ልጆቻችሁን አስተምሩ
በአምላክም ሆነ በጓደኞቿ ዘንድ ተወዳጅ ነበረች
በአሁኑ ወቅት ስሟ ማን እንደሆነ የሚያውቅ ሰው የለም። ዛሬ የምትታወቀው የዮፍታሔ ልጅ ተብላ ነው። ስለ እነዚህ ሁለት ሰዎች ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን እንመርምር። ይህም የዮፍታሔ ሴት ልጅ በይሖዋ ብቻ ሳይሆን በጓደኞቿም ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነች ለመገንዘብ ያስችለናል።
ስለ ዮፍታሔና ስለ ሴት ልጁ የሚናገረውን ታሪክ መሳፍንት 11 ላይ ማግኘት እንችላለን። ዮፍታሔ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በመሆኑ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት በየጊዜው ከልጁ ጋር ይወያይ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።
ዮፍታሔ የኖረው የአምላክ ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ከመጠየቃቸው በፊት ነበር። ዮፍታሔ ጥሩ የውጊያ ችሎታ ያለው ጠንካራ ሰው ነበር። በመሆኑም እስራኤላውያን በአካባቢያቸው ከሚኖሩት አሞናውያን ጋር በሚያደርጉት ጦርነት መሪያቸው እንዲሆን ዮፍታሔን ጠየቁት።
ዮፍታሔ አሞናውያንን ለማሸነፍ አምላክ እንዲረዳው ስለፈለገ አንድ ስዕለት ተሳለ። ይሖዋ በጦርነቱ እንዲያሸንፍ ከረዳው ወደ ቤቱ ሲመለስ እሱን ለመቀበል ከቤት አስቀድሞ የሚወጣውን ሰው ለይሖዋ ለመስጠት ቃል ገባ። ይህ ግለሰብ ቀሪ የሕይወት ዘመኑን በሙሉ በዚያን ጊዜ ሰዎች አምላክን በሚያመልኩበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያገለግላል። ከቤት አስቀድሞ የወጣው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— *
አዎ፣ በመጀመሪያ የወጣችው የዮፍታሔ ሴት ልጅ ነበረች! በዚህ ጊዜ ዮፍታሔ በጣም አዘነ። ያለችው ልጅ እሷ ብቻ ነበረች። ይሁንና ለይሖዋ ስዕለት ስለተሳለ ቃሉን መጠበቅ ነበረበት። ልጁም ምንም ሳታቅማማ እንዲህ አለችው፦ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ . . . ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ።” ከዚያም ለብቻዋ ወደ ተራራ ሄዳ ለማልቀስ ሁለት ወር እንዲሰጣት ጠየቀች። ያዘነችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አባቷ የገባውን ቃል ለመፈጸም ስትል ጋብቻ የመመሥረትና ልጆች የመውለድ መብቷን መተው ነበረባት። ይሁንና ይህን ፍላጎቷን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ነገር አድርጋ አልተመለከተችውም ነበር። አባቷን የመታዘዝ ብሎም ለይሖዋ ታማኝ የመሆን ፍላጎት ነበራት። ይህች ልጅ ይሖዋንና አባቷን እንዳስደሰተች ይሰማሃል?—
በመሆኑም ዮፍታሔ፣ ልጁ ከሴት ጓደኞቿ ጋር ለሁለት ወራት ወደ ተራራ እንድትሄድ ፈቀደላት። ከዚያ እንደተመለሰች አባቷ ቀሪ ሕይወቷን ሴሎ በሚገኘው የአምላክ የማደሪያ ድንኳን ውስጥ እንድታገለግል ሲል ልጁን ወደዚያ ወሰዳት፤ በዚህ መንገድ ዮፍታሔ ስዕለቱን ፈጸመ። እስራኤላውያን ወጣት ሴቶች በየዓመቱ ወደ ሴሎ እየሄዱ የዮፍታሔን ልጅ ያበረታቷት ነበር።
አንተስ ወላጆቻቸውን የሚታዘዙና ይሖዋን የሚወዱ የምታውቃቸው ልጆች አሉ?—ከእነዚህ ልጆች ጋር በደንብ ብትተዋወቅና እነሱን ጓደኛ ብታደርጋቸው ጥሩ ነው። አንተም የዮፍታሔን ሴት ልጅ ምሳሌ በመከተል ታዛዥና ታማኝ ከሆንክ ጥሩ ጓደኞች ማፍራት ትችላለህ። እንዲህ ስታደርግ ወላጆችህ ይደሰቱብሃል፤ ይሖዋም ይወድሃል።
ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ
-
እና 1 ቆሮንቶስ 7:37, 38ን አንብብ።
^ አን.6 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።