በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ሲንጋፖር
በሲንጋፖር፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ስምንት ወጣት ወንዶች በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረዋል። ከእነዚህ መካከል አራቱ የታሰሩት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፤ ይህ የሆነው የመጀመሪያ እስራታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አቋማቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው። እነዚህ ወጣት ወንዶች ሲንጋፖር ውስጥ መፍትሔ ማግኘት የሚችሉበት ሕጋዊ መንገድ የለም። ምክንያቱም በሲንጋፖር ሕግ መሠረት ወታደራዊ አገልግሎት መስጠት ግዴታ ነው፤ እንዲሁም በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆን መብትን መንግሥት አይቀበልም።
አንድ ወጣት 18 ዓመት ሲሞላው የሲንጋፖርን ጦር ሠራዊት እንዲቀላቀል ይጠበቅበታል። በሕሊናው ምክንያት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆነ እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ይታሰራል። ይህ ጊዜ ሲያበቃ የሚለቀቅ ቢሆንም ወዲያውኑ የወታደር የደንብ ልብስ እንዲለብስና በወታደራዊ ሥልጠና እንዲካፈል ይታዘዛል። ይህን ለማድረግ አሁንም ፈቃደኛ ካልሆነ ለሁለተኛ ጊዜ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ፊት ይቀርብና እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሚደርስ እስራት ይፈረድበታል። በመሆኑም በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ወንዶች ሁለት ጊዜ እስራት ይፈረድባቸዋል፤ በአጠቃላይ እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ለሚደርስ ጊዜ ሊታሰሩ ይችላሉ።
ሲንጋፖር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደንቦች አልተቀበለችም
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አባል አገራቱ “በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ እውቅና ያገኘውን የሐሳብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት መብት ሕጋዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንደሆነ አድርገው መመልከት” እንዳለባቸው ሲያሳስብ ቆይቷል። ሲንጋፖር ከ1965 ጀምሮ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገር ብትሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለየ አቋም እንዳላት ገልጻለች። አንድ የሲንጋፖር መንግሥት ባለሥልጣን ሚያዝያ 24, 2002 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በላኩት ደብዳቤ ላይ “የግለሰቦች እምነት ወይም ድርጊት [ብሔራዊ ደህንነትን ከማስጠበቅ መብት ጋር] በሚጋጭበት ጊዜ መንግሥት ያለው ብሔራዊ ደህንነትን የማስከበር መብት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል። ባለሥልጣኑ “በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን በሁሉም አገሮች የሚሠራ መብት እንደሆነ አናምንም” በማለት አቋማቸውን በማያሻማ መንገድ ገልጸዋል።
የጊዜ ሰሌዳ
መስከረም 17, 2024
በአጠቃላይ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ታስረዋል።
ሚያዝያ 24, 2002
አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን በሲንጋፖር ሕግ ተቀባይነት እንደሌለው ገለጹ።
የካቲት 1995
የይሖዋ ምሥክር የሆኑ የሲንጋፖር ዜጎች የሚደርስባቸው ጭቆና ጨመረ፤ ብዙዎች ታሰሩ።
ነሐሴ 8, 1994
የሲንጋፖር ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ።
ጥር 12, 1972
የሲንጋፖር መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች የሰጠውን እውቅና ሰረዘ።