በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከቨርዴል እና ለሕትመት የበቃው የመጀመሪያ ሙሉ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ

ከቨርዴል እና ለሕትመት የበቃው የመጀመሪያ ሙሉ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ

ከቨርዴል እና ለሕትመት የበቃው የመጀመሪያ ሙሉ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ

በእንግሊዝኛ የታተመው የመጀመሪያው የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ የተርጓሚውን ስም አይገልጽም። ተርጓሚው ማይልዝ ከቨርዴል ሲሆን ሥራው ታትሞ የወጣውም በ1535 ነበር። መጽሐፉ በወጣበት ወቅት፣ የከቨርዴል ጓደኛ የነበረው ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ከመተርጎም ጋር በተያያዘ ባከናወነው ሥራ ምክንያት ወኅኒ ወርዶ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ቲንደል ተገደለ።

ከቨርዴል ከትርጉሙ ከፊሉን ያከናወነው በቲንደል ሥራ ላይ ተመርኩዞ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች እየታደኑ ሲገደሉ እሱ ከሞት ማምለጥና የትርጉም ሥራውን ማሳተም የቻለው እንዴት ነው? ደግሞስ ምን ቅርስ ትቶ አልፏል?

ዘሩ ተዘራ

ማይልዝ ከቨርዴል በዮርክሺር፣ እንግሊዝ በ1488 እንደተወለደ ይታመናል። ትምህርቱን የተከታተለው በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን በ1514 የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሆኖ ተሾመ። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሐድሶ ለማካሄድ እንዲነሳሳ ያደረገው አስተማሪው የነበረው ሮበርት ባርንዝ ነው። በ1528 ባርንዝ ከእንግሊዝ ሸሽቶ ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ሄደ። ይህ የተሐድሶ አራማጅ ከአሥራ ሁለት ዓመት በኋላ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቆስቋሽነት በእንጨት ላይ ታስሮ እንዲቃጠል ተደረገ።

በ1528 ከቨርዴል እንደ ምስል አምልኮ፣ ኑዛዜ ማቅረብ እና ቁርባን ያሉ መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፋቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ልማዶችን በማውገዝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መስበክ ጀመረ። በዚህም ምክንያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ስለወደቀ እንግሊዝን ለቅቆ ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የሄደ ሲሆን በዚያም ለሰባት ዓመታት ያህል ኖሯል።

ከቨርዴል ሃምቡርግ፣ ጀርመን ውስጥ የኖረው ከዊልያም ቲንደል ጋር ነበር። እነዚህ ሁለት ተርጓሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሰዎች በቀላሉ በሚያነቡት ቋንቋ ለማዘጋጀት የነበራቸውን የጋራ ዓላማ ለማሳካት አብረው ሠርተዋል። በዚህ ወቅት ከቨርዴል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ከቲንደል ብዙ እውቀት ቀስሟል።

ሁኔታዎች ተለወጡ

በዚህ መሃል በእንግሊዝ የነበረው ሁኔታ መለወጥ ጀመረ። በ1534 ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በሮም ያለውን የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሥልጣን እንደማይቀበል በይፋ አሳወቀ። ንጉሡ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለእንግሊዝ ሕዝብ በቋንቋው መተርጎሙንም ይደግፍ ነበር። ከጊዜ በኋላ ከቨርዴል ይህን ሥራ ማከናወን ጀመረ። ከቨርዴል ሐሳቡን በእንግሊዝኛ በመግለጽ ረገድ የላቀ ችሎታ ቢኖረውም ወዳጁና አስተማሪው የሆነውን የቲንደልን ያህል የዕብራይስጥ እና የግሪክ ቋንቋ ችሎታ አልነበረውም፤ ቲንደል እነዚህን ቋንቋዎች አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ከቨርዴል የላቲንና የጀርመንኛ ትርጉሞችን በመጠቀም የቲንደልን ትርጉም አረመው።

የከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስ በ1535 ይኸውም ቲንደል ከመገደሉ ከአንድ ዓመት በፊት ከእንግሊዝ ውጭ ታተመ። ከቨርዴል በትርጉሙ ላይ ንጉሥ ሄንሪን የሚያሞግስ እንዲያውም በተወሰነ መጠን ሽንገላ የሚንጸባረቅበት ሐሳብ አካትቷል። ከዚህም ሌላ ከቨርዴል፣ ቲንደል ያሰፈራቸውን የግርጌ ማስታወሻዎች ከትርጉሙ ላይ እንዳወጣ ለንጉሡ አረጋገጠለት፤ እነዚህን የግርጌ ማስታወሻዎች አወዛጋቢ ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶች የሚያጋልጡ መሆናቸው ነው። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ሄንሪ መጽሐፍ ቅዱሱ እንዲታተም ፈቃድ ሰጠ። በእርግጥም ሁኔታዎች መለወጥ ጀምረው ነበር።

የከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስ በ1537 እንግሊዝ ውስጥ ሁለት ጊዜ እንደገና ታተመ። በዚያው ዓመት፣ የቲንደልንና የከቨርዴልን ሥራዎች አንድ ላይ ያጣመረና የማቴዎስ መጽሐፍ ቅዱስ የተባለ ትርጉም በአንትወርፕ ታተመ፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የንጉሡን ፈቃድ አግኝቶ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ግን፣ የንጉሡ ዋነኛ አማካሪ የሆነው ቶማስ ክሮምዌል የማቴዎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደገና ታርሞ መውጣት እንዳለበት ተገነዘበ፤ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ክራንመር፣ ክሮምዌል እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንዲያድርበት አድርገዋል። በመሆኑም ክሮምዌል፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያርመው ከቨርዴልን እንደገና ጠየቀው። ንጉሥ ሄንሪ፣ ይህ የታረመው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲታተም በ1539 ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ሁሉም ሰው ሊያነበው እንዲችል በየቤተ ክርስቲያኑ የዚህ ትርጉም ቅጂዎች እንዲቀመጡም ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ በመሆኑ ግሬት ባይብል (ትልቁ መጽሐፍ ቅዱስ) ተብሎ ተጠራ። የአገሪቱ ነዋሪዎች በሙሉ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ በደስታ ተቀበሉት።

ከቨርዴል ትቶት ያለፈው ቅርስ

ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ ከሞተና በኤድዋርድ ስድስተኛ ከተተካ በኋላ ከቨርዴል በ1551 የኤክሲተር ጳጳስ ሆኖ ተሾመ። ይሁንና ካቶሊክ የሆነችው ንግሥት ሜሪ በ1553 ንጉሥ ኤድዋርድን ተክታ ሥልጣን ስትጨብጥ ከቨርዴል ወደ ዴንማርክ ሸሽቶ ለመሄድ ተገደደ። ከጊዜ በኋላም ወደ ስዊዘርላንድ በመሄድ ሥራውን ቀጠለ። በተጨማሪም በተለምዶ አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሦስት የእንግሊዝኛ እትሞች ያዘጋጀ ሲሆን በእነዚህ ትርጉሞች ላይ ለቀሳውስቱ የሚጠቅም የማጥኛ ጽሑፍ በላቲን አካትቷል።

የሚያስገርመው ነገር ከቨርዴል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ ላይ “ይሖዋ” የሚለውን መለኮታዊ ስም አውጥቶታል። ቲንደል በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሙ ላይ የአምላክን ስም ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል። ጄምስ ፍሬድሪክ ሞዝሊ የተባሉት ምሁር ከቨርዴል ኤንድ ሂዝ ባይብልስ በተባለው መጽሐፍ ላይ “ከቨርዴል በ1535 [ይሖዋ] የሚለውን ቃል ከነአካቴው አውጥቶታል” ብለዋል። በኋላ ላይ ግን ግሬት ባይብል በተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም የሆነውን ይሖዋ የሚለውን ቃል ሦስት ጊዜ አስገብቶታል።

ይሁንና የከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስ፣ መለኮታዊው ስም የሚጻፍባቸውን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት በመጀመሪያው ገጽ አናት ላይ በማስፈር ቀደምት የሆነ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህም ሌላ የአዋልድ መጻሕፍትን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተሰበጣጥረው እንዲቀመጡ ከማድረግ ይልቅ ለብቻቸው ተጨማሪ ክፍል ውስጥ እንዲካተቱ ያደረገ የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑም ትኩረት የሚስብ ነው።

ከቨርዴል ከተጠቀመባቸው ለየት ያሉ አገላለጾችና ቃላት መካከል ብዙዎቹን ከጊዜ በኋላ ሌሎች ተርጓሚዎችም ተጠቅመውባቸዋል። በ⁠መዝሙር 23 ቁጥር 4 ላይ የሚገኘውን “በሞት ጥላ ሸለቆ” የሚለውን ሐረግ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ፕሮፌሰር ግሪንስሌድ፣ በከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙር 23 ቁጥር 6 ላይ የሚገኘው “ፍቅራዊ ደግነት” የሚለው አገላለጽ “አምላክ ለሕዝቦቹ የሚያሳየውን ፍቅር፣ ለሰው ዘር በአጠቃላይ ከሚያሳየው ፍቅር እና ከምሕረቱ ለመለየት የሚረዳ ልዩ ቃል” እንደሆነ ገልጸዋል። ባለማጣቀሻው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ይህን ቃል የተጠቀመ ሲሆን በግርጌ ማስታወሻው ላይ “ወይም፣ ‘ታማኝ ፍቅር’” የሚል ሐሳብ አስፍሯል።

ግሬት ባይብል የተባለው የከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስ “ቲንደል የአዲስ ኪዳንን ትርጉም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ሲከናወን የቆየው ሥራ የመጨረሻ ውጤት” እንደሆነ ዘ ባይብልስ ኦቭ ኢንግላንድ የተባለው መጽሐፍ ገልጿል። በከቨርዴል ዘመን የነበሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የቻሉት ከቨርዴል መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎሙ ነው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መለኮታዊው ስም የሚጻፍባቸው አራት ፊደላት (በስተግራ)፣ በ1537 ከወጣው እትም የመጀመሪያ ገጽ ላይ የተወሰደ

[ምንጭ]

Photo source: From The Holy Scriptures of the Olde and Newe Testamente With the Apocripha by Myles Coverdale

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From the book Our English Bible: Its Translations and Translators