ነሐሴ 6, 2019
ፈረንሳይ
በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ተከፈተ
ሐምሌ 25, 2019 ከፓሪስ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው በሉቭዬ ከተማ በሚገኘው የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ተከፈተ። የቤተ መዘክሩ ጭብጥ “መጽሐፍ ቅዱስ እና መለኮታዊው ስም በፈረንሳይኛ” የሚል ነው።
በቀላሉ የማይገኙና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው በፈረንሳይኛ የተዘጋጁ በርካታ መጽሐፍ ቅዱሶች በቤተ መዘክሩ ለእይታ ቀርበዋል። ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል በ1535 የተዘጋጀው የኦሊቬታ ፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ቅጂ ይገኝበታል፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ላ ቢብል ደ ሰርየር በመባልም ይታወቃል። የኦሊቬታ ትርጉም በፕሮቴስታንቶች የተዘጋጀና ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘ የመጀመሪያው የፈረንሳይኛ ትርጉም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች በቀጥታ የተተረጎመ የመጀመሪያው ፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስም ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ በተተረጎሙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይም ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ከእነዚህ መካከል በ1537 በእንግሊዝኛ የታተመው ማቲውስ ባይብል፣ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው ጄኔቫ ባይብል እና በፈረንሳይኛ የተዘጋጀው ጄኔቫ ባይብል ይገኙበታል። በቤተ መዘክሩ ላይ ከቀረቡት በቀላሉ የማይገኙ መጽሐፍ ቅዱሶች መካከል በ1541 የታተመው የዣክ ለፌቭር ዴታፕለ ፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሦስተኛ እትም፣ በ1541 በላቲን የተዘጋጀው ኦሪት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በፓሪስ የሚኖረው ሮበርት ኤትዬን የተባለ አታሚ በ1545 ያዘጋጀው የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም በልዮን የሚኖረው ዣን ደ ቱርን የተባለ አታሚ በ1557 ያዘጋጀው ፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይገኙበታል።
የኦሊቬታ ትርጉም፣ በላቲን የተዘጋጀው ኦሪት መጽሐፍ ቅዱስ፣ በኤትዬን የተዘጋጀው የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ እና የዣን ደ ቱርን መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም ይዘዋል። እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለሚገኘው የቤተ መዘክር ዲፓርትመንት በስጦታ የተበረከቱ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ ይገኙ ከነበሩት መጽሐፍ ቅዱሶች ጋር አብረው ለእይታ ቀርበዋል።
በቤተ መዘክር ዲፓርትመንት ውስጥ የሚሠራው ኤንሪኬ ፎርድ እንዲህ ብሏል፦ “በፈረንሳይ የተከፈተው ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር የፈረንሳይኛ መጽሐፍ ቅዱስን አስደናቂ ታሪክ ይዘክራል። በተጨማሪም ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ጉልህ ቦታ ያሳያል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ቤተ መዘክሮቻችን ውስጥ ልናሳያቸው የምንችላቸውን በቀላሉ የማይገኙና ትኩረት የሚስቡ መጽሐፍ ቅዱሶች መፈለጋችንን እንቀጥላለን።”