የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በእርግጥ ሰይጣን አለ?
ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል?
መኖር አለመኖሩን ማወቅ አዳጋች ነው። ቀለምም ሆነ ሽታ የለውም፤ በመሆኑም ብዙ ሰዎች ሳያውቁት ሰለባው ይሆናሉ። በመላው ዓለም በመመረዝ ምክንያት ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ምናልባትም ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ሞት ተጠያቂ ነው፤ ይህ አደገኛ ነገር ካርቦን ሞኖክሳይድ የተባለው ጋዝ ነው። ይሁን እንጂ መሸበር አይኖርብህም። ይህ ጋዝ መኖር አለመኖሩን ማወቅና ራስህን መጠበቅ የምትችልባቸው መንገዶች አሉ። ብዙ ሰዎች ይህ ጋዝ መኖሩን የሚጠቁም መቆጣጠሪያ ያስገጥማሉ፤ ከዚያም መቆጣጠሪያው የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሲያሰማ እርምጃ ይወስዳሉ።
እንደ ካርቦን ሞኖክሳይድ ሁሉ ሰይጣንም በዓይን ስለማይታይ ተጽዕኖ እያደረገብን መሆን አለመሆኑን ማወቅ አዳጋች ሊሆንብን ይችላል፤ በመሆኑም ሰይጣን እጅግ አደገኛ ጠላት ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ሊረዳን ይችላል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አምላክ የሰጠህን ነገሮች የምትጠቀምባቸው ከሆነ ሰይጣንን የምትፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
የመምረጥ ነፃነት። ያዕቆብ 4:7 “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል” በማለት ይነግረናል። ሰይጣን ከፍተኛ ኃይል ቢኖረውም እንኳ አንተ ማድረግ የማትፈልጋቸውን ነገሮች እንድታደርግ ሊያስገድድህ አይችልም። ምክንያቱም የመምረጥ ነፃነት አለህ። 1 ጴጥሮስ 5:9 “በእምነት ጸንታችሁ በመቆም [ዲያብሎስን] ተቃወሙት” ይላል። ኢየሱስ ሰይጣን ላቀረበለት ሦስት ማባበያዎች የማያወላውል መልስ እንደሰጠ አስታውስ፤ በዚህ ጊዜ ሰይጣን ትቶት ሄደ። (ማቴዎስ 4:11) አንተም ከፈለግክ ሰይጣን የሚያመጣቸውን ፈተናዎች መቋቋም ትችላለህ።
ከአምላክ ጋር መወዳጀት። ያዕቆብ 4:8 ‘ወደ አምላክ እንድንቀርብ’ ያበረታታናል። ይሖዋ የእሱ የቅርብ ወዳጅ እንድትሆን ጋብዞሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ከአምላክ ጋር ወዳጅ ለመሆን በመጀመሪያ ስለ እሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማር አለብህ። (ዮሐንስ 17:3) ስለ ይሖዋ የምትማረው ነገር እሱን እንድትወደው ያደርግሃል፤ እሱን መውደድህ ደግሞ ፈቃዱን እንድታደርግ ያነሳሳሃል። (1 ዮሐንስ 5:3) በሰማይ ወዳለው አባትህ ይበልጥ እየቀረብክ ስትሄድ እሱስ ምን ያደርጋል? ያዕቆብ ‘እሱም ወደ አንተ ይቀርባል’ ብሏል።
ጥበቃ እንደምናገኝ የተሰጠን ተስፋ። ምሳሌ 18:10 “[የይሖዋ] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” ይላል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ሲባል የአምላክ ስም ምትሃታዊ ኃይል አለው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ስም በጥልቅ የሚያከብሩ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ይህን ስም በመጥራት ጥበቃ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ምሳሌዎች። ሥራ 19:19 በኤፌሶን የነበሩ ሰዎች ወደ ክርስትና ሲለወጡ ስላደረጉት አስገራሚ ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሁሉ ሰው ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ ሃምሳ ሺህ የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት።” * እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ዋጋቸው ምንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ያላቸውን ነገሮች በሙሉ አቃጥለዋል። እነሱ ከተዉት ምሳሌ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ይህ ዓለም በአስማትና በመናፍስታዊ ድርጊት ተሞልቷል። ምንም ጉዳት የሌላቸው የሚመስሉ ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ግንኙነት ያላቸው ዕቃዎችና ልማዶች እንኳ ለአጋንንት ጥቃት ሊያጋልጡ ይችላሉ። በመሆኑም ምንም ዓይነት መሥዋዕት ቢያስከፍልህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማስወገድህ አስፈላጊ ነው።—ዘዳግም 18:10-12
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሮሄሊዮ 50 ዓመት እስኪሆነው ድረስ ሰይጣን መኖሩን አያምንም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አመለካከቱ ተቀየረ። ለምን? ሮሄሊዮ እንዲህ ብሏል፦ “በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀት ዲያብሎስ መኖሩን አሳመነኝ። አሁንም ቢሆን በእሱ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳልወድቅ እየጠበቀኝ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን ማወቄ ነው።”
“ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁት እውቀት ዲያብሎስ መኖሩን አሳመነኝ። አሁንም ቢሆን በእሱ ተጽዕኖ ውስጥ እንዳልወድቅ እየጠበቀኝ ያለው መጽሐፍ ቅዱስን ማወቄ ነው”
ሰይጣን የማይኖርበትን ጊዜ ለማየት ትጓጓለህ? ይህ ጊዜ መምጣቱ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብዙዎችን የሚያሳስተው ዲያብሎስ “ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ” የሚወረወርበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። (ራእይ 20:10) እርግጥ ነው፣ እሳትና ድኝ ቃል በቃል አንድን የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር ሊጎዱ አይችሉም። በመሆኑም የእሳቱ ሐይቅ ዘላለማዊ ጥፋትን የሚያመለክት መሆን አለበት። አዎን፣ ሰይጣን ለዘላለም ይጠፋል። ያ ጊዜ ለአምላክ ወዳጆች በጣም የሚያስደስት ወቅት ይሆናል!
እስከዚያው ድረስ ግን ስለ ይሖዋና ስለ ባሕርያቱ የቻልከውን ያህል መማርህን ቀጥል። * “ሰይጣን የለም!” ማለት በሚቻልበት ጊዜ በሕይወት መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ።
^ አን.8 እዚህ ላይ የተጠቀሰው የብር ሳንቲም የሮማውያን ዲናር ከሆነ ይህ ገንዘብ ከ50,000 ሠራተኞች የቀን ደመወዝ ጋር የሚተካከል ነው፤ ይህ ደግሞ በጣም ብዙ ገንዘብ ነው!
^ አን.11 ስለ ሰይጣን እንዲሁም አምላክ መናፍስታዊ ድርጊትን በተመለከተ ስላለው አመለካከት ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ተመልከት። ይህን መጽሐፍ ለማግኘት አንድ የይሖዋ ምሥክር ጠይቅ።