ንድፍ አውጪ አለው?
ፍሩት ፍላይ የተባለችው ዝንብ አስደናቂ የበረራ ችሎታ
ዝንብ ለመግደል ሞክረህ ታውቃለህ? ከሆነ ይህን ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ተገንዝበህ መሆን አለበት። አብዛኛውን ጊዜ ዝንቦች፣ የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት በቅጽበት ማምለጥ ይችላሉ።
ሳይንቲስቶች፣ ፍሩት ፍላይ የተባሉት የዝንብ ዓይነቶች እንደ ጦር ጄት በአየር ላይ የመገለባበጥ ችሎታ እንዳላቸው አስተውለዋል፤ ሆኖም እነዚህ ዝንቦች ይህን የሚያደርጉት ከአንድ ሴኮንድ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ነው። ማይክል ዲከንሰን የተባሉ አንድ ፕሮፌሰር እንደተናገሩት እነዚህ ዝንቦች ሲወለዱ አንስቶ ‘ልምድ እንዳለው አብራሪ የመብረር ችሎታ’ አላቸው። ይህም ‘አንድን አራስ ሕፃን በጦር አውሮፕላን የማብረሪያ ክፍል ውስጥ አስገብቶ ሕፃኑ በትክክል ሲያበር’ የመመልከትን ያህል አስደናቂ ነው።
ተመራማሪዎች የእነዚህን ዝንቦች የበረራ ዘዴ በካሜራ ሲቀርፁት ዝንቦቹ ክንፋቸውን በሴኮንድ 200 ጊዜ እንደሚያርገበግቡ ተመልክተዋል። ያም ቢሆን ዝንቦቹ አደጋ ሲጋረጥባቸው አቅጣጫቸውን ቀይረው ከአደጋው ለመሸሽ ክንፋቸውን አንዴ ማርገብገብ ብቻ ይበቃቸዋል።
እነዚህ ዝንቦች አደጋ ሊደርስባቸው ሲል በምን ያህል ፍጥነት እርምጃ መውሰድ ይችላሉ? ዝንቦቹ፣ የሰዎች ዓይን ከሚርገበገብበት በ50 እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ፕሮፌሰር ዲከንሰን እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ዝንቦች አደጋ የመጣባቸው ከየት አቅጣጫ እንደሆነና በየት አቅጣጫ መሸሽ እንዳለባቸው ለማወቅ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ውስብስብ የሆነ ስሌት ይሠራሉ።”
የእነዚህ ዝንቦች ደቃቅ አንጎል እንዲህ ያለ አስደናቂ ነገር ማድረግ እንዴት እንደቻለ ለብዙ ተመራማሪዎች ሚስጥር ሆኖባቸዋል።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ፍሩት ፍላይ የተባለችው ዝንብ ያላት አስደናቂ የበረራ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?