ወደ አምላክ ቅረብ
‘ልባችንን ይሞላዋል’
ይሖዋ በእርግጥ ስለ እኛ ያስባል? ወይስ በምድር ላይ ያሉት ሰዎች ለሚደርስባቸው ሥቃይና መከራ ደንታ የለውም? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ የሚያጽናና ነው። አምላክ ለሰው ልጆች እንደሚያስብ እና ደስተኛ ሕይወት እንድንመራ እንደሚፈልግ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ ለሰው ልጆች በሙሉ ሌላው ቀርቶ እሱን ለማያመሰግኑት ሰዎች እንኳ በየቀኑ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ይሰጣቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንዳለ ተመልከት።—የሐዋርያት ሥራ 14:16, 17ን አንብብ።
ጳውሎስ የይሖዋ አምላኪዎች ላልነበሩት የልስጥራ ከተማ ነዋሪዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “[አምላክ] ባለፉት ትውልዶች ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤ ይሁንና መልካም ነገሮች በማድረግ ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት የተትረፈረፈ ምግብ ያቀርብላችኋል፣ ልባችሁንም በደስታ ይሞላዋል።” እነዚህ ቃላት ለጳውሎስ አድማጮች ምን ትርጉም ነበራቸው?
የልስጥራ ሰዎች ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን ለመመልከት ርቀው መሄድ አያስፈልጋቸውም። የሚተዳደሩት በግብርና ሲሆን ምድራቸው ለምና ውኃ በብዛት የሚገኝበት ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንደገለጸው ዝናብንና ፍሬያማ ወቅቶችን የሚሰጣቸው አምላክ ነው። በመሆኑም የተትረፈረፈ ሰብል ማግኘትና ጣፋጭ ምግብ በልተው መደሰት የቻሉት በአምላክ ልግስና ነው።
ጳውሎስ ለልስጥራ ሰዎች የተናገረው ነገር ስለ ይሖዋ አምላክ ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ይሰጠናል።
ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። ይሖዋ ሁሉም ሕዝቦች “በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ” እንደፈቀደላቸው ልብ በል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚናገረው፣ ይህ ሐረግ “ደስ ባላቸው መንገድ እንዲሄዱ” ወይም “የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን እንዲያደርጉ” አምላክ እንደፈቀደላቸው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ፣ አምልኮ እንዲያቀርብለት ማንንም ሰው አያስገድድም። የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ሕይወታችንን የምንመራበትን አቅጣጫ መምረጥ እንችላለን።—ዘዳግም 30:19
ይሖዋ እንድናውቀው ይፈልጋል። ጳውሎስ፣ ስለ አምላክ ሲናገር “ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም” ብሏል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚናገረው፣ ይህ አገላለጽ “ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለሰዎች በግልጽ አሳይቷል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ጥሩነቱን፣ ጥበቡን፣ ኃይሉንና ፍቅሩን ጨምሮ አስደናቂ ስለሆኑት “የማይታዩት ባሕርያቱ” ማንም ሊያስተባብለው የማይችል ምሥክርነት ይሰጣሉ። (ሮም 1:20) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ስለ ራሱ ብዙ ነገር ገልጿል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ታዲያ እንድናውቀው የሚፈልግ መሆኑ ግልጽ አይደለም?
አምላክ ለሰው ልጆች በሙሉ ሌላው ቀርቶ እሱን ለማያመሰግኑት ሰዎች እንኳ በየቀኑ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ይሰጣቸዋል
ይሖዋ ደስ እንዲለን ይፈልጋል። አምላክ ‘የተትረፈረፈ ምግብ እንደሚያቀርብልንና ልባችንን በደስታ እንደሚሞላው’ ጳውሎስ ተናግሯል። ይሖዋን የማያመሰግን ኃጢአተኛ ሰውም እንኳ እስኪጠግብ መብላት እንዲሁም በሕይወቱ ውስጥ በተወሰነ መጠን ደስታ ማግኘት ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ከዚህ ባለፈ እውነተኛና ዘላቂ ደስታ እንድናገኝ ይፈልጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ስለ እሱ እውነቱን ተምረን በሕይወታችን ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው።—መዝሙር 144:15 የ1980 ትርጉም፤ ማቴዎስ 5:3
የይሖዋን ጥሩነት በየዕለቱ እንቀምሳለን። ታዲያ ‘የተትረፈረፈ ምግብ ለሚያቀርብልህና ልብህን በደስታ ለሚሞላው’ አምላክ ያለህን አድናቆት ማሳየት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ አትፈልግም?
በሐምሌ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል