መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውርጃ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ “ውርጃ” የሚለውን ቃል፣ ሆን ብሎ ፅንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ አይጠቀምበትም። ሆኖም አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስን ጨምሮ ስለ ሕይወት ምን አመለካከት እንዳለው የሚጠቁሙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ።
ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው። (ዘፍጥረት 9:6፤ መዝሙር 36:9) አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስን ሕይወት ጨምሮ የሁሉንም ሰዎች ሕይወት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ስለዚህ ሆን ብሎ ፅንስን መግደል ነፍስ እንደ ማጥፋት ይቆጠራል።
አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና ያለጊዜዋ ብትወልድ ሆኖም ለሞት የተዳረገ ባይኖር ጉዳት ያደረሰው ሰው የሴትየዋ ባል የጠየቀውን ካሳ መክፈል አለበት፤ ፈራጆቹ የወሰኑበትን ካሳ መክፈል ይኖርበታል። ሆኖም ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት . . . እንዲመለስ ማድረግ አለብህ።”—ዘፀአት 21:22-25 a
የሰው ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው?
በአምላክ ዓይን የአንድ ሰው ሕይወት የሚጀምረው ፅንሱ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ ነው። አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማህፀን ውስጥ ያለን ሕፃን የሚገልጸው የእናቱ አካል ክፍል እንደሆነ አድርጎ ሳይሆን የራሱ ሕልውና እንዳለው ሰው አድርጎ ነው። አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለን ልጅና የተወለደን ልጅ የሚመለከትበት መንገድ ምንም ልዩነት እንደሌለው የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ንጉሥ ዳዊት “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ” በማለት በመንፈስ መሪነት ለአምላክ ተናግሮ ነበር። (መዝሙር 139:16) ዳዊት ገና ከመወለዱ በፊት እንኳ አምላክ የቆጠረው፣ የራሱ ሕልውና እንዳለው ሰው አድርጎ ነው።
በተጨማሪም አምላክ ነቢዩ ኤርምያስን ገና ከመወለዱ በፊት ለልዩ ዓላማ መርጦት ነበር። እንዲህ ብሎታል፦ “በማህፀን ውስጥ ሳልሠራህ በፊት አውቄሃለሁ፤ ከመወለድህም በፊት ቀድሼሃለሁ። ለብሔራት ነቢይ አድርጌሃለሁ።”—ኤርምያስ 1:5
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሐኪሙ ሉቃስ በማህፀን ውስጥ ያለን ልጅ እና አራስ ልጅን ለመግለጽ አንድ ዓይነት የግሪክኛ ቃል ተጠቅሟል።—ሉቃስ 1:41፤ 2:12, 16
አምላክ ውርጃ የፈጸሙ ሰዎችን ይቅር ይላል?
አዎ። ውርጃ የፈጸሙ ሰዎች አመለካከታቸውን አስተካክለው አምላክ ለሕይወት ያለውን አመለካከት ካዳበሩ ከልክ ባለፈ የጥፋተኝነት ስሜት መሠቃየት አያስፈልጋቸውም። “ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ነውና። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።” b (መዝሙር 103:8-12) ይሖዋ ውርጃ የፈጸሙ ሰዎችን ጨምሮ ቀደም ሲል ለፈጸሙት ኃጢአት ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ሰዎችን በሙሉ ይቅር ይላል።—መዝሙር 86:5
የእናትየው ወይም የልጁ ሕይወት አደጋ ላይ ከወደቀ ማስወረድ ችግር ይኖረዋል?
መጽሐፍ ቅዱስ በማህፀን ውስጥ ያለን ሕፃን አስመልክቶ ከሚናገረው ነገር አንጻር ‘በእናትየው ወይም በልጁ ላይ አደጋ ሊከሰት ይችላል’ በሚል ምክንያት ውርጃ መፈጸም ተገቢ አይሆንም።
በወሊድ ወቅት በተከሰተ ችግር የተነሳ ከእናትየው ወይም ከልጁ ሕይወት አንዱን ለመምረጥ የሚያስገድድ ሁኔታ ከስንት አንዴ ሊያጋጥም ይችላል። በዚህ ጊዜ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ግለሰቦች የእናትየውን ወይም የልጁን ሕይወት ለማትረፍ የራሳቸውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
a አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለእስራኤላውያን የተሰጠውን ይህን ሕግ፣ አሳሳቢው ነገር በፅንሱ ላይ ሳይሆን በእናትየው ላይ የደረሰው ጉዳት እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ተርጉመውታል። ሆኖም የዕብራይስጡ ጽሑፍ በእናትየውም ሆነ በፅንሱ ላይ የደረሰውን ጉዳት ሊያመለክት ይችላል።
b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18