የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ
ዓለምን የቀየረው ጦርነት
ከመቶ ዓመት በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ወደ ጦር ሜዳ ዘመቱ። እነዚህ ወጣቶች ወደ ጦርነቱ ሆ ብለው የገቡት በወቅቱ ገንኖ በነበረው የብሔራዊ ስሜት ማዕበል ተነድተው ነበር። አንድ አሜሪካዊ ወዶ ዘማች “ከፊታችን ስለሚጠብቀን አስደናቂ ጊዜ ሳስብ በደስታ እፈነድቃለሁ” በማለት በ1914 ጽፎ ነበር።
ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ይህ ደስታ ወደ ምሬት ተለወጠ። እነዚያ ታላላቅ ሠራዊቶች በቤልጂየምና በፈረንሳይ አረንቋ ውስጥ ለዓመታት ሲዳክሩ ይቆያሉ ብሎ ያሰበ አልነበረም። በዚያን ጊዜ ሰዎች ጦርነቱን “ታላቁ ጦርነት” ብለው ሰይመውት ነበር። በዛሬው ጊዜ ደግሞ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሎ ይጠራል።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ካለቁት ሰዎች አንጻር በእርግጥም ይህ ጦርነት ታላቅ ነበር። በዚህ ጦርነት 10 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች እንደሞቱና 20 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳተኛ እንደሆኑ ይገመታል። ከዚህም ሌላ ጦርነቱ የሰው ልጆች የፈጸሙት እጅግ አሳፋሪ ስህተት ውጤት ነው። የአውሮፓ የፖለቲካ ሰዎች በአገራት መካከል የተፈጠሩ ውጥረቶች ተባብሰው ወደ ዓለም አቀፍ ጦርነት እንዳይመሯቸው ማድረግ አልቻሉም። ከሁሉ በላይ ደግሞ “ታላቁ ጦርነት” ታላቅ ጠባሳ ትቶ አልፏል። ጦርነቱ ዓለምን በጣም የቀየረ ሲሆን ያስከተለው መዘዝ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ሰዎችም ተርፏል።
መተማመን እንዳይኖር ያደረጉ ስህተቶች
አንደኛው የዓለም ጦርነት የፈነዳው በተሳሳተ ውሳኔ ምክንያት ነበር። “በ1914 ሰላማዊ የበጋ ወቅት” የአውሮፓ መሪዎች፣ “በእንቅልፍ ልቡ ሲራመድ ሳይታወቀው ተደናቅፎ ገደል ውስጥ እንደወደቀ” ሰው እንደሆኑ በአንድ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል።—ዘ ፎል ኦቭ ዘ ዳይናስቲስ—ዘ ኮላፕስ ኦቭ ዚ ኦልድ ኦርደር 1905-1922
የኦስትሪያው አልጋ ወራሽ መገደል፣ ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ መንግሥታት በሙሉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሳይፈልጉ ወደ ጦርነት እንዲገቡ አደረጋቸው። ጦርነቱ ከተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ለጀርመኑ መራሄ መንግሥት “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የተፈጠረው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። እሳቸውም በሐዘን ተውጠው “ብናውቀውማ ጥሩ ነበር” የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑትን መጥፎ ውሳኔዎች ያደረጉት መሪዎች፣ ውሳኔያቸው ምን መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አልገባቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ምሽግ ውስጥ ሆነው የሚዋጉት ወታደሮች ብዙም ሳይቆይ እውነታው ግልጽ ሆነላቸው። የፖለቲካ መሪዎቻቸው ጉድ እንዳደረጓቸው፣ ቀሳውስቶቻቸው እንዳታለሏቸውና የጦር መሪዎቻቸውም አሳልፈው እንደሰጧቸው ተረዱ። ይህ የሆነው እንዴት ነው?
የፖለቲካ መሪዎቹ ጦርነቱ አዲስና የተሻለ ዓለም እንዲመጣ መንገድ እንደሚከፍት ቃል ገብተው ነበር። የጀርመኑ መራሄ መንግሥት “የምንዋጋው ኢንዱስትሪዎቻችን ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ መስፋፋት እንዲችሉ ለማድረግ፣ ታላቁን ታሪካችንን ጠብቀን ለማቆየት እንዲሁም የወደፊት ሕይወታችንን አስተማማኝ ለማድረግ ስንል ነው” በማለት ተናግረው ነበር። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን ጦርነቱ “ዓለም ዲሞክራሲ የሚያብብባት ቦታ እንድትሆን” እንደሚያደርግ የሚገልጽ ታዋቂ መፈክር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የብሪታኒያ ሕዝብ ደግሞ ይህ ውጊያ “ጦርነትን ለማስቆም የሚደረግ ጦርነት” እንደሚሆን አስቦ ነበር። ይሁንና ይህ ሁሉ ስህተት ነበር።
ቀሳውስቱ ጦርነቱን በጋለ ስሜት ደግፈዋል። ዘ ኮለምቢያ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ እንዲህ ይላል፦ “የአምላክ ቃል ባለ አደራዎች የጦርነቱ ዋነኛ አቀንቃኞች ሆኑ። ሁሉም ሰው የዘመተበት ጦርነት በሁሉም ዘንድ ጥላቻ እንዲሰፍን አደረገ።” ቀሳውስት ደግሞ የጥላቻውን ነበልባል በማጥፋት ፈንታ አራገቡት። ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ እንዲህ ይላል፦ “ቀሳውስት ክርስቲያናዊ እምነታቸውን ከብሔራዊ ስሜት ለማስቀደም አልቻሉም፤ አብዛኛውን ጊዜም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበሩም። ብዙዎቹ ቀሳውስት ቀላሉን መንገድ የመረጡ ሲሆን ክርስትና ከአገር ፍቅር ጋር እንደማይነጣጠል ይገልጹ ነበር። ከሁሉም የክርስትና ሃይማኖቶች የተውጣጡ ወታደሮች አንዳቸው ሌላውን በአዳኛቸው ስም እንዲገድሉ ይበረታቱ ነበር።”
የጦር መሪዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ ድል እንደሚቀዳጁ ተስፋ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም እንዳሰቡት አልተሳካም። ብዙ ሳይቆይ ተፋላሚዎቹ ሠራዊቶች ማናቸውም ማሸነፍ በማይችሉበት ፍጥጫ ውስጥ ገቡ። ከዚያ በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወታደሮች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠማቸው፤ ሁኔታው የሰው ልጅ ካጋጠመው አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ሥቃይ ሁሉ የከፋ እንደነበረ አንድ የታሪክ ምሁር ገልጸዋል። የሚያሰቅቅ እልቂት ቢደርስም የጦር መሪዎች፣ ወታደሮቻቸውን ወደ ጦርነቱ መማገዳቸውን አላቆሙም፤ በባለ እሾህ ሽቦ ወደታጠሩ ሠፈሮችና የጥይት እሩምታ ወደሚዘንብበት የተፋፋመ ጦርነት ወታደሮቻቸውን መላካቸውን ቀጠሉ። ከዚህ አንጻር በየቦታው ያሉ ወታደሮች በበላዮቻቸው ላይ ማመፃቸው የሚያስደንቅ አይደለም።
አንደኛው የዓለም ጦርነት በማኅበረሰቡ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? በጦርነቱ ተካፍሎ የነበረ አንድ ሰው “ጦርነቱ የትውልዱን አስተሳሰብና ምግባር አበላሽቷል” ማለቱን አንድ የታሪክ ጽሑፍ ላይ ተጠቅሷል። በእርግጥም በጦርነቱ የተነሳ አንዳንድ አገዛዞች ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል። ያንን አሳዛኝ ጦርነት ተከትሎ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋ ደም መፋሰስ የታየበት ክፍለ ዘመን መጣ። አብዮቶችና ሕዝባዊ ዓመፆች በጣም የተለመዱ ሆኑ።
ያ ጦርነት ዓለምን ያመሰቃቀላት ለምንድን ነው? ጦርነቱ በአጋጣሚ የተከሰተ ትልቅ አደጋ ብቻ ነበር? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚጠቁመው ነገር ይኖር ይሆን?