የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ሞት የሁሉ ነገር ፍጻሜ ነው?
የሰው ዘር ከሞት ጋር የሚያደርገው ትግል
ሞት አስፈሪ ጠላት ነው። ይህን ጠላት ባለ በሌለ ኃይላችን ለመዋጋት ጥረት እናደርጋለን። የምንወደውን ሰው ሲገድልብን ሁኔታውን አምነን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ወይም ደግሞ ብርቱ በሆንበት የወጣትነት ዕድሜ ላይ ይህ ጠላት ፈጽሞ እኛን ሊነካ እንደማይችል አድርገን እናስብ ይሆናል፤ እንዲሁም ማንም ስለሞት እንዲያነሳብን አንፈልግም።
እንደ ጥንቶቹ ፈርዖኖች የሞት ነገር ያስጨነቃቸው ሰዎች የሉም ማለት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን የሕይወት ዘመናቸውን ሞትን ድል ለማድረግ ሲደክሙ የኖሩ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ አገልጋዮቻቸው ጉልበትም ለዚሁ ዓላማ እንዲፈስ አድርገዋል። የገነቧቸው ፒራሚዶችም ያደረጉትን ብርቱ ጥረትና ጥረታቸው መና ሆኖ መቅረቱን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው።
የቻይና ነገሥታት ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ መንገድ የተከተሉ ቢሆንም እነሱም ያለመሞትን ባሕርይ የመላበስ ሕልም ነበራቸው፤ ስለሆነም ለዘላለም መኖር የሚያስችል አስማታዊ ኃይል ያለው መድኃኒት ለማግኘት ሲደክሙ ኖረዋል። ንጉሠ ነገሥት ቺን ሻይ ሁዋንግ፣ መድኃኒት ቀማሚዎቹን ሞትን የሚያስቀር አስማታዊ ኃይል ያለው መድኃኒት እንዲሠሩለት አዝዞ ነበር። ይሁንና የቀመሟቸው ብዙዎቹ ውሕዶች መርዛማ የሆነ ሜርኩሪ የያዙ ሲሆን ንጉሡን ለሞት የዳረገውም ከእነዚህ መድኃኒቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም።
በ16ኛው መቶ ዘመን፣ ሁዋን ፖንሴ ደ ሊዮን የተባለ ስፔናዊ አሳሽ፣ ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የሚባልለትን የውኃ ምንጭ ለመፈለግ ወደ ካሪቢያን ደሴቶች በመርከብ እንደተጓዘ ይነገራል። ይህ ሰው በዚህ ፍለጋው ላይ እያለ በዩናይትድ ስቴትስ የምትገኘውን ፍሎሪዳን ማግኘት ችሏል፤ ይሁንና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከመጀመሪያዎቹ የአሜሪካ ነዋሪዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ሕይወቱ አለፈ። ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የሚባልለት ምንጭም ተገኝቶ አያውቅም።
ፈርዖኖች፣ ነገሥታትና አሳሾች ሞትን ድል የሚያደርግ ነገር ፍለጋ ብዙ ደክመዋል። ይህን ለማድረግ የተጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ባንደግፍም እንኳ ከመካከላችን የተነሱበት ዓላማ ትክክል አይደለም ብሎ ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖራል? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም መሞት አንፈልግም።
ሞት ድል ሊደረግ ይችላል?
ሞትን ይህን ያህል የምንቃወመው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያቱን ይነግረናል። ፈጣሪያችን ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ * ሲናገር “ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ” ይላል። (መክብብ 3:11) ውብ በሆነችው ምድር ላይ 80 ወይም ከዚያ ብዙም ለማይበልጥ ዕድሜ ሳይሆን ለዘላለም መኖር እንፈልጋለን። (መዝሙር 90:10) የልባችን ፍላጎት ይህ ነው።
አምላክ በልባችን ውስጥ “ዘላለማዊነትን” ያኖረው ለምንድን ነው? ይህ ምኞታችን ሳይፈጸም በመቅረቱ የተነሳ ለብስጭት እንድንዳረግ አስቦ ነው? ይህ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም። ከዚህ በተቃራኒ አምላክ ሞት ድል የሚደረግበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሞት ስለሚወገድበት ጊዜና አምላክ ስለሰጠው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ደጋግሞ ይናገራል።— “በሞት ላይ የሚገኝ ድል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናግሯል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) ስለሆነም ከሞት ጋር የሚደረገው ትግል ምንም ተስፋ የሌለው ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ሞትን ድል ሊያደርግልን የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን አበክሮ ገልጿል።
^ አን.9 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።