የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?
በዓለም ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ተወዳጅነት ያተረፈ መጽሐፍ የለም ማለት ይቻላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር፣ በውስጡ ያለው ሐሳብ ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። በታሪክ ውስጥ የኖሩ ሰዎችን እውነተኛ የሕይወት ታሪክ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ከሌሎች ግለሰቦችና ከአምላክ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ያወሳል። እነዚህ ታሪኮች ጠቃሚ ትምህርት ይሰጡናል። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ግልጽ እና ለመረዳት ቀላል በመሆኑ በየትኛውም ዘመን የኖሩ ሰዎች ሊረዱት ችለዋል። ይህ መጽሐፍ፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በማንኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፉን ሊያገኙት ይችላሉ። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጊዜ የሚያልፍባቸው አይደሉም።
ይህን መጽሐፍ ለማወቅ እንድትነሳሳ የሚያደርግህ ከሁሉ የላቀው ምክንያት ደግሞ መጽሐፉ ስለ አምላክ የሚናገር ከመሆኑም ሌላ አምላክ ያስጻፈው መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም፣ ማንነቱን እንዲሁም ምድርንና የሰው ልጆችን የፈጠረበትን ሊለወጥ የማይችል ዓላማ ያብራራል። የክፋት ኃይሎች መልካምን ከሚፈልጉ ወገኖች ጋር ያደረጉትን ለዘመናት የቆየ ትግል ያወሳል፤ ትኩረት የሚስበውና በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉ አካላትን በሙሉ የሚመለከተው ይህ ጉዳይ በመጨረሻ አስደሳች በሆነ መልኩ ይደመደማል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በቅን ልቦና ማንበብ እምነት እንድናዳብርና ተስፋ እንዲኖረን ይረዳናል።
ሌላ የትም ቦታ ልናገኝ የማንችለውን መረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተሉት ስላሉት ጉዳዮች እውነቱን ይነግረናል፦
ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት እንደሆነና መከራ የሚደርስብን ለምን እንደሆነ
አምላክ የሰውን ልጅ ለመታደግ ምን ዝግጅት እንዳደረገ
ኢየሱስ ለእኛ ምን እንዳደረገልን
የምድርና የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ምን እንደሆነ
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው መልእክት ምን እንደሆነ ለማወቅ የሚቀጥሉትን ገጾች ለምን አታነብብም?