በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ቁማርን ያወግዛል?

መጽሐፍ ቅዱስ ቁማርን ያወግዛል?

መጽሐፍ ቅዱስ ቁማርን ያወግዛል?

የብዙዎችን አድናቆት ያተረፉ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ቁማርን በተለይም በካዚኖ ቤቶች የሚደረጉ የቁማር ጨዋታዎችን የቆነጃጅት፣ የሀብታሞችና የሠለጠኑ ሰዎች ጊዜ ማሳለፊያ እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ። እርግጥ ነው፣ ተመልካቾች በአብዛኛው በትዕይንቱ ላይ የሚደረጉት ነገሮች ልብ ወለድ እንጂ እውነት እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ።

በእውኑ ዓለም ግን የሎተሪ ቲኬቶች፣ የስፖርት ውርርዶች እና በኢንተርኔት አማካይነት የሚከናወኑ የቁማር ጨዋታዎች ከካዚኖ ቤቶች በማይተናነስ የቁማርተኞችን ትኩረት ስበዋል። ኢንተርኔት ጋምብሊንግ የተባለው መጽሐፍ “ተወዳጅነቱ እንደ ሰደድ እሳት በመስፋፋት ላይ የሚገኝ አገርና ድንበር የማይገድበው ሱስ ሆኗል” ይላል። ለምሳሌ ፖከር የሚባለው የካርታ ጨዋታ በአሁኑ ጊዜ በቴሌቪዥንና በኢንተርኔት የሚቀርብ ዋነኛ ስፖርት ሆኗል። አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው በዩናይትድ ስቴትስ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ የፖከር ተጫዋቾች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል።

ቁማር እርግጠኛ ባልሆነ ውጤት ላይ ገንዘብ ማስያዝ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ብዙ ሰዎች ገንዘቡ የቁማርተኛው እስከሆነና ግለሰቡ ሱስ እስካልያዘው ድረስ ቁማር መጫወት ምንም ክፋት የለውም ብለው ያስባሉ። እንዲያውም ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ ቁማር “አንድ ሰው ሥራውን እንዳያከናውን እንቅፋት እስካልሆነበት ድረስ እንደ ኃጢአት አይቆጠርም” ይላል። ይሁን እንጂ ይህን አመለካከት የሚደግፍ አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አልተጠቀሰም። ታዲያ አንድ ክርስቲያን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምን አመለካከት ሊኖረው ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ቁማርን ይደግፋል ወይስ ያወግዛል?

ቅዱሳን መጻሕፍት ቁማርን በቀጥታ እንደማይጠቅሱ ልብ ማለት ይገባል። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰጠ ምንም ዓይነት መመሪያ የለም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እያንዳንዱ ሁኔታ ወይም እንቅስቃሴ ሕግ ከመስጠት ይልቅ “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ” ይላል። (ኤፌሶን 5:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ኢተልበርት ቡሊንገር እንደሚሉት ‘ማስተዋል’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አእምሮን አሠርቶ፣ አሰላስሎና አገናዝቦ በሚገኝ እውቀት” አማካኝነት የአንድን ጉዳይ የተለያዩ ገጽታዎች አንድ ላይ ማሰባሰብን ያመለክታል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከቁማር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በማሰባሰብና በእነዚያ ላይ በማሰላሰል በጉዳዩ ላይ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል ይችላል። ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ጥቅሶች በምታነብበት ጊዜ ‘ቁማር ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ይስማማል? አምላክ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ስላለው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

ዕድል ወጥመድ ይሆናል

ቁማር ባልተረጋገጠ ነገር ላይ መወራረድን ስለሚጠይቅ በተለይ ሰዎች የሚወራረዱት በገንዘብ ከሆነ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ዕድል ማለትም በአጋጣሚ የሚፈጸሙ ነገሮችን እንደሚቆጣጠር የሚታሰበው ሚስጥራዊ ኃይል ነው። ለምሳሌ ሰዎች የሎተሪ ቲኬት ሲገዙ ገዳም ናቸው የሚባሉ ቁጥሮችን ይመርጣሉ። ማዦንግ የሚባለውን ጨዋታ የሚጫወቱ ሰዎች እንዲቀናቸው አንዳንድ ቃሎችን ከአፋቸው ላለማውጣት ይጠነቀቃሉ፤ እንዲሁም ጠጠር በሚጣልበት ጊዜ ትንፋሽ እፍ ይባልበታል። ለምን? በአብዛኛው ቁማርተኞቹ ዕድል በውጤቱ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ስለሚያምኑ ነው፤ ይህ ባይሆን እንኳ በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይሰማቸዋል።

በዕድል መተማመን ምንም ጉዳት የሌለው ተራ ጨዋታ ነው? በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ተሰምቷቸው ነበር። ዕድላቸው ብልጽግና እንደሚያስገኝላቸው አምነው ነበር። ታዲያ ይሖዋ አምላክ ስለ ጉዳዩ ምን ተሰማው? አምላክ በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግን ይሖዋን ትታችኋል፣ ቅዱስ ተራራዬን ረስታችኋል፣ መልካም ዕድል ለተባለ አምላክ ማዕድ አሰናድታችኋል፣ ዕጣ ለተባለ አምላክም የተደባለቀ ወይን ጠጅ በዋንጫ ሞልታችኋል።” (ኢሳይያስ 65:11 NW) አምላክ በዕድል ማመንን እንደ ጣዖት አምልኮ የሚመለከተው ሲሆን ይህ ዓይነቱ እምነት ከእውነተኛው አምልኮ ጋር አይስማማም። አንድ ሰው በዕድል ማመኑ ከእውነተኛው አምላክ ይልቅ ሐሳብ በወለደው ኃይል እንደሚተማመን ያሳያል። አምላክ ይህን አመለካከቱን ለውጧል ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምንም ምክንያት የለም።

ሽልማቱ የሚገኝበት መንገድ

የቁማር ጨዋታው ዓይነት በኢንተርኔት አማካኝነት መወራረድም ይሁን የሎተሪ ቲኬት መግዛት አሊያም የስፖርት ውርርድ ወይም በካዚኖ ቤቶች ቁማር መጫወት ቁማርተኞች ሊያገኙት የሚጓጉለት ሽልማት ምንጩ ምን እንደሆነ ብዙ ጊዜ አያስቡም። ቁማርተኛው ማግኘት የሚፈልገው ሌሎች የከሰሩትን ገንዘብ መሆኑ ቁማርን ከሌሎች ሕጋዊ ግብይቶች ወይም ግዥዎች የተለየ ያደርገዋል። * በካናዳ የሚገኝ የሱስ ማገገሚያና የአእምሮ ጤና ማዕከል “ሎተሪ አሸንፎ ሚሊዮነር ከሆነ ከእያንዳንዱ ሰው በስተጀርባ ገንዘባቸውን የከሰሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች አሉ!” ብሏል። አንድን ክርስቲያን አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት እንዳለው ለመረዳት የሚያስችሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

ለእስራኤል ሕዝብ ከተሰጡ አሥር ትእዛዛት የመጨረሻው “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የእርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የእርሱ የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” ይላል። (ዘፀአት 20:17) የአንድን ሰው ነገር ማለትም ንብረት፣ ሀብትና ገንዘብ መመኘት ሚስቱን ከመመኘት የማይተናነስ ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ተገልጿል። ሐዋርያው ጳውሎስም ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ “አትጎምጅ” የሚለውን ይህን ትእዛዝ ለክርስቲያኖች ጠቅሷል። (ሮም 7:7) ታዲያ በሌላው ኪሳራ ትርፍ ማግኘት የሚፈልግ ክርስቲያን ጎምጅቷል ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል?

ፊሊፕ ቮግል የተባሉ የአንድ መጽሔት አምድ አዘጋጅ እንዲህ ብለዋል፦ “አብዛኞቹ ቁማርተኞች ተቀበሉትም አልተቀበሉት፣ ድርጊቱን ከመጀመራቸው በፊት ያስያዙት ዶላር ጥቂት ቢሆንም እንኳ ብዙ ገንዘብ እንዲያስገኝላቸው በልባቸው መመኘታቸው አይቀርም።” እንደነዚህ ያሉት ቁማርተኞች በአቋራጭ ብዙ ሀብት ለማጋበስ ያልማሉ። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ክርስቲያን “ለተቸገረ ሰው ሊሰጥ የሚችለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት [እንዲሠራ]” ከሚሰጠው ምክር ጋር እንደሚቃረን ግልጽ ነው። (ኤፌሶን 4:28) ሐዋርያው ጳውሎስ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ሲያደርግ “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ሥራቸውን በመሥራት በድካማቸው ያገኙትን [ይብሉ]” ብሏል። (2 ተሰሎንቄ 3:10, 12) ታዲያ ቁማር እንደ ሥራ ሊቆጠር አይችልም?

ቁማር ከፍተኛ ትኩረት ሊጠይቅ የሚችል ጨዋታ ቢሆንም በቁማር የተገኘ ማንኛውም ገንዘብ በማሸነፍ እንጂ ሥራ በመሥራት ወይም አገልግሎት በመስጠት የተገኘ ክፍያ አይደለም። በቁማር ጨዋታ ወቅት ሰዎች ገንዘብ የሚያስይዙ ሲሆን በአብዛኛው ውጤቱ የተመካው በአጋጣሚ ላይ እንዲሁም ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ይሳካልኝ ይሆናል በሚል ተስፋ ላይ ነው። በአጭሩ አንድ ቁማርተኛ ምንም ሳይለፋ ማግኘት ይፈልጋል። በሌላ በኩል ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች በሐቅ ላይ የተመሠረተ ሥራ በመሥራት የልፋታቸውን እንዲያገኙ ተመክረዋል። ጠቢቡ ሰለሞን “ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም። ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደሚሰጥ አየሁ” ብሏል። (መክብብ 2:24) አዎ፣ የአምላክ አገልጋዮች ደስታና በረከት ለማግኘት አምላክን ተስፋ ያደርጋሉ እንጂ ተስፋቸውን በቅዠት ላይ አያደርጉም፤ ወይም ሌላ አቋራጭ መንገድ አይፈልጉም።

ልንርቀው የሚገባ “ወጥመድ”

አንድ ተጫዋች ቢያሸንፍ እንኳን ለጊዜው የሚያገኘውን ደስታ ሳይሆን ቁማር የሚያስከትልበትን የረጅም ጊዜ ውጤት መመልከት ይኖርበታል። ምሳሌ 20:21 “ከጅምሩ ወዲያው [“በስግብግብነት፣” NW] የተገኘ ርስት፣ በመጨረሻ በረከት አይኖረውም” ይላል። በርካታ የሎተሪ አሸናፊዎችም ሆኑ ሌሎች ቁማርተኞች ያሸነፉት ገንዘብ ደስታ እንዳላመጣላቸው በምሬትና በጸጸት ይናገራሉ። ክርስቲያኖች “ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን ለእኛ ደስታ ሲል ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን አምላክ ላይ” እንዲጥሉ የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መታዘዛቸው ምንኛ የተሻለ ይሆናል!—1 ጢሞቴዎስ 6:17

ቁማር መጫወት ማሸነፍም ሆነ መሸነፍ ከሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ሌላ አደገኛ ገጽታ አለው። የአምላክ ቃል “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም ሰዎችን ጥፋትና ብልሽት ውስጥ በሚዘፍቁ ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ” ይላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) ወጥመድ የሚጠመደውን እንስሳ ጠላልፎ እንዲይዝ ተደርጎ ይሠራል። ትንሽ ገንዘብ ብቻ ለማስያዝ ወይም ጥቂት ጊዜ ብቻ ቁማር ለመሞከር ያሰቡ ሰዎች ተጠላልፈው ራሳቸውን ከቁማር ሱስ ማላቀቅ አቅቷቸዋል። የቁማር ሱስ ብዙዎችን ከሥራቸው አፈናቅሏል፣ የትዳር ጓደኞቻቸውን እንዲያሳዝኑ አድርጓል እንዲሁም ቤተሰቦችን አፈራርሷል።

ከቁማር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን እነዚህን በርካታ ጥቅሶች ከተመለከትክ በኋላ አምላክ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አመለካከት እንዳለው አስተዋልክ? ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ” ሲል መክሯል። (ሮም 12:2) አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን መምራት የሚገባው በብዙኃኑ አስተሳሰብ ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደመሆኑ መጠን የቁማር ወጥመድ ከሚያስከትለው መራራ ፍሬ ነፃ የሆነ አስደሳች ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 1:11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው የጥቅምት 8, 2000 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ከገጽ 25 እስከ 27 ላይ በአክስዮን ገበያ ገንዘብን ኢንቨስት ማድረግ ከቁማር የተለየ የሆነው እንዴት እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጣል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ አገልጋዮች በሐቅ ላይ የተመሠረተ ሥራ በመሥራት የልፋታቸውን ያገኛሉ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ማሸነፍ የሚፈጥረው የደስታ ስሜት

ቁማር ሱስ ሊሆን የሚችል ነገር ነው? ዶክተር ሃንስ ብራይተር ቁማርተኞች ሲያሸንፉና ሲሸነፉ የሚሰማቸውን ስሜት በተመለከተ ጥናት ካደረጉ በኋላ “ለሙከራ በተደረገ ቁማር በሚመስል ጨዋታ ላይ የተገኘ የገንዘብ ሽልማት በሰዎች ላይ የፈጠረው ስሜት የኮኬይን ሱሰኛ ኮኬይን ሲወጋ ከሚኖረው የአንጎል መነቃቃት ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል ታይቷል” ብለዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁማርተኞች ለማግኘት የሚመኙት የማንን ገንዘብ ነው?