አሁንም ሆነ ለዘላለም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት
አሁንም ሆነ ለዘላለም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት
በአሁኑ ጊዜም እንኳ እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ። እንዴት? የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያዘሉ መመሪያዎች በመከተል ነው። እስቲ ከእነዚህ መመሪያዎች ውስጥ ጥቂቶቹን እንመርምር።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ንጉሥ ሰሎሞን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም” በማለት ጽፏል።—መክብብ 2:24
የተፈጠርነው ጠቃሚ ሥራ በማከናወን እርካታ ማግኘት እንድንችል ተደርገን ነው። በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ በትጋትና በሐቀኝነት በመሥራት በአሁኑ ጊዜ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ትችላለህ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ብዙ ሰዎች ለሌሎች መልካም ነገር ማድረግ ማለትም በችግር ጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ ጊዜንና ጉልበትን መስጠት እንደሚክስ እንዲሁም እውነተኛ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመምራት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተገንዝበዋል። ሰለሞን “ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 3:27
እስቲ የራልፍን ሁኔታ እንመልከት። ራልፍ ጡረታ ከወጡ በኋላ እሳቸውም እንደ ባለቤታቸው በክርስቲያናዊው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ በመግባት ማገልገል ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች በማስተማሩ ሥራ ለመካፈል ሲሉ እያንዳንዳቸው በወር ውስጥ ብዙ ሰዓት ያሳልፉ ነበር።
ራልፍ “አመሻሹ ላይ ቤታችን ስንገባ ይደክመናል፤ ሆኖም የሚደክመን ዕድሜያችን በመግፋቱ ብቻ ሳይሆን ጉልበታችንን ሁሉ የሰማዩን አባታችንን ለማገልገል በማዋላችን ነው” ብለዋል። አክለውም “ሆኖም ለመልካም ሥራ መድከም የሚያስደስት ነው!” ብለዋል። እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው በመስጠት ላይ ያተኮረ ሕይወት ስለሚመሩ ደስተኞች ናቸው።የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።”—ምሳሌ 17:17
ችግራችንን ለሌሎች ማካፈል ሸክሙ ይበልጥ እንዲቀልልን ሊያደርግ ይችላል። መጣጥፍ አዘጋጅ የሆኑት እንግሊዛዊው ፍራንሲስ ቤከን እውነተኛ ወዳጆች ለሌላቸው ሰዎች “ዓለም ጭው ያለች ምድረ በዳ ናት” በማለት ጽፈዋል። እውነተኛ ወዳጆች ማግኘትህና አንተም ጥሩ ወዳጅ መሆንህ የሕይወት ሸክም እንዲቀልልህ ብሎም ሕይወት አስደሳችና አርኪ እንዲሆንልህ ሊያደርግ ይችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3
ኢየሱስ፣ የአምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት የምትፈልግ ከሆነ ልታሟላው የሚገባውን በጣም ወሳኝ የሆነ መሥፈርት ማለትም መንፈሳዊ ፍላጎትህን ማርካት እንዳለብህ ገልጿል። እኛ ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ የሕይወትን ትርጉምና ዓላማ የመረዳት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን። ይህን ፍላጎታችንን ሊያረካልን የሚችለው ደግሞ ይሖዋ አምላክ ብቻ ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ነው። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ እዚህ ምድር ላይ የምንኖረውና ይህን ያህል ብዙ መከራ ሊኖር የቻለው ለምን እንደሆነ እንዲሁም አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ይነግረናል። እንዲህ ዓይነቶቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች መረዳት ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት ለመምራት ወሳኝ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጊዜ የሚመድቡና የተማሩትን ነገር በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋቸው ‘ደስተኛ በሆነው አምላክ’ ማለትም በፈጣሪያችን በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በመጣል ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ያስችላቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የችግር ጊዜ ሳይመጣ፣ ‘ምንም ዓላማ የላቸውም’ የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣ . . . ፈጣሪህን አስብ።”—መክብብ 12:1 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
ንጉሥ ሰለሞን፣ በወጣትነት ዕድሜያቸው ወቅት ወደፊት ሕይወት ሊያመጣብን የሚችለውን አሳዛኝ መከራ ማስተዋል ላልቻሉ ወጣቶች የሰጠው ይህ ምክር ለሁላችንም ጠቃሚ ነው። በፈጣሪ ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ጥረት አድርግ። ሕይወትህ እውነተኛ ዓላማ እንዲኖረው የሚያደርገው ይህ ነው። “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚለውን አስተሳሰብ አስወግድ። (1 ቆሮንቶስ 15:32) መክብብ 8:12 እንደሚናገረው በሕይወትህ አምላክን የምታስቀድም ከሆነ ነገሮች ‘መልካም ይሆኑልሃል።’
ዌንዲ የተባለች አንዲት ወጣት ይህ እውነት መሆኑን ተረድታለች። ወጣት በነበረችበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች የሚሰብኩ ሰዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት የዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሄዳ ለመስበክ ስትል ከእህቷ ጋር ስፓንኛ ተምራ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደን ለመስበክ ብዙ መሥዋዕቶችን ከፍለናል፤ ይሁን እንጂ በሕይወታችን ሁሉ እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ አሳልፈን አናውቅም። እነዚያን ስድስት ወራት በምንም ነገር ልለውጣቸው አልችልም! የከፈልነው መሥዋዕት ካገኘነው በረከት ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።”
ለአምላክ ታማኝ መሆን ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል
ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ሕይወትህ በጣም ልዩ በሆነ መንገድ ትርጉም እንዲኖረው አስተዋጽዖ ሊያደርግ ይችላል። እንዴት? ሰይጣን አዳምና ሔዋን በአምላክ አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ በማድረግ ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ማንም ሰው ፈተና ቢደርስበት ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ጠብቆ እንደማይኖር በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጿል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) አንተም ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ! እንዴት? ለአምላክ ያለህን ታማኝነት ጠብቀህ በመኖር፣ መመሪያዎቹን በጥብቅ በመታዘዝ እንዲሁም ለእኛ ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር የመወሰን ብቸኛ መብት ያለው ይሖዋ መሆኑን እንደምትገነዘብ በማሳየት ነው።—ራእይ 4:11
ትክክለኛውን መንገድ መከተል የምንፈልግ ከሆነ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ሊያስፈልገን ይችላል። ታዲያ እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ትርጉም ያለው ሕይወት እንዳንመራ እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ? አንድ ተንኮለኛ ጠላት የምንወደውን ጓደኛችንን ወይም የቤተሰባችንን አባል ስም እያጎደፈ ነው እንበል። ለምንወደው ሰው ጥብቅና በመቆማችን ጠላት አንዳንድ መከራዎችን ቢያደርስብን ይህ ሁኔታ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዳንመራ ሊያደርገን ይችላል? በጭራሽ! የምንወደው ሰው ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ስንል የሚደርስብንን መከራ ሁሉ በደስታ እንቋቋማለን። ለአምላክ ያለንን ታማኝነት በመጠበቅ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ ክፉ ነገሮች እየደረሱብንም እንኳ ታማኝነታችንን መጠበቃችን የአምላክን ልብ ደስ ያሰኛል።—ምሳሌ 27:11
ለዘላለም ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት
እንግዲያው ስለ አምላክና ስለ ዓላማው የቻልከውን ያህል የመማር ግብ ይኑርህ። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) አምላክ ለምድር ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ በሚፈጽምበት ጊዜ ሰዎች ይሖዋ በመጀመሪያ አስቦላቸው የነበረውን ዓይነት ሕይወት ማለትም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ “የዘላለም ሕይወት” ያገኛሉ። በዚያን ጊዜ ሕይወት በእርግጥም ትርጉም ያለውና አርኪ ይሆናል።—መዝሙር 145:16
ታዲያ ኢየሱስ የተናገረውን ዓይነት እውቀት ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? አምላክ በመንፈሱ ካስጻፈው ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህን እውቀት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ። እነሱም ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መማር እንድትችል አንድ ሰው እንዲረዳህ ዝግጅት ያደርጉልሃል።