የሕይወት ታሪክ
በዓይኖቹ አምላክን የሚያገለግለው ሃይሮ
ከዓይኖቻችሁ በቀር መላ ሰውነታችሁን መቆጣጠር ባትችሉ ምን እንደሚሰማችሁ መገመት ትችላላችሁ? ወንድሜ ሃይሮ የሚኖረው በእንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው። ሆኖም ሕይወቱ ትርጉም ያለው ነው። ወንድሜ በሕይወቱ ደስተኛ መሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ ከመግለጼ በፊት ታሪኩን ልንገራችሁ።
ሃይሮ ሲወለድ ጀምሮ ስፓስቲክ ክዎድሪፕሌጂያ የተባለው የሴሬብራል ፖልዚ በሽታ ዓይነት አለበት። * በዚህም የተነሳ አብዛኛውን የሰውነት ክፍሎቹን መቆጣጠር አይችልም። አንጎሉ ለጡንቻዎቹ ግልጽ መልእክት ስለማያስተላልፍ እጆቹና እግሮቹ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ሁኔታ ይጥመለመላሉ ወይም ይንፈራገጣሉ። ሃይሮ ድንገት ሲንፈራገጥ በራሱ ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ጊዜ አለ። አጠገቡ ያሉ ሰዎችም ካልተጠነቀቁ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። የሚያሳዝነው ነገር፣ እንዲህ ዓይነቱን አደጋ ለመከላከል ሲባል ብዙውን ጊዜ እጆቹና እግሮቹ ከተሽከርካሪ ወንበሩ ጋር መታሰር አለባቸው።
በሥቃይ ለአካለ መጠን ደረሰ
የሃይሮ የልጅነት ሕይወት በሥቃይ የተሞላ ነው። ገና የሦስት ወር ሕፃን እያለ ራሱን እስኪስት ድረስ ሰውነቱ ይንዘፈዘፍ ነበር። ብዙ ጊዜ እማዬ የሞተ እየመሰላት ጥብቅ አድርጋ ይዛው በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ትሄድ ነበር።
የሃይሮ ሰውነት በተደጋጋሚ ይገተርና ይኮማተር ስለነበር ከጊዜ በኋላ አጥንቶቹ ተወላገዱ። በ16 ዓመቱ የዳሌ አጥንቱ ስለወለቀ በጭኑ፣ በሽንጡና በዳሌው ላይ ከባድ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት። ሃይሮ ከቀዶ ሕክምናው በሚያገግምበት ጊዜ ከሥቃዩ የተነሳ ሁልጊዜ ሌሊት ሌሊት ያለቅስ እንደነበር አሁንም ትዝ ይለኛል።
ሃይሮ ባለበት ከባድ የአካል ጉዳት የተነሳ እንደ መብላት፣ ልብስ መልበስና አልጋ ላይ መውጣት ያሉ የዕለት ተዕለት ተግባሮችን ለማከናወን የሌሎች እርዳታ ያስፈልገዋል። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ረገድ የሚረዱት እማዬና አባዬ ናቸው። ሃይሮ የሌሎች የማያቋርጥ እርዳታ የሚያስፈልገው ቢሆንም ወላጆቻችን በሕይወቱ ውስጥ የሰዎች ብቻ ሳይሆን የአምላክ እርዳታም ጭምር እንደሚያስፈልገው ሁልጊዜ ያስገነዝቡት ነበር።
መነጋገር የምንችልበት መንገድ አገኘን
ወላጆቻችን የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው፤ በመሆኑም ሃይሮ ገና ሕፃን ሳለ ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ያነቡለት ነበር። ወላጆቻችን፣ ሕይወት ትርጉም የሚኖረው አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ዝምድና ካለው ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። ሃይሮ የራሱን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የማይችልና ደካማ ቢሆንም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕና ጠንካራ ተስፋ ሊኖረው እንደሚችል ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ሃይሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት መረዳት መቻሉ ያሳስባቸው ነበር።
አንድ ቀን፣ ሃይሮ ትንሽ ልጅ እያለ አባዬ “ሃይሮ፣ እባክህ አናግረኝ” አለው። ከዚያም “የምትወደኝ ከሆነ ልታወራኝ ትችላለህ!” አለው። አባዬ ሌላው ቢቀር አንድ ቃል እንኳ እንዲናገር ሲለምነው የሃይሮ ዓይኖች እንባ አቀረሩ። ሃይሮ ስሜቱን በቃላት ለመግለጽ ቢጥርም ወፍራም የሆኑ የጉሮሮ ድምፆችን
ከማሰማት በቀር ቃል ማውጣት አልቻለም። አባቴ ሃይሮን ስላስለቀሰው አዘነ። ነገር ግን ሃይሮ ስሜቱን የገለጸበት መንገድ አባቴ የተናገረው ነገር እንደገባው የሚያሳይ ነበር። ችግሩ መናገር አለመቻሉ ነበር።ብዙም ሳይቆይ ወላጆቻችን፣ ሃይሮ ሐሳቡንና ስሜቱን ለመግለጽ ሲሞክር ዓይኖቹን በፍጥነት እንደሚያንቀሳቅስ አስተዋሉ። ሃይሮ ሌሎች ሐሳቡን እንዲረዱት ማድረግ አለመቻሉ ያበሳጨው ነበር። ይሁን እንጂ ወላጆቼ የዓይኖቹን እንቅስቃሴ ተረድተው የሚያስፈልገውን ነገር ሲያደርጉለት ፈገግ ይላል። ሃይሮ ‘አመሰግናለሁ’ የሚልበት መንገድ መሆኑ ነው።
የመናገር እክል ያለባቸውን ሰዎች የምትረዳ አንዲት ሐኪም፣ ከሃይሮ ጋር በተሻለ ሁኔታ ለመግባባት ‘አዎ’ ወይም ‘አይ’ በማለት የሚመለሱ ጥያቄዎችን በምንጠይቅበት ጊዜ ሁለቱን እጆቻችንን ወደ ላይ ማንሳት እንደምንችል ጠቆመችን። ቀኝ እጃችን ‘አዎ’ ማለት ሲሆን ግራ እጃችን ደግሞ ‘አይ’ ማለት ነው። በዚህ መንገድ ሃይሮ የሚፈልገውን ምርጫ በሚያመለክተው እጅ ላይ ዓይኑን በመትከል ፍላጎቱን መግለጽ ይችላል።
በሃይሮ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ክስተት
የይሖዋ ምሥክሮች በዓመት ሦስት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች የሚቀርቡባቸው ትላልቅ ስብሰባዎችን ያደርጋሉ። ሃይሮ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለሚጠመቁ ሰዎች ንግግር በሚቀርብበት ወቅት በጣም ይደሰት ነበር። ሃይሮ የ16 ዓመት ወጣት ሳለ አባቴ “ሃይሮ፣ መጠመቅ ትፈልጋለህ እንዴ?” ብሎ ጠየቀው። ሃይሮ ወዲያውኑ ዓይኑን በአባዬ ቀኝ እጅ ላይ በማሳረፍ ይህን እርምጃ መውሰድ እንደሚፈልግ ገለጸ። ከዚያም አባዬ “አምላክን ለዘላለም እንደምታገለግለው በጸሎት ቃል ገብተህለታል?” ብሎ ጠየቀው። አሁንም እንደገና ዓይኖቹን በአባዬ ቀኝ እጅ ላይ አሳረፈ። በዚህ መንገድ ሃይሮ ሕይወቱን ለይሖዋ ለመስጠት እንደወሰነ አወቅን።
ሃይሮ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ የክርስቲያኖች ጥምቀት ያለውን ትርጉም እንደተረዳ ግልጽ ሆነ። ስለዚህ በ2004 “የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችሁን ለእሱ ወስናችኋል?” ለሚለው ከሁሉ የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥያቄ መልስ ሰጠ። ሃይሮ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጠው ዓይኖቹን ወደ ላይ በማንሳት ነበር። በዚህ መንገድ አዎንታውን መግለጽ እንደሚችል አስቀድሞ ተነግሮት ነበር። በመሆኑም ሃይሮ በ17 ዓመቱ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
በአምላክ አገልግሎት ላይ ያተኮሩ ዓይኖች
በ2011 ሃይሮ፣ ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችልበት አዲስ መሣሪያ ይኸውም በዓይን እንቅስቃሴ የሚሠራ ኮምፒውተር አገኘ። ሃይሮ የዓይኑን ብሌን በማንቀሳቀስ በስክሪኑ ላይ ያሉትን ፕሮግራሞች መጠቀም ይችላል። በኮምፒውተሩ ላይ አንድን ፕሮግራም ለመክፈት፣ የፕሮግራሙ ምልክት ላይ ዓይንን ብልጭ ድርግም ማድረግ ወይም ምልክቱን አተኩሮ ማየት በቂ ነው። በኮምፒውተሩ ላይ ቃላትን ወይም ሐረጎችን የሚያመለክቱ ሥዕላዊ ምልክቶችን የያዘ ፕሮግራም አለ፤ ይህም ሃይሮ
ሐሳቡን መግለጽ እንዲችል ረድቶታል። ሃይሮ በእነዚህ ሥዕላዊ ምልክቶች ላይ ዓይኖቹን ብልጭ ድርግም ሲያደርግ ፕሮግራሙ ምልክቶቹ የሚያመለክቱትን ጽሑፍ ወደ ኤሌክትሮኒክ ድምፅ ይቀይረዋል።ሃይሮ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ እየጨመረ ሲሄድ ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያለው ፍላጎትም እያደገ መጣ። በየሳምንቱ በቤተሰብ በምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ብዙውን ጊዜ እኔንና ኮምፒውተሩን በየተራ ያየናል። ሃይሮ እንዲህ የሚያደርገው በክርስቲያን የጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ በጥያቄና መልስ በሚካሄዱ ፕሮግራሞች ላይ መስጠት የሚፈልገውን ሐሳብ እንድጽፍለት ነው።
ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ሃይሮ፣ አስቀድሞ የተዘጋጀው ሐሳብ የተቀመጠበትን ሥዕላዊ ምልክት ለማግኘት በትዕግሥት ስክሪኑን ሲያስስ ይቆያል፤ ከዚያም ኮምፒውተሩ፣ ሃይሮ አስቀድሞ ያዘጋጀውን ሐሳብ ያነብለታል። በዚህ መንገድ የጉባኤውን አባላት ባበረታታ ቁጥር ፊቱ በፈገግታ ይፈካል። ወጣት ከሆኑ የሃይሮ ጓደኞች አንዱ የሆነው አሌክስ “ሃይሮ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ሐሳብ ሁልጊዜ ያስደንቀኛል” በማለት ተናግሯል።
ሃይሮ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ለሌሎች ለመንገርም ዓይኖቹን ይጠቀማል። ይህን የሚያደርግበት አንዱ መንገድ እንስሳትና ከሁሉም ዓይነት ዘር የተውጣጡ ሰዎች በሰላም ተስማምተው ሲኖሩ የሚያሳይ ገነት የሚታይበትን ሥዕላዊ ምልክት በዓይኖቹ እንቅስቃሴ መክፈት ነው። ይህን ምልክት ሲከፍተው ኮምፒውተሩ “መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን እንዲሁም በሽታና ሞት እንደማይኖሩ ተስፋ ይሰጣል፤ ራእይ 21:4” የሚል ድምፅ ያሰማል። በዚህ ጊዜ አድማጩ ፍላጎት ካሳየ ሃይሮ ሌላ ሥዕላዊ ምልክት በመክፈት “ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ትፈልጋለህ?” የሚል ድምፅ እንዲሰማ ያደርጋል። የሚገርመው ነገር አያታችን ይህን ግብዣ ተቀበለ። ሃይሮ አንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር እያገዘው አያታችንን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስተምር ማየት በጣም አስደስቶን ነበር! ደስ የሚለው፣ አያታችን በነሐሴ 2014 ማድሪድ ውስጥ በተደረገው የክልል ስብሰባ ላይ ተጠመቀ።
ሃይሮ ለአምላክ ያደረ መሆኑን የትምህርት ቤት አስተማሪዎቹም አስተውለዋል። ከንግግር ጋር በተያያዘ ከሚረዱት ሐኪሞች አንዷ የሆነችው ሮሳሪዮ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ሃይማኖት ውስጥ ለመግባት ካሰብኩ የይሖዋ ምሥክር ነው የምሆነው። ሃይሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም እምነቱ፣ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲኖር እንደረዳው አይቻለሁ።”
“አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሃይሮ ሳነብለት ዓይኖቹ በደስታ ይበራሉ። (ኢሳይያስ 35:6) አንዳንዴ ተስፋ የሚቆርጥበት ጊዜ ቢኖርም በአጠቃላይ ሲታይ ደስተኛ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው በሕይወቱ ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዙት አምላክና ክርስቲያን የሆኑ ጓደኞቹ ስለሆኑ ነው። ሃይሮ ያለው ብሩሕ አመለካከት እንዲሁም ጠንካራ እምነት በአስቸጋሪ ሁኔታም እንኳ ይሖዋን ማገልገል ሕይወታችንን ትርጉም ያለው እንደሚያደርገው ምሥክር ነው።
^ አን.5 ሴሬብራል ፖልዚ የተባለው በሽታ፣ በአንጎል ላይ በሚደርስ ጉዳት የተነሳ የሰውነትን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ከባድ እንዲሆን የሚያደርጉ የጤና እክሎች የሚጠሩበት ስያሜ ነው። በተጨማሪም ይህ በሽታ የሰውነት መንዘፍዘፍ፣ የአመጋገብ ልማድ መዛባት እንዲሁም የመናገር ችግር ሊያስከትል ይችላል። ስፓስቲክ ክዎድሪፕሌጂያ የተባለው የጤና እክል ከሁሉ የከፋው የሴሬብራል ፖልዚ በሽታ ዓይነት ሲሆን እጆችና እግሮች ግትር እንዲሉ ብሎም አንገት እንዲልፈሰፈስ ሊያደርግ ይችላል።