የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ፊልጵስዩስ 4:8—“እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ . . . ማሰባችሁን አታቋርጡ”
“በመጨረሻም ወንድሞች፣ እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8 አዲስ ዓለም ትርጉም
“በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የፊልጵስዩስ 4:8 ትርጉም
አምላክ የሰው ልጆች ለሚያስቡት ነገር ትኩረት ይሰጣል፤ ምክንያቱም ወደ ድርጊት የሚመራው ሐሳብ ነው። (መዝሙር 19:14፤ ማርቆስ 7:20-23) በመሆኑም አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች በእሱ አመለካከት መጥፎ የሆኑ ሐሳቦችን ለማስወገድና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ነገሮች ለማሰብ ጥረት ያደርጋሉ።
ይህ ጥቅስ ክርስቲያኖች ‘ሳያቋርጡ ማሰብ’ ያለባቸውን ስምንት ዓይነት ጥሩ ነገሮች ይጠቅሳል።
“እውነት።” ይህ ቃል ትክክል የሆኑና እምነት የሚጣልባቸውን ነገሮች ያመለክታል፤ ይህም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች ይጨምራል።—1 ጢሞቴዎስ 6:20
“ቁም ነገር ያለበትን።” ይህ ሐረግ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ያመለክታል። እነዚህ ነገሮች ተራ፣ ከንቱ ወይም ያን ያህል ቦታ የማይሰጣቸው ነገሮች አይደሉም። አንድ ክርስቲያን ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰቡ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ያጠናክርለታል።—ቲቶ 2:6-8
“ጽድቅ።” ይህ ቃል ከሰብዓዊ ጥበብ አንጻር ሳይሆን ከአምላክ መሥፈርቶች አንጻር ትክክል የሆኑ ሐሳቦችንና ድርጊቶችን ያመለክታል።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 14:12
“ንጹሕ።” ይህ ቃል ቅዱስ የሆኑ ሐሳቦችንና ዝንባሌዎችን ያመለክታል፤ ቃሉ ከፆታዊ ጉዳዮች ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ሁሉንም የሕይወታችንን ዘርፎች ያካትታል።—2 ቆሮንቶስ 11:3
“ተወዳጅ።” ይህ ቃል አስደሳች የሆኑ እንዲሁም ጥላቻን፣ ምሬትንና ጠብን ሳይሆን ፍቅርን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ያመለክታል።—1 ጴጥሮስ 4:8
“በመልካም የሚነሳ።” ይህ ሐረግ አንድ ሰው መልካም ስም እንዲያተርፍ የሚያደርጉ ነገሮችን እንዲሁም አምላክን በሚያከብሩ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ነገሮችን ያመለክታል።—ምሳሌ 22:1
“በጎ።” ይህ ቃል የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚያሟሉ ነገሮችን ያመለክታል። እነዚህ ነገሮች ምንም እንከን አይወጣላቸውም።—2 ጴጥሮስ 1:5, 9
“ምስጋና የሚገባው።” ይህ ሐረግ በተለይ አምላክ አድናቆት የሚገባቸው አድርጎ የሚቆጥራቸውን ነገሮች ያመለክታል። አምላክ ያከናወናቸውን ምስጋና የሚገባቸው ሥራዎችም ይጨምራል፤ ሰዎች ስለ እነዚህ ነገሮች ማሰባቸው ጠቃሚ ነው።—መዝሙር 78:4
የፊልጵስዩስ 4:8 አውድ
ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ሮም ውስጥ የቁም እስር ላይ ነበር። ያም ቢሆን ደብዳቤው ደስታ የሚንጸባረቅበትና በርካታ የፍቅር መግለጫዎችን የያዘ ስለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን “የደስታ ደብዳቤ” ብለው ይጠሩታል።—ፊልጵስዩስ 1:3, 4, 7, 8, 18፤ 3:1፤ 4:1, 4, 10
ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ያሉትን መንፈሳዊ ወንድሞቹንና እህቶቹን ይወዳቸው ነበር፤ እንዲሁም እሱ ያገኘው ዓይነት ሰላምና ደስታ እንዲያገኙ ይፈልግ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:17, 18) በመሆኑም በደብዳቤው መደምደሚያ ላይ ደስተኛ እንዲሆኑ፣ ምክንያታዊ እንዲሆኑ፣ ምንጊዜም ወደ አምላክ በመጸለይ በእሱ እንዲታመኑ እንዲሁም አእምሯቸው ውስጣዊ ሰላምና ከአምላክ ጋር ሰላም በሚያስገኙላቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩር እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 4:4-9
የፊልጵስዩስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።