ንድፍ አውጪ አለው?
የጥንዚዛ ቅርፊት
ዳያቦሊካል አይረንክላድ ቢትል (Phloeodes diabolicus) የተባለው ጥንዚዛ የሚኖረው በሰሜን አሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል ነው። ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት፣ ይህ ጥንዚዛ ከአካሉ ክብደት በ39,000 እጥፍ የሚበልጥ ክብደት መቋቋም ይችላል፤ እንዲሁም መኪና ቢሄድበትም እንኳ አይሞትም። ይህ ጥንዚዛ ይህን ያህል ከባድ ጭነት የመቋቋም ችሎታ ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?
በጥንዚዛው ጀርባና ሆድ ላይ ያሉት የቅርፊቱ ክፍሎች ጎንና ጎኑ ላይ ባሉ መጋጠሚያዎች የተያያዙ ናቸው። አንደኛው የመጋጠሚያ ዓይነት፣ ቅርፊቱ ጫና ሲያርፍበት ቅርጹ እንዳይቀየር ይከላከላል፤ ይህም የጥንዚዛውን ውስጣዊ የአካል ክፍሎች ከጉዳት ለመጠበቅ ያስችላል። ሌላኛው የመጋጠሚያ ዓይነት የመጀመሪያውን ያህል ድርቅ ያለ አይደለም፤ ይህም የቅርፊቱ ሌላ ክፍል ቅርጹ እንዲቀየር ያስችላል። ሦስተኛው የመጋጠሚያ ዓይነት ደግሞ ቅርፊቱ ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ያስችላል። ይሄኛው መጋጠሚያ፣ ጥንዚዛውን በጠባብ የዛፍ ቅርፊት ስንጥቅ ውስጥ እንዲገባ ወይም በቀጭን የዓለት ስንጥቅ ውስጥ እንዲደበቅ ያስችለዋል።
በተጨማሪም በጥንዚዛው ጀርባ ላይ ቅርፊቱን መሃል ለመሃል የሚያያይዘው መጋጠሚያ እርስ በርሳቸው የሚሰካኩ ጥርሶች አሉት፤ ይህም ጫናውን ለመበተን ያስችላል። ጥርሶቹ በፕሮቲኖች በተጣበቁ የተለያዩ ንብርብሮች የተሠሩ ናቸው። ጥንዚዛው ጫና ሲያርፍበት ፕሮቲኖቹ ይሰነጣጠቃሉ፤ ይህም ጥርሶቹ ሳይሰበሩ ጫናውን ውጠው እንዲያስቀሩ ያስችላል፤ የፕሮቲኖቹ ስንጥቅ ደግሞ በኋላ ላይ ይድናል።
ተመራማሪዎች የዚህን ጥንዚዛ ቅርፊት በመኮረጅ፣ ጫናን ወይም ግጭትን መቋቋም የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን፣ ድልድዮችን፣ ሕንፃዎችን ወይም ሌሎች ነገሮችን መሥራት እንደሚቻል ይገምታሉ።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ዳያቦሊካል አይረንክላድ ቢትል የተባለው ጥንዚዛ ቅርፊት በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?