መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
በሩሲያ የምትኖር የዕፅ ሱሰኛ የነበረች አንዲት ነጠላ ወላጅ ካለባት ሱስ መላቀቅና ከልጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሻሻል የቻለችው እንዴት ነው? በኪዮቶ፣ ጃፓን ይኖር የነበረ አንድ ጎዳና ተዳዳሪ ለድህነት የዳረገውን የግል ድክመት ለማሸነፍ የሚያስችል ጥንካሬና ድፍረት ያገኘው እንዴት ነው? በአውስትራሊያ የሚኖር ከብት በማገድ ሥራ የተሠማራ ሰው ከመጠን በላይ አልኮል የመጠጣት ልማዱን እንዲተው ያስቻለው ምን ነበር? እስቲ እነዚህ ሰዎች የሚሉትን እንስማ።
“ራሴን የማስተዳደር ግዴታ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።”—ኔሊ ባይማቶቫ
ዕድሜ፦ 45
የትውልድ አገር፦ ሩሲያ
የኋላ ታሪክ፦ የዕፅ ሱሰኛ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግሁት የሰሜን ኦሴሺያ ሪፑብሊክ (የአሁኗ አላኒያ) ዋና ከተማ በሆነችው በቭላዲካቭካዝ ነበር። ቤተሰቦቼ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ ሀብታሞች ነበሩ። በቁሳዊ ረገድ ምንም የጎደለብኝ ነገር ባይኖርም በሕይወቴ ግን ደስተኛ አልነበርኩም። ሠላሳ አራት ዓመት ሳይሞላኝ ሁለት ጊዜ አግብቼ ፈትቻለሁ። ለአሥር ዓመት አብሮኝ የቆየ የዕፅ ሱስ የነበረብኝ ሲሆን ሁለት ጊዜ ክሊኒክ ገብቼ የሕክምና እርዳታ ተደርጎልኛል። ሁለት ልጆች የነበሩኝ ቢሆንም በወቅቱ ለእነሱ ምንም ፍቅር አልነበረኝም፤ ከዚህም ባሻገር ከጓደኞቼና ከቤተሰቦቼ ጋር ጤናማ ግንኙነት አልነበረኝም።
ከጊዜ በኋላ እናቴ የይሖዋ ምሥክር ሆነች፤ እሷም ይሖዋ እንዲረዳኝ እያለቀሰች ስትጸልይ ብዙ ጊዜ እሰማት ነበር። እኔም ‘እናቴ እንዴት የዋህ ናት! ይሖዋ እንዴት ሊረዳኝ ይችላል?’ ብዬ አስብ ነበር። ዕፅ መውሰድ ለማቆም ሞክሬ ነበር። ይሁንና ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚያስችል ጥንካሬ አልነበረኝም። በአንድ ወቅት ለሁለት ቀን ያህል ዕፅ ሳልወስድ ቆየሁ። ከዚያም ከቤት መውጣት እንዳለብኝ ወሰንኩና በመስኮት ዘለልኩ። የሚያሳዝነው ነገር በወቅቱ የነበርኩት ሁለተኛ ፎቅ ላይ ነበር። ከዚህም የተነሳ በእጄና በእግሬ ላይ ስብራት የደረሰብኝ ሲሆን ወገቤም ተጎዳ። ስለሆነም ከአንድ ወር በላይ የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ።
እናቴ ከደረሰብኝ ጉዳት እስካገግም ድረስ የተንከባከበችኝ ሲሆን በተፈጠረው ሁኔታ አልወቀሰችኝም። ስሜቴ በቀላሉ ሊጎዳ እንደሚችልና አስተሳሰቤ የተዛባ እንደሆነ ተረድታ ነበር። ያም ሆኖ የተወሰኑ የንቁ! መጽሔት * እትሞች ከአልጋዬ አጠገብ ታስቀምጥልኝ ነበር። እኔም መጽሔቶቹን አንድ በአንድ ያነበብኳቸው ሲሆን በጣም ማራኪና ትምህርት ሰጪ መሆናቸውን ተገነዘብኩ። ከዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰንኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ያስተማረኝ አንዱ አስፈላጊ ነገር፣ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው መሆን እንዳለብኝ ነው። እናቴ እኔን እንድትደግፈኝ ከመጠበቅ ይልቅ ራሴንም ሆነ ልጆቼን የማስተዳደር ግዴታ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ያን ሁሉ ዘመን እንዳሻኝ ስኖር ከቆየሁ በኋላ ቋሚ ሥራ መሥራት ለእኔ ቀላል አልነበረም።
ዘዳግም 6:5-7 ላይ የሚገኘው ምክር በእርግጥ ረድቶኛል። ሁለቱን ልጆቼን ስለማሳድግበት መንገድ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደምሆን ተገነዘብኩ። ይህን ሐቅ ማስተዋሌ ከልጆቼ ጋር ጊዜ እንዳሳልፍና ለእነሱ ተገቢውን ፍቅር ለማዳበር ጥረት እንዳደርግ ገፋፋኝ።
በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ አምላክ ማስተማር እንዳለባቸው የሚገልጸው በይሖዋ ስለ እሱ እውነቱን እንድማር ስለፈቀደልኝ ውስጤ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞላ። ስለዚህ ሕይወቴን ለእሱ ወሰንኩኝና ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ የግልፍተኝነት ባሕርዬን መቆጣጠር በመማሬ ከእናቴ ጋር ያለኝ ግንኙነት ተሻሻለ። ከልጆቼ ጋር የነበረኝ ግንኙነትም እየተሻሻለ ሄዷል።
ሥነ ምግባር ለጎደላቸው ነገሮች ጥላቻ ስላዳበርኩ ከቀድሞ አኗኗሬ ጋር የተያያዙት ብዙዎቹ ችግሮች ተወግደውልኛል። አሁን ሌሎች፣ አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን ስለ ይሖዋ እውነቱን እንዲያውቁ በመርዳት ከፍተኛ ደስታ እያገኘሁ ነው።
“ሕይወቴን ቃል በቃል ከሞት እንዳተረፈልኝ ይሰማኛል።”—ሚኖሩ ታኬዳ
ዕድሜ፦ 54
የትውልድ አገር፦ ጃፓን
የኋላ ታሪክ፦ የጎዳና ተዳዳሪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በያማጉቺ ከተማ ሲሆን የምኖረው ከአባቴና ከሴት አያቴ ጋር ነበር። እናቴን ጨርሶ አላውቃትም። አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ ሴት አያቴ ሞተች፤ እኔም ከአባቴ ጋር መኖር ቀጠልኩ። በወቅቱ የወጥ ቤት ሠራተኛ ሆኜ እሠራ የነበረ ሲሆን አባቴም በዚሁ መስክ ተሰማርቶ ነበር። የሥራ ፈረቃችን ስለሚለያይ የምንገናኘው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። እኔም ረጅም ሰዓት የመሥራትና ከጓደኞቼ ጋር አልኮል የመጠጣት ልማድ ተጠናወተኝ።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሥራ ሰለቸኝ። ከአለቃዬ ጋር መጣላትና ብዙ መጠጣት ጀመርኩ። በኋላም በ20ዎቹ ዕድሜዬ መገባደጃ ላይ ስደርስ፣ ከቤት ለመውጣትና ከአገር ወደ አገር እየተዘዋወርኩ ለመጎብኘት ወሰንኩ። ገንዘቤ ሲያልቅብኝ በአንድ ፓቺንኮ (ቁማር) መጫወቻ ቤት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። በዚያም ከአንዲት ልጅ ጋር ተዋወቅሁና ተጋባን። ይሁን እንጂ ትዳራችን የቆየው ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ብቻ ነበር።
በጭንቀት ተውጬና አስተሳሰቤ ተዛብቶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቄ ነበር። ከዕዳ አስከፋዮቹ ሸሽቼ ወደ ትውልድ ከተማዬ በመሄድ ለተወሰነ ጊዜ ከአባቴ ጋር ተቀመጥኩ፤ ይሁን እንጂ እሱንም ስለዋሸሁት ግንኙነታችን ሻከረ። ከአባቴ ቤት ገንዘብ ሰርቄ ወጣሁና ለተወሰነ ጊዜ ቁማር እየተጫወትኩ መኖሬን ቀጠልኩ። ውሎ አድሮ ግን በከፋ ድህነት ላይ ወደቅሁና ለጥቂት ጊዜ በባቡር ጣቢያ ውስጥ ኖርኩ። በኋላም ወደ ሀካታ፣ ከዚያም ወደ ሂሜጂ፣ በመጨረሻም ወደ ኪዮቶ ከተማ ሄድኩ። ለተወሰኑ ዓመታት በጎዳና ላይ ኖሬያለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ1999 በኪዮቶ ውስጥ በካሞጋዋ ወንዝ አጠገብ በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ እያለሁ ሁለት ሴቶች ወደ እኔ መጡ። አንደኛዋ ሴት “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ትፈልጋለህ?” ስትል ጠየቀችኝ። እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። በአካባቢው ባለ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን አስጠኑኝ፤ እንዲሁም በውስጡ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ
ማዋል ያለውን ጠቀሜታ እንድገነዘብ ረዱኝ። ሥራና መኖሪያ ቤት ለማግኘት ጥረት እንዳደርግ ሐሳብ አቀረቡልኝ። እኔም እነሱን ለማስደሰት ስል ብቻ ሥራ ለማግኘት ሞክሬ ነበር፤ ያም ሆኖ መጀመሪያ ላይ ከልብ ጥረት አላደረግሁም። በኋላ ግን አምላክ እንዲረዳኝ መጸለይና ሥራ ለማግኘት ከልብ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ፤ ውሎ አድሮም ሥራ አገኘሁ።ጸሎት የገጠመኝን በጣም ከባድ ፈተና እንዳልፍም ረድቶኛል። ስሸሻቸው የኖርኩት ገንዘብ አበዳሪዎች ተከታትለው ደረሱብኝና ገንዘቡን እንድከፍላቸው ጠየቁኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ተጨነቅሁ። ከዚያም በየቀኑ በማደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወቅት በኢሳይያስ 41:10 የሚገኘውን ጥቅስ አነበብኩ። በዚህ ጥቅስ ላይ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን በእርግጥ ‘እንደሚረዳቸው’ ቃል ገብቶላቸዋል። አምላክ የገባው ይህ ቃል ለእኔም ብርታትና ድፍረት ሰጠኝ። በትጋት በመሥራት ውሎ አድሮ ያሉብኝን ገንዘብ ነክ ችግሮች መፍታት ቻልኩ። በ2000 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቃሁ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩት ነገር ከአባቴ ጋር የነበረኝን የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል እንድጥር ያነሳሳኝ ሲሆን እሱም ቀድሞ ለፈጸምኳቸው ድርጊቶች ይቅርታ አደረገልኝ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመርኩ ሲያውቅ ተደሰተ። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጌ ሕይወቴን ቃል በቃል ከሞት እንዳተረፈልኝ ይሰማኛል።
በተጨማሪም ሥራ በመሥራት የሚያስፈልጉኝን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት ችያለሁ። (ኤፌሶን 4:28፤ 2 ተሰሎንቄ 3:12) እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እውነተኛ ጓደኞች አግኝቻለሁ። (ማርቆስ 10:29, 30) ይሖዋ ስላስተማረኝ ነገሮች እጅግ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
“አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ ለእኔ ቀላል አልነበረም።”—ዴቪድ ሁድሰን
ዕድሜ፦ 72
የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ
የኋላ ታሪክ፦ ኃይለኛ ጠጪ
የቀድሞ ሕይወቴ፦ ለወላጆቼ ለዊሊና ለሉሲ 11ኛ ልጅ ነበርኩ። ቤተሰቦቼ የሚኖሩት በሰሜናዊ ኩዊንስላንድ ክልል፣ ርቆ በሚገኝ ኦሩከን ተብሎ በሚጠራ የአቦርጂኖች ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር። ኦሩከን የሚገኘው ውብ በሆነው የአርቸር ወንዝ ዳርቻ ላይ ሲሆን ከባሕር ብዙም አይርቅም ነበር። ወላጆቼ ለእኛ ለልጆቻቸው መተዳደሪያ እንዲሆነን አደንና ዓሣ ማጥመድ አስተምረውናል። በዚያን ጊዜ መንግሥት እኛ አቦርጂኖችን ገንዘብ እንዳንይዝ ይከለክለን የነበረ ሲሆን የምንኖረው ለእኛ ሲባል በተከለለ ቦታ ውስጥ ነበር።
ወላጆቼ በውስጤ ጥሩ ባሕርያትን ለመቅረጽ የቻሉትን ሁሉ ያደረጉ ሲሆን ሁላችንንም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉትን አረጋውያን እንድናከብርና ያለን ነገር ትንሽም ቢሆን እንኳ ለሌሎች ማካፈል እንዳለብን አስተምረውናል። በመሆኑም አረጋውያንን በሙሉ እንደ እናታችንና እንደ አባታችን እንዲሁም እንደ አክስቶቻችንና አጎቶቻችን አድርገን እንመለከታቸው ነበር።
የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ሞተ፤ እኛም ከኦሩከን በስተሰሜን 150 ኪሎ ሜትር ርቆ ወዳለውና በማፑን ወደሚገኘው
የአቦርጂኖች መኖሪያ ተዛወርን። ዕድሜዬ 12 ሲሆን ፈረሶችንና ከብቶችን መጠበቅ ጀመርኩ፤ እስከ 40ዎቹ ዕድሜዬ መገባደጃ ድረስም በብዙ የከብት ጣቢያዎች ውስጥ ከብት በማገድ ሠርቻለሁ። ኑሮው ችግር የበዛበት ነበር። እኔም አዘውትሬ በጣም እጠጣ የነበረ ሲሆን በዚያም የተነሳ ብዙ ጊዜ ራሴን ያመኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለተለያዩ ችግሮች ተዳርጌ ነበር።በአንድ ወቅት እንደወትሮዬ በጣም ጠጥቼ ሳለ፣ ከነበርኩበት ሆቴል እየተንገዳገድሁ ወጣሁና እየበረረ በሚሄድ መኪና ውስጥ ገባሁ። በመሆኑም ቀጣዮቹን ሁለት ዓመታት ከሱስ ለመላቀቅ በሚረዳ ተቋም ውስጥ ስረዳ እንዲሁም የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ሲደረግልኝ ቆየ፤ ከከብት ጥበቃ ሥራዬም ተሰናበትኩ።
መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በተሐድሶ ፕሮግራሙ ላይ ሳለሁ አንዲት የሴት ጓደኛዬ የተወሰኑ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን እንዳነብ ታመጣልኝ ነበር። ይሁን እንጂ እምብዛም ስላልተማርኩ የንባብ ችሎታዬ ጥሩ አልነበረም። ከዚያም በአንድ ወቅት፣ የ83 ዓመት አረጋዊ የሆኑ ሰው በአንድ ሞቃታማ ቀን ወደ እኔ መጡ። እኔም ቀዝቀዝ ያለ ውኃ ይጠጡ ዘንድ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዝኳቸው። እሳቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አንዳንድ ጽሑፎችን ሰጡኝና በሌላ ጊዜ ተመልሰው በመምጣት የጽሑፎቹን ይዘት እንደሚያብራሩልኝ ገለጹልኝ። ውሎ አድሮም መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመርን። እኔም አምላክን ለማስደሰት ከፈለግሁ በባሕርዬና በአኗኗሬ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንዳለብኝ መገንዘብ ጀመርኩ።
አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች ማድረግ ለእኔ ቀላል አልነበረም። ይሁንና እናቴ ባስተማረችኝ ነገሮች የተነሳ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያስጠኑኝ አረጋዊም ሆነ ላካፈሉኝ መንፈሳዊ ማስተዋል ጥልቅ አክብሮት ነበረኝ። ያም ሆኖ ሕይወቴን ለአምላክ ለመወሰን ፈራ ተባ እል ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ማወቅ እንዳለብኝ ሆኖ ይሰማኝ ነበር።
ሆኖም አንድ የሥራ ባልደረባዬ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን አስተሳሰብ እንዳስተካክል ረዳኝ። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክር ስለነበር በቆላስይስ 1:9, 10 ላይ የሚገኘውን የሚያበረታታ ሐሳብ ጠቀሰልኝ። ጥቅሱ ‘ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደግን መሄድ’ እንደሚገባን ይገልጻል። የሥራ ባልደረባዬ፣ ምንጊዜም አዳዲስ ነገሮችን እየተማርኩ እንደምሄድና እውቀቴ ውስን መሆኑ ወደኋላ እንድል ምክንያት እንደማይሆነኝ እንድገነዘብ ረዳኝ።
በተለይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ስጀምር በጣም ተገረምኩ። የተለያየ የኑሮ ደረጃና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች በአንድነት አምላክን ሲያመልኩ ተመለከትኩ። ይህ አንድነት እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ በደንብ አሳመነኝ፤ ስለዚህ በ1985 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ያገኘሁት ጥቅም፦ የንባብ ችሎታዬ ተሻሽሏል፤ እንዲሁም አሁን ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡና እንዲያጠኑ በመርዳት በየሳምንቱ ብዙ ሰዓት አሳልፋለሁ። በተጨማሪም መጀመሪያ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች እንዳነብ ታመጣልኝ የነበረችው የሴት ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ካጠናች በኋላ ተጠመቀች፤ አሁን የምወዳት ባለቤቴ ሆናለች። አንድ ላይ ሆነን በአቦርጂን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲማሩ በመርዳት እውነተኛ ደስታ እያጣጣምን ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ባለቤቴና እኔ በአቦርጂን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ስለ አምላክ እንዲማሩ በመርዳት እውነተኛ ደስታ እያጣጣምን ነው