የኢየሱስ ትንሣኤ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል!
የኢየሱስ ትንሣኤ በዛሬው ጊዜ ላለነው ሰዎች ትርጉም የሌለው በጥንት ጊዜ የተፈጸመ አንድ ክስተት ብቻ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት በጻፈ ጊዜ ትንሣኤው ያለውን ጠቀሜታ ገልጿል፦ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል። ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው። ምክንያቱም ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።”—1 ቆሮንቶስ 15:20-22
ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ኒሳን 16 ቀን 33 ዓ.ም. ማለትም አይሁዳውያን በየዓመቱ ከመጀመሪያው የእህል አዝመራቸው ላይ በኩራቱን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አምላክ በሚያቀርቡበት ዕለት ነው። ጳውሎስ ኢየሱስን በኩራት ብሎ መጥራቱ ከሞት የሚነሱ ሌሎች ሰዎችም እንዳሉ ያመለክታል።
ጳውሎስ በመቀጠል የተናገረው ሐሳብም በኢየሱስ ትንሣኤ አማካኝነት የሚፈጸሙ ነገሮችን ይገልጻል። “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው” ብሏል። ከአዳም በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና ምክንያት ሁላችንም እንሞታለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የሰው ዘር በትንሣኤ አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ከፍቷል። ጳውሎስ በሮም 6:23 ላይ እንዲህ በማለት ጉዳዩን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል፦ “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው፤ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።”
ኢየሱስ ራሱ የእሱ ሞትና ትንሣኤ ለእኛ ያለውን ትርጉም ገልጿል። ራሱን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው። አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:14-16
ሥቃይ፣ መከራ ወይም ሐዘን የሌለበት ዘላለማዊ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው! (ራእይ 21:3, 4) እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! አንድ ምሁር ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ገልጸውታል፦ “መቃብሮች የሕይወትን አጭርነት የሚያስታውሱ ቢሆኑም ትንሣኤ ደግሞ ሞት በአጭር እንደሚቀጭ ያረጋግጣል።” አዎን፣ የኢየሱስ ትንሣኤ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል!