ሚያዝያ 22, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ
የመጀመሪያው “የመንግሥት አዳራሽ” ከ85 ዓመት በኋላ በድጋሚ ተወሰነ
ወቅቱ 1935 ነው። በ1228 ፔንሳኮላ መንገድ፣ ሆኖሉሉ፣ ሃዋይ የሚገኘው “የመንግሥት አዳራሽ” ግንባታ ሲጀመር የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በቦታው ተገኝቶ ነበር። በዓለም ላይ “የመንግሥት አዳራሽ” ተብሎ የተጠራው የመጀመሪያው አዳራሽ ይህ ነው። ይህ አዳራሽ ለቀጣዮቹ ስምንት አሥርተ ዓመታት ይሖዋን ለማምለክ ጥቅም ላይ ውሏል። የፔንሳኮላ የስብሰባ አዳራሽ ከተገነባ 85 ዓመት ያለፈው ሲሆን አራት ጉባኤዎች የሃዋይ ፒጅንን ጨምሮ በአምስት ቋንቋዎች ስብሰባ ያካሂዱበታል። a
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ወንድሞቻችን ይህን ሕንፃ ሙሉ በሙሉ በማደስ ከየካቲት 11 እስከ 15, 2020 ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆን አደረጉ፤ ለጉብኝት ከተጋበዙት ሰዎች መካከል የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና መምህራን ይገኙበታል። እንግዶቹ በአስጎብኚ ታግዘው ሕንፃውን የጎበኙ ሲሆን ስለ ሕንፃው ታሪክ የሚገልጹ ሥዕሎችን ተመልክተዋል እንዲሁም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ወንድሞች የሰጡትን መግለጫ አዳምጠዋል። ፕሮግራሙ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን የካቲት 16 በሰጠው የውሰና ንግግር ተደመደመ።
ፕሮግራሙን በማዘጋጀቱ ሥራ የተካፈለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ጉብኝት የተዘጋጀው ለስብከት ባይሆንም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለማወቅ አጋጣሚ ላላገኙ ብዙ ሰዎች ትልቅ ምሥክርነት እንደሰጠ ይሰማናል።”
ፕሮግራሙ በሃዋይ ደሴቶች የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ስለ ውድ መንፈሳዊ ቅርሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ ያሳደገላቸው ከመሆኑም ሌላ “በባሕር ደሴቶችም የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ” የሚለው ትንቢት ሲፈጸም በዓይናቸው ማየት ችለዋል።—ኢሳይያስ 24:15
a በአሁኑ ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች የሚካሄዱት ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት ሳይሆን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነው።