ለአምላክ ያለብንን ግዴታ መወጣት
ወደ አምላክ ቅረብ
ለአምላክ ያለብንን ግዴታ መወጣት
‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ? ይሖዋ እንዲህ ያለ ጥያቄ መጠየቅ እንድንችል ብቻ ሳይሆን መልሱን የማወቅ ጥልቅ ፍላጎት እንዲኖረንም አድርጎ ፈጥሮናል። ደስ የሚለው ነገር አፍቃሪው አምላካችን የጥያቄውን መልስ ማግኘት የምንችልበትንም መንገድ አመቻችቶልናል። የምንፈልገው መልስ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ንጉሥ ሰለሞን በመክብብ 12:13 ላይ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ እንመልከት።
ሰለሞን ለየት ያለ ሁኔታ የነበረው ሰው ነው። ደስታ ማግኘትና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አፉን ሞልቶ መናገር ይችል ነበር። ሰለሞን አስደናቂ ጥበብ፣ ተዝቆ የማያልቅ ሀብትና የንግሥና ሥልጣን ስለነበረው ሀብትንና ክብርን ጨምሮ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያሳድዷቸውን ሌሎች ነገሮች በራሱ ሕይወት በደንብ መመልከት ችሏል። (መክብብ 2:4-9፤ 4:4) ከዚያም የደረሰበትን መደምደሚያ በመንፈስ መሪነት እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።” እነዚህ ቃላት የላቀ በረከት የሚያስገኘውና ሰዎች ሊደክሙለት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ይገልጻሉ።
“እግዚአብሔርን ፍራ።” አምላክን መፍራት የሚለው ሐሳብ መጀመሪያ ላይ አይዋጥልን ይሆናል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው ፍርሃት ግን ከልብ የሚመነጭ ጤናማ ፍርሃት ነው። ኃይለኛ የሆነውን ጌታውን ላለማስቆጣት የሚፈራ ባሪያ የሚሰማውን ስሜት ሳይሆን አፍቃሪ የሆነውን አባቱን ለማስደሰት ከልቡ የሚፈልግ ልጅ የሚኖረውን ስሜት ያመለክታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ፈሪሃ አምላክ ማለት “የአምላክ ሕዝብ አምላክን ስለሚወደው እንዲሁም ኃይሉንና ታላቅነቱን ስለሚያከብር ለእሱ የሚኖረው የአምልኮና የአድናቆት ስሜት ነው።” እንዲህ ያለው ስሜት፣ አምላክን ስለምንወድደውና እሱም እንደሚወድደን ስለምናውቅ ለፈቃዱ እንድንገዛ ያነሳሳናል። እንዲህ ያለው ጤናማ ፍርሃት እንዲያው ስሜት ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር የሚታይ ነገር ነው። እንዴት?
“ትእዛዛቱንም ጠብቅ።” አምላካዊ ፍርሃት እሱን እንድንታዘዘው ያነሳሳናል። ደግሞም ይሖዋን መታዘዝ ልናደርገው የሚገባ ነገር ነው። አንድ ፋብሪካ ምርቱ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንደሚያውቅ ሁሉ አምላክም ፈጣሪያችን በመሆኑ ሕይወታችንን ልንመራ የምንችልበትን ከሁሉ የተሻለ ጎዳና ያውቃል። በዚያ ላይ ደግሞ ይሖዋ ለእኛ የሚጠቅመንን ነገር ይመኝልናል። ደስተኛ እንድንሆን የሚፈልግ ከመሆኑም ሌላ መመሪያዎቹ እኛን ለመጥቀም ተብለው የተዘጋጁ ናቸው። (ኢሳይያስ 48:17) ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ጉዳይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:3) ታዛዥ መሆናችን ለአምላክ ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ሲሆን ትእዛዛቱ ደግሞ እሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያንጸባርቃሉ።
“ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነው።” ይህ ሐሳብ አምላክን ለመፍራት ብሎም ለመታዘዝ የሚያነሳሳንን ወሳኝ የሆነ ምክንያት ይጠቁመናል። እንዲህ ማድረግ ሁለንተናዊ ተግባራችን ወይም ግዴታችን ነው። ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ ሕይወታችንን እንኳ ያገኘነው ከእሱ ነው። (መዝሙር 36:9) ለአምላክ ታዛዥ መሆንም ይጠበቅብናል። ሕይወታችንን እሱ በሚፈልገው መንገድ ከተጠቀምንበት ግዴታችንን እየተወጣን ነው ማለት ይቻላል።
ታዲያ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? በአጭሩ ሲቀመጥ፦ የተፈጠርነው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ነው። ሕይወትህ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የምትችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ የለም። ስለ ይሖዋ ፈቃድ ይበልጥ ለማወቅና ሕይወትህን ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመምራት ለምን አትሞክርም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ረገድ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።
በኅዳር ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
◼ ምሳሌ 22 እስከ 31፤ መክብብ 1 እስከ 12፤ ማሕልየ መሓልይ 1 እስከ 8