የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ትችላለህ
መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት እገዛ ማግኘት
አንድን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ እየጎበኘህ ነው እንበል። በዚያ ሕዝቡም ሆነ ባሕሉ እንዲሁም ምግቡ ለአንተ እንግዳ ነው፤ ገንዘባቸውንም ቢሆን ከዚህ በፊት አይተኸው አታውቅም። ሁኔታው ግራ ሊያጋባህ እንደሚችል ግልጽ ነው።
አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታነብ ተመሳሳይ ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። በዚህ ጊዜ ወደማታውቀው አንድ ጥንታዊ ዓለም የሄድክ ያህል ነው። በዚያም ፍልስጤማውያን የሚባሉ ሕዝቦች ታገኛለህ፣ ‘ከልብስ መቅደድ’ ጋር የተያያዘ ያልተለመደ ባሕል ትመለከታለህ ወይም መና የሚባል ምግብና ድራክማ የሚባል ሳንቲም መኖሩን ታያለህ። (ዘፀአት 16:31፤ ኢያሱ 13:2፤ 2 ሳሙኤል 3:31፤ ሉቃስ 15:9) ይህ ሁሉ ግራ ሊያጋባህ ይችላል። በመሆኑም የማታውቀውን አገር ስትጎበኝ የሚመራህ ሰው እንደሚያስፈልግ ሁሉ በዚህ ረገድም ነገሮችን የሚያብራራልህ ሰው ብታገኝ ደስ አይልህም?
በጥንት ጊዜ የቀረበ እርዳታ
ቅዱሳን መጻሕፍትን በ16ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጻፍ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰዎች መልእክቱን መረዳት እንዲችሉ እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል ብሔር የመጀመሪያ መሪ የነበረው ሙሴ በሕጉ ላይ የተጻፈውን ነገር ለሕዝቡ “ያብራራ” ነበር።—ዘዳግም 1:5
ከዚያ ከአሥር መቶ ዓመታት ገደማ በኋላም ብቃት ያላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት አስተማሪዎች ይገኙ ነበር። በ455 ዓ.ዓ. በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ አደባባይ ላይ በርካታ ሕፃናትን ጨምሮ ብዛት ያላቸው አይሁዳውያን ተሰብስበው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎቹ ከቅዱስ ‘መጽሐፉ ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አነበቡላቸው።’ ይሁንና በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። “የተነበበውን ነገር ማስተዋል እንዲችል ሕዝቡን ይረዱት ነበር።”—ነህምያ 8:1-8
ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመሳሳይ የሆነ የማስተማር ሥራ አከናውኗል። እንዲያውም በሕዝቡ ዘንድ በዋነኝነት የሚታወቀው በአስተማሪነቱ ነበር። (ዮሐንስ 13:13) ብዛት ያላቸው ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችንም አስተምሯል። አንድ ወቅት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕዝብ በሰፊው የሚታወቀውን የተራራ ስብከቱን የሰጠ ሲሆን እነሱም “በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።” (ማቴዎስ 5:1, 2፤ 7:28) በ33 ዓ.ም. የጸደይ ወራት ኢየሱስ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ወዳለች አንዲት መንደር ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እየተነጋገረ በተጓዘበት ወቅት ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ገልጦላቸዋል [‘በግልጽ አብራርቶላቸዋል፣’ የግርጌ ማስታወሻ]።’—ሉቃስ 24:13-15, 27, 32
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ነበሩ። አንድ ወቅት ላይ ከኢትዮጵያ የሄደ ባለሥልጣን ቅዱሳን መጻሕፍትን እያነበበ ሳለ ፊልጶስ የተባለ አንድ ደቀ መዝሙር ወደ እሱ ቀርቦ “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊውም “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” በማለት መለሰለት። ከዚያም ፊልጶስ ያነብ የነበረው ክፍል ምን ትርጉም እንዳለው አብራራለት።—የሐዋርያት ሥራ 8:27-35
በዛሬው ጊዜ የሚገኝ እርዳታ
በጥንት ዘመን እንደነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በ239 አገሮች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር ሥራ ይካፈላሉ። (ማቴዎስ 28:19, 20) ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን በየሳምንቱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ። ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ቀደም ሲል የክርስትና እምነት ተከታዮች አልነበሩም። ለጥናቱ ምንም ዓይነት ክፍያ አይጠየቅም፤ እንዲሁም በሚያጠናው ግለሰብም ቤት ሆነ በሌላ አመቺ ቦታ ሊካሄድ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ኮምፒውተር ወይም ተንቀሳቃሽ መሣሪያ በመጠቀም በስልክ ወይም በቪዲዮ መጽሐፍ ቅዱስ ይማራሉ።
በዚህ ዝግጅት እንዴት መጠቀም እንደምትችል በዝርዝር ለማወቅ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን እንድታነጋግር እናበረታታሃለን። እንዲህ ካደረግክ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ሊገባው የማይችል መጽሐፍ ከመሆን ይልቅ “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ” የሚጠቅም እንደሆነ ትገነዘባለህ። በመሆኑም ‘ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ መታጠቅና ሙሉ በሙሉ ብቁ መሆን’ ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17