በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአምላክ ቃል ተማር

ክርስቲያኖች የሚጠመቁት ለምንድን ነው?

ክርስቲያኖች የሚጠመቁት ለምንድን ነው?

ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት መልሶቹን መጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።

1. የክርስቲያኖች ጥምቀት ምን ትርጉም አለው?

ጥምቀት ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንድንችል እሱን የምንጠይቅበት መንገድ ነው። ስለሆነም አንድ ክርስቲያን መጠመቅ ያለበት በሕፃንነቱ ሳይሆን ስለ አምላክ ማወቅ እና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን በሚችልበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 8:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) ኢየሱስ ያዘዛቸውን ነገሮች ስንማርና ተግባራዊ ስናደርግ የእሱ ደቀ መዝሙር እንሆናለን።​—ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።

የኢየሱስ ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ እና ስለ ኢየሱስ በተማሩት ነገር ላይ ተመሥርተው አፋጣኝ እርምጃ ወስደዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዚያ ወቅት ይኖር የነበረ አንድ ሰው የኢየሱስ ሞት ለመዳን በር እንደከፈተ ሲረዳ ወዲያውኑ ደቀ መዝሙር ሆኗል። በዛሬው ጊዜም ቅን ልብ ያላቸው በርካታ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች ለመሆን መርጠዋል።​—የሐዋርያት ሥራ 8:26-31, 35-38ን አንብብ።

2. ኢየሱስ የተጠመቀው ለምንድን ነው?

አጥማቂው ዮሐንስ፣ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በማጥለቅ ሲያጠምቀው ኢየሱስ 30 ዓመቱ ነበር። የኢየሱስ ጥምቀት፣ አምላክ ለእሱ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም እንደወሰነ ያመለክት ነበር። (ዕብራውያን 10:7) ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆንን ይጨምራል። ኢየሱስ በምድር ላይ ለመኖር ከሰማይ ከመውረዱ በፊትም ቢሆን ምንጊዜም አባቱን ይሖዋን ይወድደው እንዲሁም ይታዘዘው ነበር።​—ማርቆስ 1:9-11⁠ን፤ ዮሐንስ 8:29ን እና ዮሐ 17:5ን አንብብ።

3. አንድ ክርስቲያን መጠመቅ ያለበት ለምንድን ነው?

እኛ የሰው ልጆች ኃጢአተኞች ሆነን ስለተወለድን ያለንበት ሁኔታ ከኢየሱስ ይለያል። ያም ሆኖ የኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት እንድንችል መንገድ ከፍቶልናል። (ሮም 5:10, 12፤ 12:1, 2) እንዲያውም የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 6:18) ይሁንና እንዲህ ዓይነት መብት ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ በሕይወታችን ሙሉ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቃል በመግባት በጸሎት አማካኝነት ራሳችንን ለይሖዋ መወሰን ያስፈልገናል። በዚህ መንገድ ራሳችንን ከወሰንን በኋላ ውሳኔያችንን ለሌሎች ለማሳወቅ በሕዝብ ፊት እንጠመቃለን።​—ማቴዎስ 16:24ን እና 1 ጴጥሮስ 4:2ን አንብብ።

4. ለጥምቀት መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አምላክ መቅረብ ከሚፈልግ ከማንኛውም ሰው ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሉ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ለአምላክ ያለህን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለህን እምነት ያጠናክሩልሃል። በተጨማሪም አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህና ጥሩ ልማዶችን እንድታዳብር ይረዱሃል። ፍቅርን፣ እምነትን እና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን ማዳበርህ ይሖዋን ለዘላለም ለማገልገል የገባኸውን ቃል ጠብቀህ እንድትኖር ያስችልሃል።​—ዮሐንስ 17:3ን እና ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለን መጽሐፍ ምዕራፍ 18 ተመልከት።