የኢየሱስ ሞት ከሚያስገኛቸው በረከቶች ተጠቀም
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጋባዥ እንግዶቻቸው በየዓመቱ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ይሰበሰባሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የኢየሱስን ትእዛዝ በማክበር ነው። (ሉቃስ 22:19) በዚህ በዓል ላይ ስንገኝ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ሕይወቱን መስጠቱ ያለውን ትልቅ ትርጉም እንማራለን። በተጨማሪም የእሱ መሥዋዕት አሁንም ሆነ ወደፊት ለእያንዳንዳችን የሚያስገኛቸውን በረከቶች እንመለከታለን።—ዮሐንስ 3:16
አንተም ዘንድሮ በተከበረው የመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተህ ይሆናል። ታዲያ ኢየሱስ ሕይወቱን ለሰው ልጆች መስጠቱ ከሚያስገኛቸው በረከቶች መጠቀም ትፈልጋለህ? ኢየሱስ እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ልናደርጋቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮችን አስተምሯል፦
1. ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ተማር። ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።”—ዮሐንስ 17:3
2. የተማርከውን ተግባራዊ አድርግ። ኢየሱስ የእሱን ትምህርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ጎላ አድርጎ አስተምሯል። ለምሳሌ ታዋቂ የሆነውን የተራራ ስብከቱን የደመደመው ‘ቃሉን የሚሰሙና የሚያደርጉ’ ሰዎችን በማድነቅ ነው። (ሉቃስ 6:46-48) በሌላ ጊዜም “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:17
ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ የበለጠ ማወቅ ትፈልጋለህ? የተማርከውን በሕይወትህ እንዴት ተግባራዊ እንደምታደርግ ምክር ያስፈልግሃል? ለዚህ ሊጠቅሙህ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት
ብዙዎች፣ በነፃ በምንሰጠው አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርና በሕይወታቸው ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል።
ስለዚህ የትምህርት መርሐ ግብር ለማወቅ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከአስተማሪ ጋር” የሚለውን ገጽ ተመልከት።
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠኑበት ፕሮግራም ምን እንደሚመስል ለማወቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራምህ እንኳን ደህና መጣህ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች
የይሖዋ ምሥክሮች በሳምንት ሁለት ጊዜ በስብሰባ አዳራሾቻቸው ውስጥ ለአምልኮ ይሰበሰባሉ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ይብራራል፤ ምክሮቹን በሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርግም እንማራለን።
እነዚህ ስብሰባዎች ለሕዝብ ክፍት ናቸው፤ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰውም መገኘት ይችላል። ሁኔታው እንደየአካባቢው ቢለያይም በአካል ወይም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በስብሰባው ላይ መገኘት ይቻላል።
እነዚህ ስብሰባዎች ምን እንደሚመስሉ አጠቃላይ ግንዛቤ ለማግኘት በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
“የይሖዋ ምሥክሮች ሳምንታዊ ስብሰባዎች” የሚለው ገጽ ላይ በአካባቢህ ስብሰባው የሚካሄድበትን ቦታ ማግኘት ትችላለህ።
ኢንተርኔት ላይ የወጡ ርዕሶችና ቪዲዮዎች
ስለ ኢየሱስ ትምህርቶችና ሞቱ ስላስገኘው ጥቅም ብዙ መረጃ የሚሰጡ ርዕሶችና ቪዲዮዎች ድረ ገጻችን ላይ ይገኛሉ።
ለምሳሌ የአንድ ሰው ሞት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ “ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?” እና “ኢየሱስ የተሠቃየውና የሞተው ለምንድን ነው?” የሚሉትን ርዕሶች አንብብ ወይም ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።