ወደ አምላክ ቅረብ
“የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ”
የሚወዱት ሰው ተሠቃይቶ ሲሞት መመልከት ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ያስከትላል። ሰው ሲሞትብን በጥልቅ ማዘናችን እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ የሚሰማንን ጥልቅ ሐዘን እንደሚረዳ ማወቃችን ያጽናናናል። ከዚህም በላይ ታላቅ ኃይሉን በመጠቀም የሞቱትን ለማስነሳት ይጓጓል። በኢዮብ 14:13-15 ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ኢዮብ የተናገረው ሐሳብ የያዘውን ተስፋ ልብ በል።
እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ጠንካራ እምነት የነበረው ኢዮብ ቁሳዊ ንብረቱን ያጣና የሚወዳቸውን ልጆቹን በሙሉ በሞት የተነጠቀ ሲሆን በአሰቃቂ በሽታም ተሠቃይቷል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከባድ መከራዎችም ደርሰውበታል። ይህ ነው በማይባል መከራ ውስጥ ተዘፍቆ ሳለ “በሲኦል [የሰው ልጆች የጋራ መቃብር] ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ!” በማለት ወደ አምላክ ጮዃል። (ቁጥር 13 የ1954 ትርጉም) ኢዮብ ሲኦልን ከሥቃይ እፎይታ እንደሚገኝበት ቦታ አድርጎ ተመልክቶታል። በዚያ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎችና ከሥቃይ ስለሚገላገል ልክ አምላክ እንደሸሸገው ውድ ሀብት ይሆናል። *
ታዲያ ኢዮብ ለዘላለም በሲኦል ይኖራል ማለት ነው? ኢዮብ እንዲህ የሚል እምነት አልነበረውም። ጸሎቱን ሲቀጥል “ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣ ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ!” ብሏል። ኢዮብ በሲኦል የሚቆየው ለጊዜው እንደሆነና ይሖዋም እንደማይረሳው ጠንካራ ተስፋ ነበረው። ኢዮብ ሳይወድ በግድ በሲኦል የሚቆይበትን ይህን ዘመን “ከግዳጅ አገልግሎት” ጋር አመሳስሎታል። ታዲያ በሲኦል የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ኢዮብ “እፎይታ የማገኝበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 14 NW) እፎይታ ማግኘት ከሲኦል መውጣትን በሌላ አባባል ከሞት መነሳትን ያመለክታል።
ኢዮብ እፎይታ የሚያገኝበት ዘመን እንደሚመጣ እርግጠኛ የነበረው ለምንድን ነው? አፍቃሪው ፈጣሪያችን በሞት ስላንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹ ምን እንደሚሰማው በሚገባ ያውቅ ስለነበር ነው። ኢዮብ “ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 15) ኢዮብ የአምላክ የእጅ ሥራ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ኢዮብን እንዲጸነስና እንዲወለድ ያደረገው ሕይወት ሰጪ አምላክ ኢዮብ ከሞተም በኋላ ሊያስነሳው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢዮብ 10:8, 9፤ 31:15
ኢዮብ የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ ያስተምሩናል፦ ይሖዋ በእሱ ዘንድ ተፈላጊ የሆኑ ሰዎች ተደርገው እንዲቀረጹ በእጁ ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ልዩ ዝምድና ይመሠርታል። (ኢሳይያስ 64:8) ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን እንደ ውድ ሀብት አድርጎ ይመለከታቸዋል። በሞት ያንቀላፉ ታማኝ አገልጋዮቹን ‘ይናፍቃቸዋል።’ አንድ ምሑር እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “የመናፈቅን ከፍተኛ ደረጃ ለመግለጽ ከሚያገለግሉት ቃላት መካከል አንዱ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም” ብለዋል። አዎን፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚያስታውስ ከመሆኑም በላይ እነሱን ከሞት ለማስነሳትም ከፍተኛ ጉጉት አለው።
መጀመሪያ ላይ ከተጻፉት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አንዱ በሆነው በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ያለውን ዓላማ በመግለጹ አመስጋኝ ልንሆን ይገባል። * አምላክ በሞት ከተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ጋር እንድትገናኝ ፍላጎት አለው። ይህ ተስፋ ከሐዘንህ እንድትጽናና ሊረዳህ ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነው አምላክ ለመማርና ዓላማው ፍጻሜውን ሲያገኝ ለማየት የምትበቃ ሰው አድርጎ እንዲቀርጽህ ምን ማድረግ እንደምትችል ለማወቅ የበለጠ ጥረት እንድታደርግ እናበረታታሃለን።
^ አን.4 አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ‘ሰውረኝ’ የሚለው ቃል “እንደ ውድ ንብረት በአስተማማኝ ቦታ አስቀምጠኝ” የሚል ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ይናገራል። ሌላ ምንጭ ደግሞ ይህ ቃል “እንደ አንድ ውድ ሀብት ደብቀኝ” የሚል ሐሳብ እንደሚያስተላልፍ ተናግሯል።
^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚከናወነውን ትንሣኤ አስመልክቶ ስለሚናገረው ተስፋ የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ተመልከት።