በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሳንቲያጎ፣ ቺሊ ከብሔራዊ ስታዲየሙ ውጭ እህቶች የጽሑፍ ጋሪ ጋ ቆመው

ታኅሣሥ 26, 2023
ቺሊ

የይሖዋ ምሥክሮች በቺሊ በተካሄደው የ2023 የአሜሪካ አህጉራት ጨዋታ ላይ ምሥራቹን ሰበኩ

የይሖዋ ምሥክሮች በቺሊ በተካሄደው የ2023 የአሜሪካ አህጉራት ጨዋታ ላይ ምሥራቹን ሰበኩ

ከጥቅምት 20 እስከ ኅዳር 5, 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ በቺሊ ባሉ የተለያዩ ከተሞች የ2023 የአሜሪካ አህጉራት ጨዋታ ተካሂዶ ነበር። የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በሚካሄዱበት በዚህ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ላይ ከ46 አገሮች የተውጣጡ ከ6,900 የሚበልጡ አትሌቶች ተሳትፈዋል። ወደ 1,500 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ውድድሮቹ በተካሄዱበት ጊዜ ላይ በተደረገው ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካፍለዋል። የስፓንኛ፣ የእንግሊዝኛና የፖርቱጋልኛ ጽሑፎችን የያዙ የጽሑፍ ጋሪዎች ተዘጋጅተው ነበር። ወንድሞቻችን ከአትሌቶችና ፕሮግራሙን ለመመልከት ከመጡ ሰዎች ጋር ብዙ ጥሩ ውይይቶችን ማድረግ ችለዋል።

ለምሳሌ፣ አንድ ታዋቂ አትሌት ወደ ጽሑፍ ጋሪው መጣ። ከዚያም በልጅነቱ ከእናቱ ጋር በስብሰባዎች ላይ ይገኝ እንደነበር ተናገረ። አትሌት መሆኑ ብዙ ገንዘብ ቢያስገኝለትም የጠበቀውን ያህል ደስታና እርካታ አላመጣለትም። የይሖዋ ምሥክሮቹ አንዳንድ የሚያበረታቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አነበቡለት፤ እሱም ላካፈሉት የሚያጽናና ሐሳብ አመሰገናቸው።

በልጅነቱ በስብሰባዎቻችን ላይ ይገኝ የነበረ ፖሊስም ወደ ጽሑፍ ጋሪው ሄዶ ወንድሞችን አነጋገራቸው። እነሱን ሲያያቸው በልጅነቱ ከጉባኤው ጋር ያሳለፈው አስደሳች ጊዜ ትዝ እንዳለው ገለጸላቸው። ወንድም በአካባቢው ስብሰባ የሚደረግበትን ቦታና ሰዓት ለፖሊሱ ነገረው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስና ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ሰጠው። ፖሊሱ የይሖዋ ምሥክሮችን ድጋሚ በማግኘቱ በጣም እንደተደሰተ ገልጿል።

ወደ ጽሑፍ ጋሪያችን ሄዳ ከአንዲት እህታችን ጋር የተነጋገረች የ19 ዓመት ሴት በቅርቡ ወደ አምላክ በመጸለይ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ እንዲረዳት ለምናው እንደነበር ተናገረች። እህታችን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና ስትጋብዛት ግብዣውን በደስታ ተቀበለች። በዚያኑ ቀን በኋላ ላይ እህታችን ከወጣቷ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቋሚነት እያጠናች ትገኛለች።

በዚህ ልዩ የስብከት ዘመቻ የተካፈሉ በቺሊ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከልብ እናደንቃቸዋለን። ትጋት የተሞላበት ጥረታቸው ያስገኘው ውጤት፣ ይሖዋ እሱን የሚፈልጉትን ሰዎች መባረኩን እንደሚቀጥል የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።​—ኢሳይያስ 55:6