በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 27, 2019
ጋና

አዲስ ዓለም ትርጉም በንዜማ ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በንዜማ ቋንቋ ወጣ

ኅዳር 22, 2019 በባዊያ፣ ዌስተርን ሪጅን፣ ጋና በተካሄደ የክልል ስብሰባ ላይ ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በንዜማ ቋንቋ መውጣቱ ተገለጸ፤ የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ አራት ዓመት ፈጅቷል። የጋና ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ክዌሲ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን በአዳራሹ ለተሰበሰቡት 3,051 ሰዎች አብስሯል።

ሰባት ተርጓሚዎችን ያቀፈ ቡድን በሥራው ተካፍሎ ነበር። ከተርጓሚዎቹ አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም የሚጠቀመው ቀለል ያለ ቋንቋ ነው፤ በመሆኑም ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች ይህን ትርጉም በቀላሉ መረዳት ይችላሉ። ይህም አንባቢዎቹን ወደ አባታቸው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንደሚያነሳሳቸው ጥያቄ የለውም።”

የንዜማ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ አስፋፊዎች ቀደም ሲል የሚጠቀሙት በጋና የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ሆኖም ይህ ትርጉም የአምላክን ስም አይጠቀምም፤ እንዲሁም ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም ጋና ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋጋው ውድ ስለሆነ አንዳንድ አስፋፊዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት አቅማቸው አይፈቅድም ነበር።

በንዜማ ቋንቋ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ይዟል፤ የተጻፈው ለመረዳት ቀላል በሆነ ቋንቋ ነው፤ እንዲሁም የሚሰጠው በነፃ ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በጋና ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚያገለግሉት የንዜማ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ 1,532 አስፋፊዎች 330,000 ገደማ ለሚሆኑት የቋንቋው ተናጋሪዎች ለመስበክ በሚያደርጉት ጥረት እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።

ወንድሞቻችን በዚህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አማካኝነት “በይሖዋ ሕግ” ደስ እንዲላቸው ምኞታችን ነው።—መዝሙር 1:1, 2