አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
የገና በዓልን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
በመላው ዓለም የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ገናን ያከብራሉ። አንዳንዶቹ በዓሉን የሚያከብሩት ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ ስለሚፈልጉ ነው። ለሌሎች ደግሞ በዓሉ ስለ አምላክ የሚያስቡበት ወይም ድሆችንና ችግረኞችን የሚረዱበት ጊዜ ነው። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ጥሩ ተግባራት እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥሩ ተግባራት መጥፎ ከሆኑት የዚህ በዓል ገጽታዎች ጋር የተያያዙ ናቸው።
አንደኛ፣ የገና በዓልን የሚያከብሩ ብዙ ሰዎች በዓሉ የኢየሱስ ልደት የሚከበርበት ቀን እንደሆነ ቢያምኑም ብዙ የታሪክ ምሁራን ኢየሱስ የተወለደበት ቀን በእርግጠኝነት እንደማይታወቅ ይናገራሉ። ዘ ክርስቺያን ቡክ ኦቭ ዋይ እንደሚገልጸው “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከጣዖት አምልኮ ልማዶች መጠበቅ ይፈልጉ ስለነበር የኢየሱስ ልደት ቀን ብለው አንድን ዕለት ለመወሰን ፈቃደኞች አልነበሩም።” ኢየሱስ የራሱንም ሆነ የሌላ ሰውን የልደት በዓል እንዳከበረ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለመገኘቱ ልብ ሊባል ይገባዋል። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የእሱን ሞት መታሰቢያ እንዲያከብሩ አዝዟል።—ሉቃስ 22:19
ሁለተኛ፣ በገና በዓል ላይ የሚደረጉት አብዛኞቹ ልማዶች የክርስቲያኖች እንዳልሆኑና ከጣዖት አምልኮ ልማዶች የመጡ እንደሆኑ ብዙ ምሁራን ይስማማሉ። ከእነዚህ መካከል ሳንታ ክላውስ (የገና አባት)፣ ሚስልቶ (ትናንሽ ፍሬዎች ያሉት ተክል)፣ የገና ዛፍ፣ ስጦታ መለዋወጥ፣ ሻማ ማብራት፣ ዩል ሎግ (ለገና በዓል የሚቀርብ የኬክ ዓይነት)፣ የአበባ ጉንጉን ማንጠልጠል እና የገና መዝሙሮች ይገኙበታል። ዚ ኤክስተርናልስ ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች የተባለው መጽሐፍ ከእነዚህ ልማዶች መካከል ስለ አንዳንዶቹ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የገና ስጦታዎችን በምንሰጥበት ወይም በምንቀበልበት እንዲሁም የአበባ ጉንጉን በቤታችን ወይም በቤተ ክርስቲያናችን በምንሰቅልበት ጊዜ የጣዖት አምልኮ ልማዶችን እየተከተልን ሊሆን እንደሚችል የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?”
“የገና ስጦታዎችን በምንሰጥበት ወይም በምንቀበልበት እንዲሁም የአበባ ጉንጉን በቤታችን ወይም በቤተ ክርስቲያናችን በምንሰቅልበት ጊዜ የጣዖት አምልኮ ልማዶችን እየተከተልን ሊሆን እንደሚችል የምናውቅ ስንቶቻችን ነን?”
ይሁንና እነዚህን ምንም ጉዳት የሌላቸው የሚመስሉ ልማዶችን መከተል ስህተቱ ምን እንደሆነ ግራ ያጋባህ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ እንዲሆንህ ቀጥሎ የቀረበውን ሦስተኛውን ነጥብ ተመልከት። አምላክ የጣዖት አምልኮ ልማዶች ከንጹሕ አምልኮ ጋር እንዲቀላቀሉ አይፈልግም። ይሖዋ አምላክ በጥንቷ እስራኤል ለነበሩት ዓመፀኛ የሆኑ ሕዝቦቹ በነቢዩ አሞጽ አማካኝነት እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ዓመት በዓላችሁን ተጸይፌአለሁ፤ ጠልቼውማለሁ፤ . . . የዝማሬህን ጩኸት ከእኔ አርቅ።”—አሞጽ 5:21, 23
አምላክ እንዲህ ዓይነት ኃይለኛ መልእክት ያስተላለፈው ለምንድን ነው? በጥንቱ ሰሜናዊ የእስራኤል መንግሥት የነበሩ ሰዎች ምን ያደርጉ እንደነበር ተመልከት። ኢዮርብዓም የተባለው የመጀመሪያው ንጉሣቸው፣ የወርቅ ጥጆችን ሠርቶ ዳንና ቤቴል በተባሉ ከተሞች ውስጥ በማስቀመጥ ሕዝቡ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ይሖዋን በተገቢው መንገድ እንዳያመልኩ አደረገ። ንጉሡ በዓሎችን ያቋቋመ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ በዓሎቹን እንዲያከብሩ የሚረዱ ካህናትን ሾመ።—1 ነገሥት 12:26-33
እነዚህ እስራኤላውያን ያደረጉት ነገር መጥፎ አይመስል ይሆናል። ደግሞም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያደረጉት አምላክን ለማምለክና እሱን ለማስደሰት ብለው ነበር። አምላክ በአሞጽና በሌሎች ነቢያት በኩል የተናገራቸው ኃይለኛ መልእክቶች እንደዚህ ስላሉት ድርጊቶች ምን እንደሚሰማው በግልጽ ያሳያሉ። አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ በኩል “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል። (ሚልክያስ 3:6) ይህም አምላክ በዛሬው ጊዜ በገና በዓል ወቅት ስለሚደረጉት የተለያዩ ልማዶች ምን እንደሚሰማው ይጠቁመናል።
በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከላይ የተገለጹትን እውነታዎች ከመረመሩ በኋላ ገናን ላለማክበር ወስነዋል። ከዚህ ይልቅ በዓመቱ ውስጥ በፈለጉት ጊዜ ላይ ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ እንዲሁም ድሆችንና ችግረኞችን በመርዳት ደስታና እውነተኛ እርካታ ማግኘት ችለዋል።