በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሄሮድስ ቤተ መቅደሱን እንደገና ሲገነባ ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመውት ነበር?

መጀመሪያ ላይ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ የገነባው በኮረብታ ላይ ሲሆን በዚህ ቅዱስ ሕንፃ ዙሪያ ለጥ ያሉ እርከኖችን ለመሥራት ሲል በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የማጠናከሪያ ግንቦች ገንብቶ ነበር። ሄሮድስ ከሰሎሞን የበለጠ ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ መገንባት ስለፈለገ ነባሩን ቤተ መቅደስ በአዲስ መልክ የመገንባትና የማስፋፋት ሥራ ጀመረ።

የሄሮድስ መሐንዲሶች ከቤተ መቅደሱ በስተሰሜን ያለውን ደልዳላ ቦታ ያሰፉ ሲሆን ይህን ያደረጉት በዚያ የነበሩትን እርከኖች ለማስፋት ብለው ነው። በስተደቡብ በኩል መድረኩ 32 ሜትር ያህል እንዲሰፋ ተደረገ። ይህን ለማከናወን በርካታ የድንጋይ ንጣፍና ሰፊ የማጠናከሪያ ግንብ ተገነባ። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ግንቡ 50 ሜትር ከፍታ ነበረው።

ሄሮድስ አይሁዳውያንን ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳይፈጸም እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የሚከናወኑት አገልግሎቶችና የሚቀርቡት መሥዋዕቶች እንዳይቋረጡ ጥንቃቄ አድርጓል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ ሄሮድስ ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ የማይፈቀድለት ሠራተኛ እንዳይገባ ሲል አይሁዳውያን ካህናትን አሠልጥኖ ድንጋይ ጠራቢዎችና አናፂዎች እንዳደረገ ገልጿል።

ሄሮድስ በሕይወት ቆይቶ የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተጠናቆ ለማየት አልበቃም። በ30 ዓ.ም. የመልሶ ግንባታ ሥራው ከተጀመረ 46 ዓመት ሆኖት ነበር። (ዮሐንስ 2:20) ሥራው የተጠናቀቀው የሄሮድስ የልጅ ልጅ በሆነው በዳግማዊ አግሪጳ ሲሆን ጊዜው ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ነበር።

የማልታ ነዋሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ነፍሰ ገዳይ እንደሆነ የተሰማቸው ለምንድን ነው?

የፍትሕ ሴት አምላክ (በስተግራ)፣ ፍትሕ የምታዛባውን ሴት አምላክ ስትመታ

በማልታ በሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች ላይ የግሪክ ሃይማኖት ጽንሰ ሐሳብ ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው አልቀረም። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ጳውሎስ ይጓዝበት የነበረው መርከብ ማልታ ላይ ከተሰበረ በኋላ ምን እንደተፈጸመ እንመልከት። ሐዋርያው አብረውት ይጓዙ የነበሩትና ከተሰበረው መርከብ የተረፉት ሰዎች እየሞቁ በነበረው እሳት ውስጥ ጭራሮ ሰብስቦ ሲጨምር አንዲት እፉኝት እጁ ላይ ተጣበቀች። በዚህ ጊዜ የደሴቲቱ ነዋሪዎች “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ መሆን አለበት፤ ከባሕሩ ተርፎ በደህና ቢወጣም እንኳ ፍትሕ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” አሉ።—የሐዋርያት ሥራ 28:4

እዚህ ጥቅስ ላይ “ፍትሕ” ተብሎ የተተረጎመው “ዳይክ” የሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። ቃሉ ፍትሕን በደፈናው ሊያመለክት ይችላል። ይሁንና ዳይክ ለፍትሕ የቆመችው ሴት አምላክ ስም እንደሆነ የግሪክ አፈ ታሪክ ይገልጻል። ዳይክ፣ የሰዎችን ጉዳይ እንደምትከታተል እንዲሁም ከሰው እይታ የተሰወሩ የፍትሕ መዛባት ድርጊቶችን ለዙስ እንደምትነግርና ጥፋተኛው እንዲቀጣ እንደምታደርግ ይታመን ነበር። በመሆኑም አንድ ምንጭ እንደገለጸው “ጳውሎስ ከባሕር ቢተርፍም እንኳ ሴት አምላክ ከሆነችው ከዳይክ ግን ሊያመልጥ አልቻለም . . . በእፉኝት አማካኝነት አግኝታዋለች” በማለት የማልታ ነዋሪዎች ሳያስቡ አልቀረም። ይሁንና ነዋሪዎቹ በጳውሎስ ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ በግልጽ ሲያዩ አመለካከታቸውን ለመቀየር ተገደዱ።