በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብርሃም—ትሑት ሰው

አብርሃም—ትሑት ሰው

አብርሃም—ትሑት ሰው

አብርሃም ከቀኑ ሐሩር ጥላ ለማግኘት በድንኳኑ ውስጥ አረፍ ብሏል። ወደ ማዶ አሻግሮ ሲመለከት ከርቀት ሦስት እንግዶች ሲመጡ አየ። * ምንም ሳያመነታ እየሮጠ ወደ እንግዶቹ በመሄድ ወደ መኖሪያው ገብተው አረፍ እንዲሉና እንዲስተናገዱ ጋበዛቸው። አብርሃም እንግዶቹን ሲጋብዛቸው ‘ቁራሽ እንጀራ ላምጣላችሁ’ (የ1954 ትርጉም) ቢላቸውም ትኩስ ቂጣ፣ እርጎ፣ ወተት እንዲሁም ለስላሳ ሥጋ ያለው ጥጃ አርዶ በማቅረብ ሰፊ ግብዣ አደረገላቸው። አብርሃም እንዲህ ያለ መስተንግዶ ማድረጉ አስገራሚ የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዳለው ብቻ ሳይሆን በኋላ ላይ እንደምንመለከተው እውነተኛ ትሕትና እንዳለውም ያሳያል።​—ዘፍጥረት 18:1-8

ትሕትና ምንድን ነው? ትሕትና የሚለው ቃል ትዕቢተኛ ወይም እብሪተኛ አለመሆንን ያመለክታል። ትሑት የሆነ ሰው፣ ሌሎች ሰዎች በሆነ መንገድ ከእሱ እንደሚበልጡ ያስባል። (ፊልጵስዩስ 2:3) እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሌሎችን ሐሳብ የሚያዳምጥ ከመሆኑም ሌላ እነሱን ለማገልገል ዝግጁ ነው።

አብርሃም ትሑት እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነው? አብርሃም ሌሎችን በደስታ አገልግሏል። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አብርሃም ሦስቱን እንግዶች በተመለከተ ጊዜ ወዲያውኑ እነሱን ለማስተናገድ ጥረት አድርጓል። ባለቤቱ ሣራም በፍጥነት ምግብ ማዘጋጀቷን ተያያዘችው። በዚህ ወቅት አብርሃም ብዙ ሥራ እንዳከናወነ አስተውለሃል? አብርሃም እንግዶቹን ለመቀበል ሮጦ የወጣ ከመሆኑም ባሻገር ምግብ እንዲበሉ ጋብዟቸዋል፤ በተጨማሪም ወደ መንጋው ሮጦ የሚታረደውን እንስሳ የመረጠው እንዲሁም ምግቡን በእንግዶቹ ፊት ያቀረበው እሱ ነበር። ሥራውን ሁሉ ለአገልጋዮቹ ከመስጠት ይልቅ ትሑት የሆነው ይህ ሰው እንግዶቹን ለማስተናገድ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። ሌሎችን ማገልገል ክብሩን እንደሚነካበት ሆኖ አልተሰማውም።

አብርሃም በሥሩ ያሉ ሰዎች የሰጡትን ሐሳብ ሰምቷል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብርሃምና ሣራ ስላደረጓቸው የሐሳብ ልውውጦች ብዙም አይነግረንም። ያም ቢሆን አብርሃም ሁለት ጊዜ የሣራን ሐሳብ አዳምጦ እርምጃ እንደወሰደ ተዘግቧል። (ዘፍጥረት 16:2፤ 21:8-14) እንዲያውም አንደኛው ዘገባ እንደሚገልጸው ሣራ ያቀረበችው ሐሳብ መጀመሪያ ላይ አብርሃምን ‘እጅግ አስጨንቆት’ ነበር። ይሁን እንጂ የሣራ ሐሳብ የተሻለ እንደሆነ ይሖዋ በነገረው ጊዜ አብርሃም በትሕትና ሐሳቧን ከመቀበሉም ሌላ ተግባራዊ አድርጎታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን? ከልባችን ትሑት ከሆንን ሌሎችን ማገልገል ያስደስተናል። ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ የተቻለንን ያህል መጣር እርካታ ያመጣልናል።

ሌሎች ሰዎች ለሚያቀርቡልን ሐሳብ ምላሽ የምንሰጥበት መንገድም ትሑት መሆናችንን ያሳያል። አንድን ሐሳብ እኛ ስላላመጣነው ብቻ ከመቃወም ይልቅ የሌሎችን አስተያየት ለማዳመጥ ፈቃደኛ በመሆን ጠቢብ እንደሆንን እናሳያለን። (ምሳሌ 15:22) በተለይ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች የሌሎችን አስተያየት ለመስማት ዝግጁ መሆናቸው ጠቃሚ ነው። ጆን የተባለ ተሞክሮ ያለው የበላይ ተመልካች “በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ሰው ሥራውን ጥሩ አድርጎ የሚያከናውነው፣ ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያበረታታ ሁኔታ ከፈጠረ ብቻ እንደሆነ አስተውያለሁ” ብሏል። “በሥራችሁ ያለ ሰው አንድን ሥራ ከእናንተ በተሻለ መንገድ ሊያከናውን እንደሚችል መቀበል ትሕትና ይጠይቃል። ደግሞም ጥሩ ሐሳቦችን የሚያፈልቀው በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ግለሰብ ወይም አንድ ሰው ብቻ ነው ማለት አይቻልም።”

የሌሎችን ሐሳብ በመስማትና እነሱን በማገልገል አብርሃም የምንመስል ከሆነ የይሖዋን ሞገስ እናገኛለን። “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”​—1 ጴጥሮስ 5:5

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 አብርሃም መጀመሪያ ላይ ባያስተውለውም እንግዶቹ የአምላክ መላእክት ነበሩ።​—ዕብራውያን 13:2