ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የኢየሱስ ሞት የሰው ልጆች የኃጢአት ይቅርታና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ አስችሏል። (ሮም 6:23፤ ኤፌሶን 1:7) በተጨማሪም የኢየሱስ ሞት አንድ ሰው በጣም ከባድ የሆነ ፈተና ቢያጋጥመውም እንኳ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ መቀጠል እንደሚችል አረጋግጧል።—ዕብራውያን 4:15
የአንድ ሰው ሞት እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንዲከናወኑ ያስቻለው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።
ኢየሱስ የሞተው “የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ” ሲል ነው።—ቆላስይስ 1:14
የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው ፍጹም ይኸውም ኃጢአት የሌለበት ሆኖ ነው። ይሁንና አዳም አምላክን ላለመታዘዝ መረጠ። አዳም አምላክን ባለመታዘዝ ኃጢአት ሠርቷል፤ ይህም በዘሮቹ ሁሉ ላይ ከባድ ጉዳት አስከትሏል። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ” ይናገራል።—ሮም 5:19
ኢየሱስም ልክ እንደ አዳም ፍጹም ነበር፤ ሆኖም ምንም ኃጢአት አልሠራም። በመሆኑም “ለእኛ ኃጢአት የቀረበ የማስተሰረያ መሥዋዕት” ሊሆን ችሏል። (1 ዮሐንስ 2:2) የአዳም አለመታዘዝ መላው የሰው ዘር በኃጢአት እድፍ እንዲበከል እንዳደረገ ሁሉ የኢየሱስ ሞት ደግሞ በእሱ ላይ እምነት ያላቸውን ሁሉ ከኃጢአት እድፍ አንጽቷል።
አዳም የሰው ልጆችን በሙሉ ለኃጢአት ባርነት ሸጧቸዋል ማለት ይችላል። ኢየሱስ ግን ለሰው ልጆች ሲል ለመሞት ፈቃደኛ በመሆን የሰው ልጆችን ከተሸጡበት ባርነት ገዝቷቸዋል። በመሆኑም “ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”—1 ዮሐንስ 2:1
ኢየሱስ የሞተው “[በእሱ] የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል” ነው።—ዮሐንስ 3:16
አዳም የተፈጠረው ለዘላለም እንዲኖር ቢሆንም የሠራው ኃጢአት የሞት ቅጣት አስከትሎበታል። በአዳም አማካኝነት “ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”—ሮም 5:12
የኢየሱስ ሞት ግን በእሱ ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ ከኃጢአት እድፍ እንዲጸዱ ብቻ ሳይሆን ከሞት ቅጣት እንዲድኑም አስችሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዩን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአት ከሞት ጋር እንደነገሠ ሁሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ አማካኝነት እንዲነግሥ ነው።”—ሮም 5:21
እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች የተወሰነ ያህል ዕድሜ ኖረው ይሞታሉ። ይሁንና አምላክ ጻድቅ ለሆኑ የሰው ልጆች ወደፊት የዘላላም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል፤ በተጨማሪም አምላክ የሞቱ ሰዎችን በማስነሳት እነሱም ከኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል።—መዝሙር 37:29፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22
ኢየሱስ ‘እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ በመሆን’ የሰው ልጆች ማንኛውም ዓይነት ፈተና ወይም መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለአምላክ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ አረጋግጧል።—ፊልጵስዩስ 2:8
አዳም ፍጹም አእምሮና አካል የነበረው ቢሆንም ራስ ወዳድ በመሆን ለእሱ የማይገባውን ነገር የፈለገ ሲሆን በዚህም ምክንያት አምላክን ሳይታዘዝ ቀርቷል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:6) ከጊዜ በኋላ፣ የአምላክ ዋነኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን የሰው ልጆች በሙሉ አምላክን የሚታዘዙት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነና በተለይም ሕይወታቸው አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ አምላክን ማገልገላቸውን እንደሚተዉ ተናግሯል። (ኢዮብ 2:4) ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስ ግን ክፉኛ ተዋርዶና ተሠቃይቶ እስከመሞት ድረስ አምላክን በመታዘዝ ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ እንደሆነ አሳይቷል። (ዕብራውያን 7:26) በዚህ መንገድ የሚከተለውን ሐቅ አረጋግጧል፦ የሰው ልጆች ማንኛውም ዓይነት ፈተና ወይም መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለአምላክ ታማኝ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላል።
ከኢየሱስ ሞት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች
ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለመታደግ መሠቃየትና መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? አምላክ በሰው ልጆች ላይ ያስተላለፈውን የሞት ፍርድ ሊሽረው አይችልም ነበር?
የአምላክ ሕግ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” ይላል። (ሮም 6:23) አምላክ ይህን ሕግ ለአዳም በግልጽ ነግሮታል፤ አለመታዘዙ ሞት እንደሚያስከትልበት አሳውቆታል። (ዘፍጥረት 3:3) “ሊዋሽ የማይችለው አምላክ” አዳም ኃጢአት በሠራበት ወቅት ቃሉን ጠብቋል። (ቲቶ 1:2) አዳም ለዘሮቹ ያወረሰው ኃጢአትን ብቻ ሳይሆን የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞትንም ጭምር ነው።
ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የሞት ቅጣት ይገባቸው የነበረ ቢሆንም አምላክ ‘ከተትረፈረፈ ጸጋው’ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አጋጣሚውን ከፍቶላቸዋል። (ኤፌሶን 1:7) የሰው ልጆችን ለመታደግ ሲል ያደረገው ዝግጅት ማለትም ኢየሱስ ወደ ምድር በመምጣት ፍጹም መሥዋዕት እንዲሆን ማድረጉ የእሱን ወደር የለሽ ፍትሕና ምሕረት ያንጸባርቃል።
ኢየሱስ የሞተው መቼ ነው?
ኢየሱስ የሞተው የአይሁዳውያን ፋሲካ በዋለበት ዕለት ከሰዓት በኋላ “ዘጠኝ ሰዓት” አካባቢ ነው። (ማርቆስ 15:33-37) በዘመናዊ የቀን መቁጠሪያዎች መሠረት ይህ ቀን የዋለው አርብ፣ ሚያዝያ 1, 33 ዓ.ም ነው።
ኢየሱስ የሞተው የት ነው?
ኢየሱስ የተገደለው ‘የራስ ቅል ቦታ’ ወይም “በዕብራይስጥ ጎልጎታ” በተባለ ስፍራ ነው። (ዮሐንስ 19:17, 18) ኢየሱስ በኖረበት ዘመን ይህ ስፍራ የሚገኘው ከኢየሩሳሌም ‘ከተማ በር ውጭ’ ነበር። (ዕብራውያን 13:12) መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ሞት “ከሩቅ ሆነው የሚያዩ” አንዳንድ ሰዎች እንደነበሩ ስለሚናገር ቦታው የሚገኘው ኮረብታ ላይ ሳይሆን አይቀርም። (ማርቆስ 15:40) ይሁንና ጎልጎታ በዛሬው ጊዜ የት አካባቢ እንደሚገኝ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።
ኢየሱስ የሞተው እንዴት ነው?
ብዙዎች ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሠቅሎ እንደሞተ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” በማለት ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 2:24፣ የ1954 ትርጉም) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኢየሱስ የተሰቀለው ምን ላይ እንደሆነ ለማመልከት ስታውሮስ እና ዛይሎን የሚሉትን ሁለት የግሪክኛ ቃላትን ተጠቅመዋል። በርካታ ምሁራን እነዚህ ቃላት የሚያመለክቱት አንድን ቀጥ ያለ እንጨት ወይም አጠና እንደሆነ ይሰማቸዋል።
የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ልናከብር የሚገባው እንዴት ነው?
የአይሁዳውያን ፋሲካ በዋለበት ምሽት ላይ ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር አነስ ያለ ዝግጅት ካደረገ በኋላ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:24) ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ኢየሱስ ተገደለ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ኢየሱስን በፋሲካ ዕለት መሥዋዕት ሆኖ ይቀርብ ከነበረው በግ ጋር አመሳስለውታል። (1 ቆሮንቶስ 11:24) የፋሲካ በዓል እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ እንደወጡ ያስታውሳቸው እንደነበር ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያም ክርስቲያኖችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንደወጡ ያስታውሳቸዋል። የፋሲካ በዓል ይከበር የነበረው በዓመት አንድ ጊዜ ሲሆን የሚውለውም በጨረቃ አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ላይ ነው፤ የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ በዓመት አንድ ጊዜ ያከብሩ ነበር።
በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ኒሳን 14 በሚውልበት ቀን ላይ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ያከብራሉ።