የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ኢሳይያስ 42:8—“እኔ እግዚአብሔር ነኝ”
“እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።”—ኢሳይያስ 42:8 አዲስ ዓለም ትርጉም
“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፣ ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።”—ኢሳይያስ 42:8 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የኢሳይያስ 42:8 ትርጉም
አምላክ መጠሪያ ስሙን የነገረን ከመሆኑም ሌላ ክብሩን ወይም ምስጋናውን ለጣዖታት እንደማያጋራ ገልጿል።
አምላክ ለራሱ ያወጣው ስም በአማርኛ አብዛኛውን ጊዜ “ይሖዋ” ተብሎ ይተረጎማል። a (ዘፀአት 3:14, 15) ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም በብሉይ ኪዳን (የዕብራይስጥና የአረማይክ ቅዱሳን መጻሕፍት) ውስጥ 7,000 ጊዜ ገደማ የሚገኝ ቢሆንም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “እግዚአብሔር” ወይም “ጌታ” በሚሉት የማዕረግ ስሞች ተክተውታል። ለዚህ አንዱ ምሳሌ መዝሙር 110:1 ነው፤ ጥቅሱ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። አዲሱ መደበኛ ትርጉም “ጌታ [ይሖዋ] ጌታዬን [ኢየሱስን] . . . አለው” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 2:34-36) አዲስ ዓለም ትርጉም መለኮታዊውን ስም በትክክለኛው ቦታ በማስገባት በሁለቱ “ጌቶች” መካከል መምታታት እንዳይፈጠር አድርጓል። እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ጌታዬን እንዲህ ብሎታል፦ ‘በቀኜ ተቀመጥ፤ ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ሁን።’”
በርካታ ምሁራን መለኮታዊው ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያምናሉ። እንዲህ ባለ ስም ሊጠራ የሚችለው እውነተኛው አምላክ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ዓላማውን ለመፈጸም ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን እንዲሁም ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን ሁሉ እንዲሆኑ ማድረግ የሚችለው እሱ ብቻ ነው።
ይሖዋ ፈጣሪያችንና ብቸኛው እውነተኛ አምላክ በመሆኑ ልናመልከው የሚገባው እሱን ብቻ ነው። ጣዖታትንና ምስሎችን ጨምሮ ሌላ ማንኛውም አካል አምልኮ አይገባውም።—ዘፀአት 20:2-6፤ 34:14፤ 1 ዮሐንስ 5:21
የኢሳይያስ 42:8 አውድ
በኢሳይያስ ምዕራፍ 42 የመጀመሪያ ቁጥሮች ላይ ይሖዋ ‘የመረጠው አገልጋዩ’ ስለሚያከናውነው ነገር ትንቢት ተናግሯል። አምላክ የመረጠውን አገልጋዩን በተመለከተ “እሱ ለብሔራት ፍትሕን ያመጣል” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 42:1) አምላክ ይህን ተስፋ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን እናገራለሁ። ገና ከመከሰታቸው በፊት ስለ እነሱ እነግራችኋለሁ።” (ኢሳይያስ 42:9) በአምላክ ‘ስለተመረጠው አገልጋይ’ የሚናገረው ትንቢት የተከሰተው ወይም የተፈጸመው በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ መሲሑ ወይም ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ነው።—ማቴዎስ 3:16, 17፤ 12:15-21
a የአምላክ ስም በዕብራይስጥ ሲጻፍ አራት ተነባቢ ፊደላትን የያዘ ነው፤ እነዚህ ፊደላት በአማርኛ የሐወሐ በሚሉት ፊደላት ይወከላሉ። አንዳንድ የአማርኛ ትርጉሞች የአምላክን ስም “ያህዌህ” ብለው ይተረጉሙታል። ለተጨማሪ መረጃ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ሀ4 ተመልከት።