ተስፋችን መቅረቡን የሚያመለክቱ ችግሮች
ተስፋችን መቅረቡን የሚያመለክቱ ችግሮች
“በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን [ይመጣል]።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1
ከሚከተሉት አሳዛኝ ክስተቶች ውስጥ ቢያንስ ስለ አንዱ ሰምተህ አሊያም በገዛ ዓይንህ ተመልክተህ ታውቃለህ?
● አንድ ቀሳፊ በሽታ የብዙዎችን ሕይወት ቀጠፈ።
● በአንድ ቦታ የተከሰተ ረሃብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳረገ።
● በአንድ አገር የደረሰ የመሬት ነውጥ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድል ብዙዎችን ቤት አልባ አደረገ።
ስለ ዓለም ሁኔታ ቆም ብለህ እንድታስብ የሚያደርጉህ እነዚህን ስለመሰሉ ክስተቶች የሚናገሩ አንዳንድ እውነታዎች በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ቀርበውልሃል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እነዚህ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ትንቢት እንደተናገረ ትመለከታለህ። *
የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ዓላማ በችግር በተሞላ ዓለም ውስጥ እንደምንኖር አንተን ማሳመን አይደለም። ችግሮቹን በገዛ ዓይንህ አይተህ ሊሆን ስለሚችል ይህን ለአንተ መንገር ለቀባሪው አረዱት ማለት ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ርዕሶቹ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖርህ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ከመሆኑም ሌላ ስድስቱ ትንቢቶች ፍጻሜ ማግኘታቸው “መጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚደመደሙበት ጊዜ መቅረቡን የሚያመለክት እንደሆነ ያሳያሉ። በተጨማሪም በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩ አንዳንድ የተቃውሞ ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ሲሆን በቅርቡ የተሻለ ነገር የሚመጣ መሆኑን እንድናምን የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያትም ይሰጡናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 አምላክ እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች እንዲከሰቱ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በዚህ እትም ከገጽ 16-17 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።