ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንቷ ነነዌ ‘የደም ከተማ’ የተባለችው ለምን ነበር?
ነነዌ የአሦር ግዛት ዋና ከተማ ነበረች። ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ቤተ መንግሥቶችና ቤተ መቅደሶች፣ ሰፋፊ ጎዳናዎች እንዲሁም ግዙፍ የሆኑ ቅጥሮች ያሏት ታላቅ ከተማ ነበረች። ዕብራዊው ነቢይ ናሆም ነነዌን ‘የደም ከተማ’ በማለት ጠርቷታል።—ናሆም 3:1
ለዚህች ከተማ ይህ ስያሜ መሰጠቱ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም በነነዌ በነበረው የሰናክሬም ቤተ መንግሥት ውስጥ የተተከሉ ሐውልቶች አሦራውያን ጨካኝ እንደነበሩ ይመሠክራሉ። አንደኛው ሐውልት፣ አንድ ገራፊ በችንካር ከመሬት ጋር የተጣበቀን እስረኛ ምላስ መንጭቆ ሲያወጣ ያሳያል። በሐውልቶች ላይ የተቀረጹ ጽሑፎች የምርኮኞችን አፍንጫ ወይም ከንፈር በስተው መንጠቆ ካስገቡ በኋላ በገመድ እየጎተቱ ይወስዷቸው እንደነበር በጉራ ይገልጻሉ። የተማረኩ ባለሥልጣናት፣ የነገሥታቶቻቸውን ጭንቅላት እንደ አንገት ጌጥ እንዲያንጠለጥሉ በማድረግ ቀፋፊ ነገር ይፈጸምባቸው ነበር።
የአሦራውያንን ታሪክ የሚያጠኑት አርከቦልድ ሄንሪ ሳስ አንድ ከተማ ከተማረከ በኋላ የሚፈጸመውን አረመኔያዊ ድርጊት እንዲህ በማለት ገልጸዋል፦ “ድል አድራጊው በሚያልፍበት ጎዳና የሰዎች ጭንቅላት እንደ ፒራሚድ ይቆለላል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከነሕይወታቸው በእሳት ይቃጠሉ ወይም ከዚያ የከፋ ዕጣ ይጠብቃቸው ነበር፤ ደግሞም ወንዶች በስቅላት ይቀጡ፣ በቁማቸው ቆዳቸው ይገፈፍ፣ ዓይናቸው ይጠፋ ወይም እጃቸው፣ እግራቸው፣ጆሯቸውና አፍንጫቸው ይቆረጥ ነበር።”
አይሁዳውያን በቤታቸው ጣሪያ ዙሪያ መከታ የሚያደርጉት ለምን ነበር?
አምላክ፣ አይሁዳውያንን እንደሚከተለው በማለት አዟቸው ነበር፦ “አዲስ ቤት በምትሠራበት ጊዜ፣ ከጣራው ላይ ሰው ወድቆ በቤትህ ላይ የደም በደል እንዳታመጣ፣ በጣራው ዙሪያ መከታ አብጅለት።” (ዘዳግም 22:8) ይህ መከታ አስፈላጊ ነበር፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አይሁዳውያን በቤታቸው ጣሪያ ላይ ብዙ ነገር ያከናውኑ ነበር።
የአብዛኞቹ እስራኤላውያን ቤት ጣሪያ ጠፍጣፋ ነበር። ስለዚህ ጣሪያው ፀሐይ ለመሞቅ፣ ለመናፈስ ወይም አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን ተስማሚ ቦታ ነው። በበጋ ወቅት ደግሞ ይህ ቦታ ለመተኛት ያመቻል። (1 ሳሙኤል 9:26) አንድ ገበሬ፣ እህል ከመፈጨቱ በፊት ለማስጣት ወይም በለስ፣ ዘቢብና ተልባ ለማድረቅ የቤቱን ጣሪያ ይጠቀምበታል።—ኢያሱ 2:6
በተጨማሪም ሰዎች የቤታቸውን ጣሪያ ትክክለኛውን አምልኮም ሆነ የጣዖት አምልኮ ለማከናወን ይጠቀሙበት ነበር። (ነህምያ 8:16-18፤ ኤርምያስ 19:13) ሐዋርያው ጴጥሮስ በቀትር ሰዓት ላይ ለመጸለይ ወደ ቤቱ ጣሪያ ወይም ሰገነት ወጥቶ እንደነበር ተገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 10:9-16) የቤቱ ጣሪያ በወይን ተክል ወይም በዘንባባ ቅጠል ጥላ ከተደረገለት ደግሞ ደስ የሚል ማረፊያ ይሆናል።
ዘ ላንድ ኤንድ ዘ ቡክ የተሰኘው መጽሐፍ የእስራኤላውያን ቤቶች “ከመኖሪያ ክፍሉ ውጭ ሆኖም በግቢው ውስጥ” ወደ ጣሪያው የሚወጣባቸው ደረጃዎች ወይም መሰላሎች እንደነበሯቸው ይናገራል። ስለዚህ አንድ ሰው ቤት ውስጥ መግባት ሳያስፈልገው ከጣሪያው ወርዶ መሄድ ይችል ነበር። ይህም ኢየሱስ “በጣሪያ ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለማውጣት አይውረድ” በማለት ጥፋት ከተደቀነባት ከተማ በአስቸኳይ እንዲሸሽ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ግልጽ ያደርግልናል።—ማቴዎስ 24:17