ነቅታችሁ ጠብቁ!
የዘር እኩልነት የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ሁሉም ዘሮች እኩል የሚታዩበት ዓለም ብዙዎች የሚመኙት ነገር ነው፤ ሆኖም የሕልም እንጀራ ሆኖባቸዋል።
“ዘረኝነት ጠንቅ ያልሆነበት ማኅበረሰብ የለም፤ በተቋማት፣ በማኅበራዊ መዋቅሮች አልፎም በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ መርዙን መርጨቱን ቀጥሏል። መድልዎንና ኢፍትሐዊነትን ማስወገድ የተሳነን ለዚህ ነው።”—አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ
ታዲያ የዘር እኩልነት የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ ለዘር እኩልነት ያለው አመለካከት
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የተለያየ ዘር ላላቸው ሰዎች ያለውን አመለካከት ያስተምረናል።
አምላክ “በምድር ሁሉ ላይ [እንዲኖሩ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።”—የሐዋርያት ሥራ 17:26
“አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጅ ወደ ኋላ ዘሩ ቢመዘዝ ከአንድ ቤተሰብ እንደተገኘ ያስተምረናል፤ በተጨማሪም አምላክ ከየትኛውም ዘር ቢሆን ሰዎችን እንደሚቀበል ይነግረናል።
የዘር እኩልነት የሚረጋገጠው እንዴት ነው?
በዓለም ላይ እኩልነትን የሚያሰፍነው በሰማይ የተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ነው። ወደፊት ይህ መንግሥት፣ ተገዢዎቹ አንዳቸው ሌላውን በአክብሮት እንዲይዙ ያስተምራል። ሰዎች ዘረኝነትን ከነርዝራዡ ከልባቸው ነቅለው እንዲያስወግዱ ትምህርት ይሰጣቸዋል።
“የምድሪቱ ነዋሪዎች ስለ ጽድቅ ይማራሉ።”—ኢሳይያስ 26:9
“የእውነተኛ ጽድቅ ውጤት ሰላም፣ የእውነተኛ ጽድቅ ፍሬም ዘላቂ ጸጥታና ደህንነት ይሆናል።”—ኢሳይያስ 32:17
ዛሬም ሚሊዮኖች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው ሌሎችን በአክብሮትና በደግነት መያዝን ተምረዋል።
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ጭፍን ጥላቻ ፍቱን መድኃኒት ይገኝለት ይሆን?” የሚል ርዕስ ያለውን ንቁ! መጽሔት አንብብ።
ይህን ርዕሰ ጉዳይ አንስተህ ከልጆችህ ጋር መነጋገር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ከፈለግህ “ልጆችን ስለ ዘረኝነት ማስተማር” የሚለውን ርዕስ አንብብ።