ኤደን ገነት—በእርግጥ የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ነበር?
ኤደን ገነት—በእርግጥ የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ነበር?
በአንድ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በአካባቢው ምንም የሚረብሽ ነገር የለም፤ ከሩቅ የሚመጣም የከተማ ጫጫታ ባለመኖሩ ስፍራው ሰላማዊ ነው። ይህ የአትክልት ስፍራ በጣም ሰፊ ሲሆን ጸጥታውን የሚያደፈርስ አንዳች ነገር የለም። ከሁሉ በላይ ደግሞ አእምሮህ ከጭንቀት ነፃ ነው፤ በዚያ ላይ አለርጂን ጨምሮ ምንም ዓይነት በሽታ ስለሌለ ምንጊዜም ጤናማ ነህ። በስሜት ሕዋሳትህ ተጠቅመህ የአካባቢህን ውበት እንዳታደንቅ እንቅፋት የሚሆንብህ ምንም ነገር የለም።
ገና እንደገባህ ዓይኖችህ በቀለማት ባሸበረቁት አበቦች ላይ ያርፋሉ፤ ከዚያም ዞር ስትል ኩልል እያሉ የሚፈሱ ጅረቶችን ትመለከታለህ። ወዲያው ደግሞ አረንጓዴ ምንጣፍ የሚመስለው ሣርና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዕፅዋት ቀልብህን ይስቡታል፤ አንዳንዶቹ የፀሐይ ብርሃን ሲያርፍባቸው በሚፈጥሩት ውበት እጅግ ትደመማለህ። መንፈስን የሚያድሰው ነፋሻማ አየር ቆዳህ ላይ ሲያርፍ ይሰማሃል፤ እግረ መንገዱን ይዞት የሚመጣው አስደሳች መዓዛ ደግሞ አፍንጫህን ያውደዋል። ነፋስ የሚያወዛውዛቸው ዛፎችና ከዓለት ጋር እየተላተመ የሚወርደው የወንዝ ውኃ የሚያሰሙት ድምፅ ልዩ ስሜት ይፈጥርብሃል፤ የአእዋፋትን ዝማሬና በሥራ የተጠመዱ ነፍሳትን ድምፅ መስማትም ቢሆን ጆሮህ አይሰለቸውም። ይህን ስፍራ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ስትሞክር ምን ተሰማህ? ‘ምናለ እንዲህ ባለ ቦታ በኖርኩ’ ብለህ አልተመኘህም?
በመላው ዓለም ያሉ ሕዝቦች የሰው ልጅ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ባለ ስፍራ ይኖር እንደነበር ያምናሉ። በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች አምላክ አዳምንና ሔዋንን ከፈጠራቸው በኋላ በኤደን የአትክልት ስፍራ እንዳኖራቸው ለብዙ ዘመናት ሲማሩ ኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አዳምና ሔዋን ሰላማዊና አስደሳች ሕይወት ይመሩ ነበር። እርስ በርሳቸውም ሆነ ከእንስሳት ጋር እንዲሁም በዚያ ውብ አካባቢ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ከሰጣቸው ከደጉ አምላካቸው ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነበራቸው።—ዘፍጥረት 2:15-24
ሂንዱዎችም ቢሆኑ በጥንት ዘመን ስለነበረችው ገነት የራሳቸው የሆነ ግንዛቤ አላቸው። ቡዲስቶች ደግሞ በወርቃማ ዘመናት ላይ ይኸውም ዓለም እንደ ገነት በምትሆንባቸው ጊዜያት ታላላቅ መንፈሳዊ መሪዎች ወይም ቡድሃዎች ይነሳሉ ብለው ያምናሉ። በአፍሪካ ያሉ በርካታ ሃይማኖቶችም ከአዳምና ሔዋን ታሪክ ጋር በሚገርም ሁኔታ የሚመሳሰሉ ታሪኮችን ያስተምራሉ።
እንዲያውም በጥንት ዘመን ስለነበረችው ገነት የሚገልጽ ሐሳብ በሁሉም
ሃይማኖትና ባሕል ውስጥ ይገኛል ማለት ይቻላል። አንድ የታሪክ ምሑር እንደገለጹት “በርካታ ማኅበረሰቦች በጥንት ዘመን ፍጽምናን የተላበሰች፣ ነፃነት የነገሠባት፣ ሰላምና ደስታ የሰፈነባት፣ ሁሉ ነገር የተንበሸበሸባት እንዲሁም ከስጋት፣ ከውጥረትና ከግጭት ነፃ የሆነች ገነት እንደነበረች የሚያምኑ መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። . . . ይህ እምነት ብዙኃኑ የጠፋችውን ሆኖም ያልተረሳችውን ገነት በእጅጉ እንዲናፍቅና ይህችን ገነት መልሶ የማግኘት ብርቱ ምኞት እንዲያድርበት አድርጓል።”እነዚህ ሁሉ ታሪኮችና ባሕሎች አንድ የጋራ መሠረት ይኖራቸው ይሆን? “ብዙኃኑ” እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲይዝ ያደረገ በድሮ ዘመን የተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ ይኖር ይሆን? በጥንት ዘመን በእርግጥ የኤደን የአትክልት ስፍራ ነበር? አዳምና ሔዋንስ በገሐዱ ዓለም የኖሩ ሰዎች ነበሩ?
ተጠራጣሪዎች ይህን ሐሳብ ያጣጥሉታል። ሳይንስ በተራቀቀበት በዚህ ዘመን ብዙ ሰዎች ስለ ኤደን ገነት የሚናገሩት ዘገባዎች ከፈጠራ ታሪክና ከተረት ያለፉ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ከእነዚህ ተጠራጣሪዎች መሃል ብዙ የሃይማኖት መሪዎች የሚገኙበት መሆኑ የሚያስገርም ነው። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ኤደን ገነት የሚባል ስፍራ ኖሮ አያውቅም ብለው ይናገራሉ። ስለ ኤደን ገነት የሚናገረው ዘገባ ተምሳሌትነት ያለው፣ ተረት፣ የፈጠራ ታሪክ ወይም ተራ ምሳሌ እንጂ እውነተኛ ታሪክ አይደለም ይላሉ።
እርግጥ ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደ ምሳሌ የተነገሩ ታሪኮች አሉ። እንዲያውም በጣም ታዋቂ የሆኑትን ምሳሌዎች የተናገረው ኢየሱስ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ኤደን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በምሳሌ መልክ የቀረበ ሳይሆን ግልጽና ምንም ያልተወሳሰበ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ከተጻፈበት መንገድ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ስለ ኤደን ገነት የሚናገረው ዘገባ ጨርሶ ያልተፈጸመ ታሪክ ከሆነ በተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ እንዴት እምነት መጣል እንችላለን? እስቲ አንዳንዶች ስለ ኤደን ገነት የሚገልጸውን ዘገባ የሚጠራጠሩት ለምን እንደሆነ እንመርምር፤ ከዚያም የሚያቀርቡት ምክንያት አጥጋቢ መሆን አለመሆኑን እናያለን። በተጨማሪም ዘገባው የእያንዳንዳችንን ሕይወት ይነካል የምንልበትን ምክንያት እንመለከታለን።