በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ቃርሚያ ምንድን ነው? ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ የነበሩትስ እነማን ናቸው?

የሙሴ ሕግ፣ ገበሬዎች መሬታቸው ላይ ያለውን ምርት ሙሉ በሙሉ እንዳይሰበስቡ ይከለክል ነበር። ከዚህ ይልቅ ሰብላቸውን ሲያጭዱ በእርሻው ዳርና ዳር ያለውን ይተዉት ነበር። የወይን ፍሬ ሲሰበስቡ ደግሞ የወዳደቀውን መልቀም ወይም ሳይበስል በመቅረቱ መጀመሪያ ላይ ትተውት የሄዱትን ወይን እንደገና ለመሰብሰብ መመለስ አይኖርባቸውም ነበር። በተጨማሪም የወይራ ፍሬ ሲያራግፉ በቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ፍሬ መተው ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 24:19-21) በመሆኑም ድሆች፣ ወላጅ አልባ ልጆች፣ መበለቶችና መጻተኞች በማሳው ላይ የቀረውን መቃረም ወይም መሰብሰብ ይችሉ ነበር።

ቃርሚያን አስመልክቶ የተሰጠው ሕግ በእስራኤል የሚኖረውን እያንዳንዱን የኅብረተሰብ ክፍል ይጠቅም ነበር። የመሬቱ ባለቤቶች ከስስት እንዲርቁና ለጋስ እንዲሆኑ እንዲሁም በይሖዋ በረከት እንዲተማመኑ ያደርጋቸው ነበር። መቃረም ከባድ ሥራ በመሆኑ የሚቃርሙት ሰዎች ደግሞ ታታሪ ሠራተኛ እንዲሆኑ ያበረታታቸው ነበር። (ሩት 2:2-17) የቃርሚያ ዝግጅት ድሆች እንዳይራቡ ወይም በኅብረተሰቡ ላይ ሸክም እንዳይሆኑ ረድቷቸዋል። በተጨማሪም ምንም ሳይሠሩ መለመን ወይም የሰውን እጅ መጠበቅ ከሚያስከትለው የዝቅተኝነት ስሜት ጠብቋቸዋል።

ሰለሞን በኢየሩሳሌም ለሚገነባው ቤተ መቅደስ ከሊባኖስ ድረስ እንጨት ማስመጣት ለምን አስፈለገው?

በ⁠1 ነገሥት 5:1-10 ላይ የሚገኘው ዘገባ በሰለሞንና የጢሮስ ንጉሥ በሆነው በኪራም መካከል ስምምነት እንደተደረገ ይገልጻል። በተደረገው ስምምነት መሠረት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን የዝግባና የጥድ ግንድ ባሕር ላይ እንዲንሳፈፍ ተደርጎ ከሊባኖስ ወደ እስራኤል ይላክ ነበር።

በጥንት ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ የዝግባ እንጨት ንግድ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር። በግብፅና በሜሶጶጣሚያ የነበሩ ሰዎች ቤተ መቅደሶችንና ቤተ መንግሥቶችን ሲሠሩ የዝግባን እንጨት ወራጅ አድርገው ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ሕንጻዎችን ለማስጌጥም ይገለገሉበት ነበር። የነገሥታት መዛግብት፣ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችና የተቀረጹ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት የዝግባ እንጨት ወደተለያዩ የደቡብ ሜሶጶጣሚያ ከተሞች ይላክ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በምርኮ ይወሰድ ብሎም በግብር መልክ ይሰጥ ነበር። በግብፅ ደግሞ ነገሥታት የሚጠቀሙባቸውን ታንኳዎች አልፎ ተርፎም የሬሳ ሣጥንና ሌሎች ለቀብር ሥነ ሥርዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ለመሥራት ያገለግል ነበር።

የሊባኖስ ዝግባ በጥንካሬው፣ በውበቱና በጥሩ መዓዛው የታወቀ ነበር፤ በምስጥ በቀላሉ የማይበላ መሆኑም ሳይጠቀስ አይታለፍም። በመሆኑም ሰለሞን ቤተ መቅደሱን ምርጥ በሆነ እንጨት መገንባት ፈልጎ ነበር። በአንድ ወቅት የሊባኖስን ተራሮች ይሸፍን የነበረው የዝግባ ዛፍ አሁን እጅግ ተመናምኗል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሊባኖስ ዝግባ ሲጓጓዝ፣ በፋርስ ከነበረው የሳርጎን ቤተ መንግሥት የተገኘ ምስል

[የሥዕሉ ምንጭ]

Erich Lessing/Art Resource, NY