ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፆታ ማስተማር ይኖርባቸዋል?
አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .
ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፆታ ማስተማር ይኖርባቸዋል?
▪ ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው በተለያዩ በሽታዎች እንዳይጠቁ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ወላጆች፣ ልጆቻቸው መጥፎ ሥነ ምግባር እንዳይኖራቸውም ተመሳሳይ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ስለ ፆታ ተገቢ የሆነ ትምህርት መስጠት ነው። (ምሳሌ 5:3-23) ልጆች በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔት፣ በመጻሕፍት እንዲሁም የካርቱን ሥዕሎችን በያዙ መጽሔቶች አማካኝነት ለብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ስለሚጋለጡ ወላጆች ሥነ ምግባርን በተመለከተ ተገቢውን ሥልጠና እንዲሁም ትምህርት መስጠታቸው አስፈላጊ ነው።
የትምህርት አሰጣጥ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳያን ሌቪን “ዛሬ ያለው ችግር ልጆቻችን ስለ ፆታ መማራቸው አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ችግሩ ያለው በሚማሩት ነገር፣ ይህን በሚማሩበት ዕድሜና በሚያስተምሯቸው ሰዎች ላይ ነው። ልጆች፣ በንግዱ ዓለም ከተሰማሩ ሰዎች እንዲሁም በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካለው አመለካከት ስለ ፆታ የሚቀስሙት ትምህርት ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም ሌላ ጎጂ ነው።”
ወላጆች ኅብረተሰቡን እየበከሉ ካሉት የተዛቡና መጥፎ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅባቸው አመለካከቶች ልጆቻቸውን መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። (ምሳሌ 5:1፤ ኤፌሶን 6:4) ልጆች የሰውነታቸው ክፍሎች ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ፣ የሰውነታቸውን ንጽሕና እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ እንዲሁም መጥፎ ሥነ ምግባር ካላቸው ሰዎች ራሳቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ ማወቅ አለባቸው። አንዲት ልጅ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ይኸውም ለአቅመ ሔዋን መድረሷን የሚጠቁሙ ምልክቶች የሚታዩበት ጊዜ ላይ ከመድረሷ በፊት በሰውነቷ ውስጥ ስለሚከናወኑት ለውጦች እንዲሁም የወር አበባዋ ለምንና እንዴት እንደሚመጣ በቂ እውቀት ማግኘት አለባት። በተመሳሳይም አንድ ልጅ በእንቅልፍ ላይ ሆኖ ዘሩ ሊፈስ እንደሚችል ወላጆቹ አስቀድመው ሊነግሩት ይገባል። ወላጆች፣ ልጆቻቸው ገና ሕፃናት ሳሉ የሰውነታቸውን ክፍሎች ትክክለኛ መጠሪያ ማስተማር ሊጀምሩ ይችላሉ። አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ስለ እነዚህ የሰውነታቸው ክፍሎች ሦስት ቁልፍ ነገሮችን ያስተምሯቸዋል፦ (1) እነዚህ ክፍሎች ልዩ ናቸው፤ እንዲሁም ማንም ሊያያቸው አይገባም። (2) ስለ እነዚህ የአካል ክፍሎች ጸያፍ የሆነ ወሬ ማውራት ተገቢ አይደለም። (3) ሌሎች ሰዎች ሊነኳቸው ወይም ሊያዩአቸው አይገባም። ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ወላጆች አንዲት ሴት እንዴት እንደምትጸንስ ለልጆቻቸው መቼ እንደሚነግሯቸው ማሰብ ያስፈልጋቸዋል። *
ወላጆች እንዲህ ዓይነቱን ትምህርት መቼ መጀመር ይኖርባቸዋል? ብዙዎች ከሚያስቡት ጊዜ ቀደም ብለው ሊጀምሩ ይገባል። አንዲት ልጅ በ10 ዓመቷ ወይም ከዚያ ቀደም ብላ የወር አበባ ማየት ልትጀምር ትችላለች። እንዲሁም አንድ ልጅ በ11 ወይም በ12 ዓመቱ ሌሊት ተኝቶ እያለ ዘሩ መፍሰስ ሊጀምር ይችላል። ልጆች በሰውነታቸው ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ካላወቁ ሕይወታቸውን የሚቀይሩት እነዚህ ክስተቶች በጣም ሊረብሿቸው ይችላሉ። በመሆኑም እነዚህ ለውጦች፣ እያደጉ ሲሄዱ የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ ነገሮች እንደሆኑ አስቀድሞ ሊነገራቸው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንቦች መከተል ያለውን ጥቅምና አስፈላጊነት ሊነገራቸው የሚገባውም በዚህ ወቅት ነው፤ እንዲህ ያለውን ሥልጠና ከአብዛኛዎቹ የሥነ ፆታ ትምህርት ፕሮግራሞች አያገኙትም።—ምሳሌ 6:27-35
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.5 ወላጆች ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጁት በሚከተሉት ጽሑፎች ላይ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘት ይችላሉ፦ “ሴት ልጃችሁ ስለ ወር አበባ በቅድሚያ አውቃ እንድትዘጋጅ መርዳት” (ግንቦት 2006 ንቁ! ከገጽ 10-13)፣ “በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?” (ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 6) እንዲሁም “ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?—ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ፆታ አውሩ” (ኅዳር 1, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-14)