በማንበብ፣ የቅጂውን ሥራ በኃላፊነት በመቆጣጠር እንዲሁም የቅጂውን ጥራት በመከታተል አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ቀረጻው ሲጠናቀቅ ቴክኒሽያኑ መሣሪያዎቹን ይዞ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳል።

በዚህ መንገድ ቪዲዮዎቻችንን ከዚህ በፊት ከነበረው በሦስት እጥፍ በሚበልጡ ቋንቋዎች ማዘጋጀት ተችሏል።

ሰዎች ለቪዲዮዎቹ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። ቪዲዮዎቻችን ለብዙዎቹ ሰዎች በቋንቋቸው የተዘጋጁ የመጀመሪያዎቹ ቪዲዮዎች ናቸው።

ቪዲዮዎቻችን ከተዘጋጁባቸው ቋንቋዎች አንዱ ፒጃንጃጃራ ሲሆን በአውስትራሊያ በሚኖሩ ከ2,500 በሚበልጡ ሰዎች የሚነገር ቋንቋ ነው። በዚህ ቋንቋ ቅጂው የተከናወነው በሰሜናዊ የአውስትራሊያ ክልል በምትገኝ አሊስ ስፕሪንግስ በተባለች ከተማ ነው። በቅጂው ሥራ እገዛ ያበረከተው ካለን ቶማስ እንዲህ ብሏል፦ “ቪዲዮዎቹ ተወዳጅነትን አትርፈዋል። የአካባቢው ሰዎች ቪዲዮዎቹን በከፍተኛ ጉጉት ይመለከቱ የነበረ ሲሆን ሌሎች ቪዲዮዎችን ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይጠይቁ ነበር። በዚህ ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች እምብዛም አይገኙም። በመሆኑም በቋንቋቸው የተዘጋጁ ነገሮችን ሲሰሙ በተለይም ሲመለከቱ በጣም ተደመሙ።”

በካሜሩን የሚኖሩ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በጀልባ በአንድ ወንዝ ላይ እየተጓዙ ነበር። ፒግሚዎች በሚኖሩበት መንደር አካባቢ ቆም ብለው በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነን አንድ የመንደር አለቃ አነጋገሩ። ይህ ሰው ባሳ የተባለውን ቋንቋ እንደሚናገር ሲረዱ ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ከታብሌታቸው ላይ አሳዩት። የመንደሩ አለቃ በጣም ከመደነቁም ሌላ ጽሑፎች እንዲሰጡት ጠየቀ።

በኢንዶኔዥያ በሚገኝ መንደር ውስጥ ያለ አንድ የሃይማኖት መሪ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚቃወም ከመሆኑም ሌላ በአካባቢው ያሰራጯቸውን ጽሑፎች በሙሉ አቃጥሏል። ሌሎች የመንደሩ ነዋሪዎች ደግሞ የመንግሥት አዳራሹን ለማቃጠል ዝተው ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አራት ፖሊሶች ወደ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤት ሄደው በእሷና በቤተሰቧ ላይ ምርመራ ማድረግ ጀመሩ። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ምን እንደሚከናወን ማወቅ ስለፈለጉ ይህች የይሖዋ ምሥክር በመንግሥት አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተባለውን ቪዲዮ በኢንዶኔዥያኛ ቋንቋ አሳየቻቸው።

አንደኛው ፖሊስ ቪዲዮውን ከተመለከተ በኋላ “ሰዎች ስለ እናንተ ያላቸው መረጃ የተዛባ እንደሆነና በደንብ እንደማያውቋችሁ መገንዘብ ችያለሁ” ብሏል። ሌላኛው ፖሊስ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ለሌሎች ማሳየት እንድችል ይህን ቪዲዮ ማግኘት እችላለሁ? ይህ ቪዲዮ ስለ እናንተ ትክክለኛውን መረጃ ይዟል።” አሁን ፖሊሶቹ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት ያላቸው ሲሆን ጥበቃም ያደርጉላቸዋል።

እነዚህን ቪዲዮዎች ተመልክተሃቸው ታውቃለህ? ካልሆነ ለምን በራስህ ቋንቋ አትመለከታቸውም?