ነቅታችሁ ጠብቁ!
ምስሎችን ማምለክ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የካቶሊክ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው መጋቢት 25, 2022 በሴንት ፒተርስ ባሲሊካ በተካሄደ አንድ ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በማርያም ሐውልት ፊት በመቆም “ዓይናቸውን ጨፍነውና አንገታቸውን አጎንብሰው በልባቸው ጸሎት አቀረቡ።” ሰላም እንድታመጣ “ማርያምን ተማጸኑ።” አንድ የቫቲካን የዜና ዘገባ ደግሞ ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጸሎታቸው አማካኝነት የሰው ዘርን፣ በተለይም ሩሲያንና ዩክሬንን ለቅድስት ማርያም አሳልፈው እንደሰጡ’ ገልጿል።
አንተስ ምን ትላለህ? በምስሎች ፊት መጸለይ ወይም ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም ተገቢ ይመስልሃል? የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ተመልከት፦
“በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግ . . . አምላክ ነኝ።”—ዘፀአት 20:4, 5 a
“የእነሱ ጣዖቶች ከብርና ከወርቅ የተሠሩ፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። አፍ አላቸው፤ መናገር ግን አይችሉም፤ ዓይን አላቸው፤ ማየት ግን አይችሉም፤ ጆሮ አላቸው፤ መስማት ግን አይችሉም፤ አፍንጫ አላቸው፤ ማሽተት ግን አይችሉም፤ እጅ አላቸው፤ መዳሰስ ግን አይችሉም፤ እግር አላቸው፤ መራመድ ግን አይችሉም፤ በጉሮሯቸው የሚያሰሙት ድምፅ የለም። የሚሠሯቸውም ሆኑ የሚታመኑባቸው ሁሉ፣ እንደ እነሱ ይሆናሉ።”—መዝሙር 115:4-8
“እኔ ይሖዋ ነኝ። ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለማንም አላጋራም። ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።”—ኢሳይያስ 42:8 የግርጌ ማስታወሻ
“ከጣዖት አምልኮ ሽሹ።”—1 ቆሮንቶስ 10:14
“ከጣዖቶች ራቁ።”—1 ዮሐንስ 5:21
መጽሐፍ ቅዱስ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን በተመለከተ ምን እንደሚል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—ምስሎች” የሚለውን ርዕስ አንብብ፤ ወይም አምላክ ምስሎችን ተጠቅመን የምናቀርበውን አምልኮ ይቀበላል? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚከተሉት ጉዳዮች ምን እንደሚል ማወቅ ትፈልጋለህ?
Photo credit: Vincenzo Pinto/AFP via Getty Images
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።