ንድፍ አውጪ አለው?
ግራኒየን የተባሉት ዓሣዎች እንቁላል የሚጥሉበት ዘዴ
ካሊፎርኒያ ግራኒየን የተባሉት ትናንሽ ዓሣዎች በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና በባሃ ካሊፎርኒያ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው የፓስፊክ ባሕር ዳርቻ እንቁላላቸውን ይጥላሉ። እነዚህ ዓሣዎች እንቁላላቸውን ለመጣል አመቺ የሆነው ጊዜ የቱ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ይህም ለሚፈለፈሉት ዓሣዎች ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ግራኒየኖች እንቁላላቸውን የሚጥሉት፣ በሙሉ ወይም በአዲስ ጨረቃ ምክንያት ከሚከሰተው ኃይለኛ ማዕበል በኋላ ባሉት ሦስት ወይም አራት ምሽቶች ብቻ ነው። ሙሉ ወይም አዲስ ጨረቃ ከመውጣቷ በፊት ባለው ምሽት ላይ እንቁላላቸውን ከጣሉ ባሕሩ ዳርቻ ላይ ያለውን አሸዋ ጠራርጎ የሚወስደው ኃይለኛ ማዕበል እንቁላሎቹንም ጭምር ሊወስዳቸው ይችላል። ሆኖም ዓሣዎቹ እንቁላላቸውን የሚጥሉት ኃይለኛው ማዕበል ከረገበና ወደ ባሕሩ ዳርቻ የሚመጣው ውኃ ከቀነሰ በኋላ ነው። በዚህ ወቅት፣ በማዕበሉ ተጠርጎ የሄደው አሸዋ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ይመለሳል። ይህም አሸዋው ውስጥ የተቀበሩት እንቁላሎች፣ ቀስበቀስ በሚቆለለው አሸዋ ይበልጥ እንዲሸፈኑና ከአደጋ እንዲጠበቁ ያደርጋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዓሣዎቹ እንቁላላቸውን በሚጥሉበት የጸደይና የበጋ ወቅት በምሽቱ ክፍለ ጊዜ የሚኖረው ኃይለኛ ማዕበል በቀኑ ክፍለ ጊዜ ከሚኖረው ኃይለኛ ማዕበል በእጅጉ ይበልጣል። ይህም ዓሣዎቹ በተቻላቸው መጠን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ርቀው በመሄድ ቀጣዩ ኃይለኛ ማዕበል ሊደርስበት በማይችል ቦታ ላይ እንቁላላቸውን ለመጣል ያስችላቸዋል።
ግራኒየኖች እንቁላላቸውን ለመጣል ወደ ባሕሩ ዳርቻ አርቆ የሚወስዳቸው ኃይለኛ ማዕበል እስኪመጣ ድርስ ይጠብቃሉ። ከዚያም በሚመጣው ማዕበል ተገፍተው ወደ ባሕሩ ዳርቻ በጣም ርቀው በመሄድ አሸዋው ላይ ይቀራሉ። ውኃው ወደ ባሕሩ መመለስ ሲጀምር ሴቷ አሳ በጭራዋ ተጠቅማ እርጥቡን አሸዋ ሰርስራ በመግባት በከፊል ሰውነቷን ትቀብራለች። ከዚያም ከአምስት እስከ ስምንት ሴንቲ ሜትር በሚደርስ ጥልቀት እንቁላሏን ከጣለች በኋላ አንድ ወይም ሁለት ወንድ ዓሣዎች መጥተው እንቁላሉ እንዲዳብር ያደርጋሉ። ከዚያም ዓሣዎቹ እየተወናጨፉ ወደ ውኃው በመሄድ ቀጥሎ በሚመጣው ማዕበል አማካኝነት ወደ ባሕሩ ይመለሳሉ።
እንቁላሎቹ በእርጥቡ አሸዋ ውስጥ ተቀብረው ይዳብራሉ፤ ሆኖም እንቁላሎቹ መፈልፈል የሚጀምሩት የባሕሩ ሞገድ በአሸዋው ላይ የሚፈጥረው ንቅናቄ ሲያነቃቃቸው ነው። በመሆኑም ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ማለትም ቀጣዩ ኃይለኛ ማዕበል በሚመጣበት ወቅት እንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ። ሆኖም ቀጣዩ ኃይለኛ ማዕበል እስኪመጣ እስከ አራት ሳምንት ሊቆይ ስለሚችል እንቁላሎቹ ሳይፈለፈሉ እዚያው ይቆያሉ።
ታዲያ ምን ትላለህ፦ ግራኒየን የተባሉት ዓሣዎች ያላቸው፣ እንቁላላቸውን መቼና እንዴት መጣል እንዳለባቸው የማወቅ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?