የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሥራህ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው
ጠንክሮ መሥራት ጊዜ ያለፈበት ነገር ነው?
ዕቃዎችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የማጓጓዝ አገልግሎት በሚሰጥ ድርጅት ውስጥ የሚሠራው አሌክስ አንዱን ካርቶን የጭነት መኪናው ላይ ከጫነ በኋላ በረጅሙ ተነፈሰ። ከዚያም እንዲህ ብሎ አሰበ፦ ‘የትም የማያደርሰኝን ይህን ሥራ የምሠራው ለምንድን ነው? መቼ ነው የሚያልፍልኝ? መሥራት ባይኖርብኝ ኖሮ ከዚህ የተሻለ ሕይወት መኖር በቻልኩ ነበር!’
እንደ አሌክስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ከባድ ሥራ መሥራት አያስደስታቸውም። አሮን የሚባል መካኒክ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች ‘ዝቅ ተደርጎ የሚታይ’ ሥራ መሥራት ለእነሱ እንደማይመጥን ያስባሉ። አብዛኞቹ ሰዎች ‘ይህን ሥራ የምሠራው የተሻለ ሥራ እስከማገኝ ድረስ ብቻ ነው’ የሚል አመለካከት ያላቸው ይመስላል።”
ብዙ ሰዎች ጠንክረው መሥራት እንደማያስፈልጋቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ምናልባት መገናኛ ብዙኃን በጣም ጥሩ የሚባለው ኑሮ ቅንጦትና ድሎት ያለበት እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡት ሐሳብ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው ይሆናል። ማቲው የተባለ አንድ የጥገና ሠራተኛ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች፣ መተዳደሪያ ለማግኘት ብዙ የሚለፋ ሰው የዚያኑ ያህል ስኬታማ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።” ሼን የተባለ አንድ የጽዳት ሠራተኛም ተመሳሳይ አዝማሚያ መኖሩን አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን አሁን፣ ሰዎች ትንሽ ሥራ ሠርተው ብዙ እንዲከፈላቸው ይጠብቃሉ።”
በሌላ በኩል ደግሞ ስኬታማ የሆኑ ብዙ ሰዎች ጠንክሮ መሥራት ያስደስታቸዋል። የግንባታ ሠራተኛ የሆነው የ25 ዓመቱ ዳንኤል “ጠንክሮ መሥራት በተለይ ደግሞ ለተገቢው ዓላማ ከሆነ እጅግ የሚክስ እንደሆነ ይሰማኛል” ብሏል። የ23 ዓመቱ አንድሬም በዚህ ሐሳብ ይስማማል። “ደስታና እርካታ ከሥራ ጋር የተዛመዱ ነገሮች እንደሆኑ አምናለሁ” ብሏል። አክሎም “ብዙ አለመሥራት ወይም ራስን በሥራ አለማስጠመድ ዘላቂ ደስታን ከማምጣት ይልቅ ሕይወት አሰልቺ እንዲሆን ያደርጋል!” በማለት ተናግሯል።
እንደ ዳንኤልና አንድሬ ያሉ ሰዎች፣ ጠንክሮ ስለ መሥራት እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት እንዲያዳብሩ የረዳቸው ምንድን ነው? በአጭሩ ለመግለጽ፣ በሕይወታቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋላቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጠንክሮ መሥራትን አይከለክልም፤ እንዲያውም ታታሪ መሆንና ጽናትን ያበረታታል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ሥራ መሥራት እንዳለብን በመግለጽ ብቻ አይወሰንም። ከሥራችን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነም ይነግረናል።
ከሥራህ ደስታ እንድታገኝ የሚረዱህ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው? እንዲህ ካሉት መመሪያዎች መካከል ጥቂቶቹ ቀጥሎ ባለው ርዕስ ላይ ተብራርተዋል።