ኅዳር 14, 2022
ዛምቢያ
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በምቡንዳ ቋንቋ ወጣ
ኅዳር 5, 2022 የዛምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሴፋስ ካሊንዳ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በምቡንዳ ቋንቋ መውጣቱን አብስሯል። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተነገረበት አስቀድሞ የተቀዳ ንግግር ከ1,500 ለሚበልጡ አድማጮች ተላልፏል። ንግግሩ እንዳበቃም መጽሐፍ ቅዱሱ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ተለቅቋል። በወረቀት የታተሙ መጽሐፍ ቅዱሶች ጥር 2023 ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምቡንዳ በዋነኝነት የሚነገረው በአንጎላና በዛምቢያ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በሰሜናዊ ሮዴዥያ (የአሁኗ ዛምቢያ) ለሚኖሩ የምቡንዳ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ምሥራቹን የሰበኩት በ1930ዎቹ ዓመታት ነው። በ2014 የምቡንዳ የትርጉም ቡድን ተቋቋመ። የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘው በዛምቢያ ምዕራባዊ ግዛት፣ ሞንጉ በተባለ ቦታ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች ካዘጋጁት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ሌላ በምቡንዳ ቋንቋ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብቻ ነው የሚገኘው። ሆኖም በውድ ዋጋ የሚሸጥና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ ትርጉም ነው። በዚህም የተነሳ የምቡንዳ ተናጋሪ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ በፊት በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶችን ለመጠቀም ተገድደው ነበር።
አንደኛው ተርጓሚ አዲስ የወጣውን መጽሐፍ ቅዱስ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ተፈጥሯዊ ለዛውን የጠበቀ፣ ግልጽ፣ ቀላል፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በትክክል የሚያስተላልፍ ትርጉም ነው።”
ሌላ ተርጓሚ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በአገልግሎት ላይ መጠቀም ስላሉት ውስንነቶች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በቀደመው ትርጉም ላይ የይሖዋ ስም አንድም ጥቅስ ላይ አይገኝም። ይሖዋን ለማመልከት ‘ጌታ አምላክ’ የሚለው የማዕረግ ስም ነው የገባው። ይህም ሰዎች የአምላክን ስም እንዳያውቁ እንቅፋት ሆኗል። አዲስ የወጣው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ግን የይሖዋን ስም 237 ጊዜ ይጠቅሳል።”
ይህ አዲስ ትርጉም፣ የምቡንዳ ተናጋሪ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡና በእሱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲጠነክር ኃይል ይሆናቸዋል ብለን እንተማመናለን።—ያዕቆብ 4:8