በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ድል ሰልፍ” ሲናገር በአእምሮው ምን ይዞ ሊሆን ይችላል?

ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[አምላክ] በድል ሰልፍ ከክርስቶስ ጋር አብረን እንድንጓዝ በማድረግ [ይመራናል]፤ የእውቀቱ ሽታ በእኛ አማካኝነት በሁሉም ቦታ እንዲናኝ [ያደርጋል]። ምክንያቱም እኛ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ባሉት መካከልና ወደ ጥፋት እያመሩ ባሉት መካከል ለአምላክ የክርስቶስ መዓዛ ነን፤ ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ሞት የሚያስከትል የሞት ሽታ፣ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላሉት ደግሞ ሕይወት የሚያስገኝ የሕይወት ሽታ ነን።”—2 ቆሮንቶስ 2:14-16

ሐዋርያው፣ በሮማውያን ልማድ መሠረት አንድ ጄኔራል በአገሩ ጠላቶች ላይ ድል ሲቀዳጅ ለጄኔራሉ ክብር ለመስጠት ሲባል የሚደረገውን የድል ሰልፍ እየጠቀሰ ነበር። በዚህ ጊዜ ምርኮውም ሆነ የጦር እስረኞቹ ለሕዝብ እይታ የሚቀርቡ ሲሆን በሬዎች መሥዋዕት ወደሚደረጉበት ስፍራ ይነዳሉ፤ ድል አድራጊው ጄኔራልና ሠራዊቱ ደግሞ ከሕዝቡ አድናቆትና ውዳሴ ይጎርፍላቸዋል። በሰልፉ መገባደጃ ላይ በሬዎቹ መሥዋዕት ይደረጋሉ፤ እንዲሁም አብዛኞቹ እስረኞች ይገደላሉ።

ለአንዳንዶች ሕይወትን ለሌሎች ደግሞ ሞትን የሚያመለክተው “የክርስቶስ መዓዛ” የሚለው ተለዋጭ ዘይቤ “ምናልባት ሮማውያን የድል ሰልፉ በሚካሄድበት ጊዜ ያከናውኑት ከነበረው ዕጣን የማጨስ ልማድ የመጣ ሊሆን ይችላል” በማለት ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ ይገልጻል። “ላሸነፉት ሰዎች ድልን የሚያመለክተው መዓዛ ለምርኮኞቹ ደግሞ የሚጠብቃቸውን የሞት ቅጣት ያስታውሳቸዋል።” *

በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙ ጊዜ የተጠቀሱት ‘በኰረብታ ላይ የተሠሩ መስገጃዎች’ ወይም “የማምለኪያ ኰረብቶች” ምንድን ናቸው?

እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በተቃረቡበት ጊዜ ይሖዋ በዚያ ይኖሩ የነበሩትን የከነዓናውያንን የማምለኪያ ቦታዎች በሙሉ እንዲያስወግዱ ነግሯቸው ነበር። አምላክ “የተቀረጹ ምስሎቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶቻቸውን በሙሉ አጥፉ፤ እንዲሁም በኰረብታ ላይ የተሠሩትን መስገጃዎቻቸውን ሁሉ አፈራርሱ” በማለት አዟቸው ነበር። (ዘኍልቁ 33:52) እነዚህ የሐሰት አምልኮ ማዕከሎች በኮረብታ አናት ላይ የሚገኙ ምንም ዓይነት መጠለያ የሌላቸው ቦታዎች አሊያም በዛፎች ሥር ወይም በከተሞች ውስጥ እንደሚሠሩ ያሉ መድረኮች ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ነገሥት 14:23፤ 2 ነገሥት 17:29፤ ሕዝቅኤል 6:3) እነዚህ ቦታዎች መሠዊያዎች፣ ቅዱስ ዓምዶች ወይም ምሰሶዎች፣ ምስሎች፣ የዕጣን ማጨሻዎችና ለአምልኮ የሚያገለግሉ ሌሎች ዕቃዎች ሊኖሯቸው ይችላሉ።

የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ከመገንባቱ በፊት እስራኤላውያን ይሖዋን የሚያመልኩት ቅዱሳን መጻሕፍት የማምለኪያ ኮረብታዎች ብለው በሚጠሯቸው ተቀባይነት ያገኙ ቦታዎች ነበር። የአምላክ ነቢይ የነበረው ሳሙኤል ጹፍ በተባለ ምድር ስሙ ባልተጠቀሰ ከተማ ‘በማምለኪያው ኰረብታ’ ላይ መሥዋዕቶችን አቅርቦ ነበር። (1 ሳሙኤል 9:11-14) ቤተ መቅደሱ ከተገነባ በኋላ ግን ለይሖዋ ታማኝ የነበሩ በርካታ ነገሥታት “የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን” ከምድሪቱ ለማስወገድ ሞክረዋል።—2 ነገሥት 21:3፤ 23:5-8, 15-20፤ 2 ዜና መዋዕል 17:1, 6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ጳውሎስ የተናገረውን ምሳሌ መንፈሳዊ ትርጉም በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 15, 1990 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሮማውያንን የድል ሰልፍ የሚያሳይ ምስል፣ ሁለተኛ መቶ ዘመን ዓ.ም.

[ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጌዜር የሚገኙ የፈራረሱ ቅዱስ ዓምዶች