በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

ዶን ኪኾቴ፣ በ16ተኛው መቶ ዘመን የኖረው ሚጌል ዴ ሴርቫንቴስ የተባለ ስፔናዊ ደራሲ ዶን ኪኾቴ በተባለው ምርጥ ልብ ወለድ ሥራው ውስጥ የጠቀሰው ታዋቂ ገጸ ባሕርይ ነው። በዚህ ድርሰት ላይ ዶን ኪኾቴ፣ ከብረት የተሠራ የጦር ልብስ ለብሰው አደጋ ውስጥ ያለችን ልጃገረድ ለመታደግ ስለሚጓዙ ጀግኖች የሚነገሩ በርካታ አፈ ታሪኮችንና ተረቶችን ያነብ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እሱም እንደ እነዚህ ጀግኖች እንደሆነ ራሱን አሳመነ። በአንድ ወቅት በነፋስ የሚሠሩ ኃይል ማመንጫዎችን ሲመለከት ግዙፍ የሆኑ አደገኛ ሽፍቶች እንደሆኑ በማሰብ ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። እነዚህን ሽፍቶች መግደሉ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንደሆነ በማመን ያደረገው ነገር ለከፍተኛ ውርደት ዳርጎታል።

ዶን ኪኾቴ በልብ ወለድ ድርሰት ውስጥ የሚገኝ ገጸ ባሕርይ በመሆኑ ድርጊቱ ሊያስቅ ይችላል፤ በገሃዱ ዓለም ግን አንድ ሰው መታለሉ ብዙውን ጊዜ አደገኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የፈለገውን ያህል ቢጠጣ ምንም እንደማይሆን የሚያስብን የአልኮል ሱሰኛ እንውሰድ፤ እንዲህ ያለው ሰው ጤንነቱ እንደሚቃወስና የቤተሰብ ሕይወቱ እንደሚናጋ የታወቀ ነው። ወይም ደግሞ ሥር የሰደደ የአመጋገብ ችግር ቢኖርባትም በደንብ እንደምትመገብና ጤነኛ እንደሆነች የሚሰማትን ሴት እንመልከት፤ ይህች ሴት ራሷን እያስራበች በመሆኑ ውሎ አድሮ ሕይወቷ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ግልጽ ነው።

ታዲያ እኛስ በዚህ ዓይነቱ ወጥመድ ልንወድቅ እንችላለን? የሚያሳዝን ቢሆንም የዚህ ጥያቄ መልስ አዎን የሚል ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም ለመታለል አደጋ የተጋለጥን ነን። ሌላው ቀርቶ ትልቅ ግምት ከምንሰጣቸው ሃይማኖታዊ እምነቶቻችን ጋር በተያያዘም ልንታለል የምንችል ሲሆን ይህም አስከፊ መዘዝ ያስከትላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እንዳትታለል መጠንቀቅ የምትችለውስ እንዴት ነው?

መታለል የሚያስከትለው አደጋ

አንድ መዝገበ ቃላት ማታለል የሚለውን ቃል “ውሸት የሆነን ወይም ትክክል ያልሆነን ሐሳብ እውነት ወይም ትክክል እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ” በማለት ፈቶታል። በተጨማሪም ቃሉ “አለማወቅን፣ ግራ መጋባትን ወይም አማራጭ ማጣትን የሚያስከትል ትክክል ያልሆነ ሐሳብ ወይም እምነት ማስተላለፍን” ያመለክታል። “ማታለል” የሚለው ቃልም ሆነ “ማሳሳት” እና “ማሞኘት” የሚሉት ቃላት የሚያስተላልፉት መሠረታዊ ሐሳብ ‘አንድን ሰው በተንኮል ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መምራት’ የሚል ነው። በእርግጥም አንድ ሰው ሆን ተብሎ በሚነገረው የተሳሳተ መረጃ የተነሳ እውነቱን ‘እንዳያውቅ፣ ግራ እንዲጋባ ወይም አማራጭ እንዲያጣ’ እየተደረገ መሆኑን ካልተገነዘበ ያለበት ሁኔታ አደገኛ ነው።

በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የተታለለው ወይም የተሞኘው ግለሰብ መሳሳቱን የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎች ቢቀርቡለትም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ነው። የሚያምንባቸውን ነገሮች በጣም ከመውደዱ የተነሳ የእነዚህን ነገሮች ትክክለኛነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ማንኛውም ማስረጃ ቢቀርብለት ለመቀበል አሻፈረኝ ይላል።

አደጋ ውስጥ ነን?

‘በሃይማኖታዊ እምነታችን ረገድ ሁላችንም ለመታለል አደጋ የተጋለጥን ነን ብሎ መናገር ማጋነን አይሆንም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። በፍጹም! እንዲህ የምንለው ኢየሱስ “የውሸት አባት” ብሎ የጠራው ሰይጣን ዲያብሎስ ሁላችንንም ለማታለልና ለማሳሳት ቆርጦ የተነሳ በመሆኑ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በማለት ይገልጸዋል። ሰይጣን በታሪክ ዘመናት በሙሉ የኖሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “አእምሮ አሳውሯል።” (2 ቆሮንቶስ 4:4) አሁንም እንኳ “መላውን ዓለም እያሳሳተ” ነው።—ራእይ 12:9

ሰይጣን የሰውን ዘር ማሳሳት የጀመረው የሰው ልጅ ታሪክ አንድ ብሎ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሔዋንን ፈጣሪዋ ላወጣው ሕግ የመገዛት ግዴታ እንደሌለባት እንዲሁም “መልካምንና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር” መሆን እንደምትችል ማለትም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ራሷ መወሰን እንደምትችል እንድታምን በማድረግ አታሏታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) ይህ የመጀመሪያው ትልቅ ማታለያ ነበር፤ ምክንያቱም አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር የመምረጥ ነፃነት ቢሰጣቸውም ትክክል የሆነውንና ስህተት የሆነውን ነገር ራሳቸው የመወሰን ችሎታ አልሰጣቸውም። አምላክ ፈጣሪና ሉዓላዊ ገዥ እንደመሆኑ መጠን እንዲህ የማድረግ መብቱም ሆነ ሥልጣኑ ያለው እሱ ብቻ ነው። (ኤርምያስ 10:23፤ ራእይ 4:11) የሰው ልጆች መልካም ወይም ክፉ የሆነውን የመምረጥ መብት ስላላቸው መልካም ወይም ክፉ የሆነውን የመወሰንም መብት ይኖራቸዋል ብሎ ማመን እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! የሚያሳዝነው ነገር፣ ፍጽምና የሌለን የሰው ልጆች እንዲህ ባለው ወጥመድ በቀላሉ እንወድቃለን።

በአንተስ ላይ ሊደርስ ይችላል?

ትልቅ ቦታ የምትሰጣቸው ሃይማኖታዊ እምነቶችህ ለዘመናት የቆዩ ምናልባትም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ለረጅም ጊዜ የቆዩ መሆናቸው ብቻ እውነት ናቸው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ለምን? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የክርስቶስ ሐዋርያት ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አታላዮች እንደተነሱና “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር” እንዳስተማሩ ይጠቁማል። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) እነዚህ ግለሰቦች ‘በማግባባት’ እንዲሁም “በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ” በመጠቀም ሰዎችን በዘዴ ማታለል ችለዋል።—ቆላስይስ 2:4, 8

ዛሬስ ቢሆን ሁኔታው የተለየ ይሆን? በፍጹም! እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ማለትም አሁን በምንኖርበት ዘመን ነገሮች እየባሱ እንደሚሄዱ አስጠንቅቋል። ጳውሎስ “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” በማለት ጽፏል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13

ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር መመልከት የጥበብ እርምጃ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:12) እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ስላለው አቋም ነው። በመሠረቱ ‘ሰይጣን ፈጽሞ አያታልለኝም’ ብሎ ማሰብ በራሱ ትልቅ ሞኝነት ነው። ማንም ቢሆን የሰይጣን “መሠሪ ዘዴዎች” ተጽዕኖ አያሳድሩብኝም ማለት አይችልም። (ኤፌሶን 6:11) ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ ሲጽፍ “እባቡ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳታለላት ሁሉ እናንተም አእምሯችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ልታሳዩ የሚገባውን ቅንነትና ንጽሕና በሆነ መንገድ እንዳታጡ እፈራለሁ” በማለት ስጋቱን የገለጸው ለዚህ ነው።—2 ቆሮንቶስ 11:3

እንዳትታለል መጠንቀቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ታዲያ ሰይጣን እንዳያታልልህ መጠንቀቅ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክን “በመንፈስና በእውነት” እያመለክህ እንዳለህ እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ? (ዮሐንስ 4:24) በዚህ ረገድ ይሖዋ አምላክ ያደረገልህን ዝግጅት ተጠቀምበት። በመጀመሪያ፣ እውነትን ከሐሰት መለየት እንድትችል “የማስተዋል ችሎታ” ሰጥቶሃል። (1 ዮሐንስ 5:20) ከዚህም በተጨማሪ የሰይጣንን ዕቅድ ማወቅ እንድትችል አድርጎሃል። (2 ቆሮንቶስ 2:11) እንዲያውም ሰይጣን አንተን ለማሳሳት የሚያደርገውን ጥረት ማክሸፍ እንድትችል የሚያስፈልጉህን ነገሮች በሙሉ ሰጥቶሃል።—ምሳሌ 3:1-6፤ ኤፌሶን 6:10-18

ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ፣ ራስህን መጠበቅ የምትችልበትን አስተማማኝ መሣሪያ ሰጥቶሃል። ይህ መሣሪያ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው የሆነውን ጢሞቴዎስን፣ ከሃይማኖታዊ እምነቱ ጋር የተያያዙ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በዚህ መሣሪያ እንዲጠቀም አበረታቶታል። ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስ ‘ክፉ ሰዎችንና አስመሳዮችን’ አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ከሰጠው በኋላ የሚያምንባቸው ነገሮች በሙሉ ‘በቅዱሳን መጻሕፍት’ ይኸውም የአምላክ ቅዱስ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ በማድረግ እነዚህን ሰዎች መቋቋም እንደሚችል ነግሮታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15

እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች በአምላክ የሚያምንና መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ የተጻፈ መሆኑን የሚቀበል ማንኛውም ሰው እንደተታለለ ይናገሩ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የተታለሉት የፈጣሪን ሕልውና እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጡትን በርካታ ማስረጃዎች ለመቀበል እምቢተኞች የሆኑት ሰዎች ናቸው። *ሮም 1:18-25፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:19-21

‘በውሸት “እውቀት” ተብለው በሚጠሩ’ ነገሮች ከመታለል ይልቅ እውነትን ለማወቅ በአምላክ ቃል ተጠቀም። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) ሐዋርያው ጳውሎስ በቤርያ ሳለ የመሠከረላቸውን ልበ ቀና ሰዎች ምሳሌ ተከተል። እነዚህ ሰዎች “ቃሉን በታላቅ ጉጉት ተቀብለዋል።” ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተማራቸውን ነገሮች በጉጉት ከመቀበላቸውም ባሻገር “የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየዕለቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ [መርምረዋል]።”—የሐዋርያት ሥራ 17:11

አንተም ቢሆን በዚህ መልኩ እምነትህን ለመመርመር መፍራት የለብህም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማንኛውንም ነገር እንደ እውነት አድርገህ ከመቀበልህ በፊት ‘ሁሉንም ነገር እንድትመረምር’ ያበረታታሃል። (1 ተሰሎንቄ 5:21) በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ” በማለት አሳስቧቸዋል። (1 ዮሐንስ 4:1) በእርግጥም፣ አንድ ሃይማኖታዊ ትምህርት “በመንፈስ የተነገረ” ወይም ከአምላክ የመጣ የሚመስል ቢሆንም እንኳ ትክክል እንደሆነ አድርገህ ከመቀበልህ በፊት ቅዱሳን መጻሕፍትን በመመርመር ማረጋገጡ የጥበብ አካሄድ ነው።—ዮሐንስ 8:31, 32

የተማርከውን ተግባራዊ አድርግ

ይሁንና ልታደርገው የሚገባ ሌላም ነገር አለ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ የውሸት ምክንያት እያቀረባችሁ ራሳችሁን በማታለል ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:22) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ማወቅ ብቻውን በቂ አይደለም። ያወቅሃቸውን ነገሮች በተግባር ላይ ማዋል አለብህ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክ እንድታደርግ ያዘዘህን ነገሮች በመፈጸምና የከለከለህን ነገሮች ባለማድረግ ነው።

ለምሳሌ ያህል፣ በዓለም ላይ የሚታየውን የሥነ ምግባር ውድቀት እስቲ እንመልከት። ይህ ሁኔታ ሰዎች የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግጋት መጣሳቸው ምንም ችግር እንደማያስከትልባቸው እያሰቡ እንዲታለሉ በማድረግ ረገድ ሰይጣን ምን ያህል እንደተሳካለት አያሳይም? በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ግልጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል፦ “አትታለሉ፦ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

ኢየሱስ፣ እሱ የተናገረውን ቃል “ሰምቶ በተግባር የማያውል” በመሆኑ “ሞኝ” ብሎ የጠራው ዓይነት ሰው መሆን የለብህም። በሴርቫንቴስ ድርሰት ውስጥ የተጠቀሰው ዶን ኪኾቴ በምናቡ በፈጠረው ነገር እንደተታለለ ሁሉ ኢየሱስ የጠቀሰውም ሰው በአሸዋማ ቦታ ላይ ጠንካራና በቀላሉ የማይናወጥ ቤት መሥራት እንደሚችል በማሰብ ተታልሏል። ከዚህ ይልቅ ‘ቤቱን በዐለት ላይ እንደሠራው’ ሰው ሁን። ኢየሱስ፣ እሱ ያስተማረውን ሰምቶ ‘በተግባር ያዋለውን’ ይህን ሰው “አስተዋይ” ሲል ጠርቶታል።—ማቴዎስ 7:24-27

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስየአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባሉትን መጻሕፍት ተመልከት።

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የነገሮችን ትክክለኛ ገጽታ ትመለከታለህ?

በ1930ዎቹ ዓመታት ኦስካር ሮይተርስቫርድ የተባለ ስዊድናዊ ሠዓሊ ኢምፖስብል ፊገርስ በመባል የታወቁትን ሥዕሎች በተከታታይ በመሥራት አሳትሞ ነበር። በስተግራ ያለው ምስል ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉ ሥዕሎችን መጀመሪያ ላይ አየት ስናደርጋቸው ፈጽሞ የማይቻለውን ነገር መሥራት የተቻለ እንዲመስለን ያደርጋሉ። ይሁንና በጥንቃቄ ስናያቸው ሠዓሊው ተመልካቹን ግራ ለማጋባት ወይም ለማሳሳት ሲል በዘዴ የሠራው ነገር መሆኑን መመልከት ይቻላል።

መጀመሪያ ላይ ስናያቸው የሚያሳስት ገጽታ ያላቸው ኢምፖስብል ፊገርስ የሚባሉት ሥዕሎች ብቻ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፦ “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።”—ቆላስይስ 2:8

ይህን ማስጠንቀቂያ የጻፈው ሰው ራሱ ተታልሎ የነበረ መሆኑ ለተናገረው ነገር ይበልጥ ክብደት እንድንሰጠው ያደርገናል። ይህ ሰው፣ በጊዜው ከነበሩት በጣም ታዋቂ የሃይማኖት መምህራን በአንዱ እግር ሥር ተቀምጦ የተማረና ትልቅ ቦታ ካላቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበረው በመሆኑ በቀላሉ የሚታለል ዓይነት ሰው አይመስልም ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 22:3

ይህ ሰው የጠርሴሱ ሳኦል ሲሆን የተማረው ነገር፣ የእሱን ሃይማኖታዊ ወጎችና ልማዶች የማይከተል ማንኛውም ሰው ሊወገዝ እንደሚገባ እንዲያምን አድርጎት ነበር። ሳኦል ከአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በተቀበለው ሥልጣን በመጠቀም፣ ክርስቲያናዊ እምነታቸውን ለመካድ ፈቃደኛ ያልሆኑትን ሰዎች በሙሉ ማሳደዱ አምላክ የሰጠውን ተልዕኮ መፈጸም እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ሌላው ቀርቶ በአንድ ወቅት፣ አምላክን ሰድቧል ተብሎ በሐሰት የተወነጀለ የአገሩ ሰው ሲገደል ተባባሪ ሆኖ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 22:4, 5, 20

ከጊዜ በኋላ ሳኦል፣ ትክክልና ስህተት በሆኑ እንዲሁም አምላክ በሚቀበላቸውና በማይቀበላቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል እንዲችል አምላክ እርዳታ አደረገለት። ሳኦል መሳሳቱን ሲገነዘብ ወዲያውኑ አካሄዱን አስተካከለ፤ ይህ ሰው ጳውሎስ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ቀናተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ለመሆን ችሏል። ጳውሎስ ትክክለኛው ነገር ስለገባው እውነተኛውን አምልኮ መከተል ጀመረ።—የሐዋርያት ሥራ 22:6-16፤ ሮም 1:1

ልክ እንደ ጳውሎስ በርካታ ልበ ቅን ሰዎች፣ ኢምፖስብል ፊገርስ እንደሚባሉት ሥዕሎች አሳማኝ በሚመስሉ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ በሌላቸው ትምህርቶች ተታልለው ነበር። (ምሳሌ 14:12፤ ሮም 10:2, 3) ሆኖም ሃይማኖታቸው የሚያስተምራቸውን ነገሮችና ያፈራቸውን ፍሬዎች ትክክለኛ ገጽታ ለመመልከት የሚያስችል እርዳታ አገኙ። (ማቴዎስ 7:15-20) እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እየቀሰሙ ሲሄዱ በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ በሚያምኑባቸው ነገሮችና በአኗኗር ዘይቤያቸው ላይ ለውጥ አድርገዋል።

አንተስ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በመከተል የምታምንባቸውን ነገሮች የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ለመመርመር ፈቃደኛ ነህ? የይሖዋ ምሥክሮች አንተን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Engravings by Doré