እውነት ሕይወትህን የመለወጥ ኃይል አለው
እውነት ሕይወትህን የመለወጥ ኃይል አለው
ቀደም ባሉት ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ ውሸት መሆናቸው ከተጋለጠው ስለ አምላክ የሚሰጡ ትምህርቶች መካከል አንዱን ሰምተህ ወይም ተምረህ ይሆናል። ያም ሆኖ የምታምንባቸውን ትምህርቶች ለመለወጥ ታቅማማ ይሆናል፤ በተለይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ስታምንባቸው የቆዩ ከሆኑ እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊፈጠርብህ ይችላል።
እንድታቅማማ ያደረገህን ምክንያት መረዳት ከባድ አይደለም። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመኖቻቸው የሚያምኑባቸውን ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲያስተያዩ አያበረታቱም። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስብስብ እንደሆነና ሁሉም ሰው ሊረዳው በሚችል መንገድ እንዳልተጻፈ በመግለጽ ውሸቱን ለመሸፋፈን ይጥራሉ። አብዛኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብዙ ያልተማሩ ተራ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም ያስተማራቸውን ትምህርት በቀላሉ መረዳት ችለው ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 4:13
በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖትህን ከመመርመር ወደኋላ የምትለው እንዲህ ማድረግ እምነት የማጣት ምልክት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ስለሚያድርብህ ይሆናል። ይሁንና አምላክ ከአንተ የሚፈልገውን ነገር ለማወቅ ለሰው ዘር ያስጻፈውን መልእክት ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን መመርመርህ አያስደስተውም የሚለው ሐሳብ ምክንያታዊ ይመስልሃል? ከዚህ በተቃራኒ ቃሉ “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]” ስለሚል ቅዱሳን መጻሕፍትን በግለሰብ ደረጃ እንድትመረምር ያበረታታሃል።—ሮም 12:2
ስለ አምላክ የሚናገረውን እውነት መማር አእምሮ ለማስፋት ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም፤ የምታገኘው እውቀት በሕይወትህ ውስጥ በጎ ለውጥ እንድታደርግ ያስችልሃል። (ዮሐንስ 8:32) በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ዲያን በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ቃል ላይ እምነት ማሳደር ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ቅዱሳን መጻሕፍት ይህን ያህል ግልጽ መሆናቸውን ፈጽሞ አልተገነዘብኩም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን የምመለከተው ለእኔ ምንም ግድ እንደሌለው አምላክ አድርጌ ሳይሆን በሰማይ የሚኖር አፍቃሪ አባቴ እንደሆነ አድርጌ ነው። ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆኖልኛል።”
ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠናም ያገኘኸው አንዳች ጥቅም እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል። አምላክን በተመለከተ የተማርካቸውን ውሸቶች ከአእምሮህ ሳታወጣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሞከር የተሳሳተ ምስል እያዩ አንድን የምስል ቁርጥራጮች በመገጣጠም ትክክለኛውን ምስል ለማምጣት የመሞከር ያህል ነው። የተወሰኑትን ቁርጥራጮች በትክክል መገጣጠም ትችል ይሆናል፤ ሆኖም የገጣጠምካቸው ቁርጥራጮች ከተሰጠህ ምስል ጋር እንደማይመሳሰሉ ስታውቅ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። መጀመሪያ ትክክለኛውን ምስል ካገኘህ ግን ቁርጥራጮቹን በትክክል መገጣጠም አያቅትህም።
ስለ አምላክ እውነቱን መማር ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ማጥናት የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበህ እንድታነጋግር አሊያም በዚህ መጽሔት ገጽ 4 ላይ ካሉት አድራሻዎች ለአንተ አመቺ ወደሆነው እንድትጽፍ እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]።”
—ሮም 12:2