አፖሎጂስቶች—የክርስትና ጠበቆች ወይስ ፈላስፎች?
አፖሎጂስቶች—የክርስትና ጠበቆች ወይስ ፈላስፎች?
በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ ክርስቲያኖች የቅርብ ዘመዶቻቸውን ያገባሉ፣ ሕፃናትን ይገድላሉ፣ ሰው ይበላሉ የሚሉና ሌሎች በርካታ የሐሰት ውንጀላዎች ይሰነዘሩባቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ኃይለኛ የሆነ የስደት ማዕበል በመነሳቱ ክርስቲያን ነን የሚሉ ፀሐፊዎች ለእምነታቸው ጥብቅና የመቆም ግዴታ እንዳለባቸው ሆኖ ተሰማቸው። ከጊዜ በኋላ አፖሎጂስቶች ወይም የእምነታቸው ጠበቆች ተብለው የተጠሩት እነዚህ ፀሐፊዎች የሮማውያን ባለሥልጣናትንና የሕዝቡን ልብ ለመማረክ ሲሉ ሃይማኖታቸው በማንም ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑን ለማሳመን ቆርጠው ተነሱ።
ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን በጣም አደገኛ ነበር፤ ምክንያቱም አፄያዊው መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ሊለዝብ የሚችለው ክርስቲያኖች አቋማቸውን ካላሉ ብቻ ነበር። ከዚህም በላይ ሳያስፈልግ አቋምን ማላላት የበለጠ ስደት ሊያስነሳ ወይም የክርስትናን እምነት ሊበርዝ ይችላል። ይሁንና አፖሎጂስቶች ለእምነታቸው ይሟገቱ የነበረው እንዴት ነው? በየትኞቹ የመከራከሪያ ነጥቦች ይጠቀሙ ነበር? ጥረታቸውስ ምን ውጤት አስገኘ?
አፖሎጂስቶችና የሮም አፄያዊ መንግሥት
አፖሎጂስቶች በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የኖሩ የተማሩ ሰዎች ነበሩ። ከእነዚህ መካከል እጅግ ታዋቂ የሆኑት ጀስቲን ማርተር፣ የእስክንድሪያው ክሌመንትና ተርቱሊያን ይገኙበታል። * ጽሑፎቻቸው በዋነኝነት የሚያነጣጥሩት በአረማውያንና በሮም ባለሥልጣናት ላይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን በብዛት እየጠቀሱ የክርስትናን እምነት የማብራራት ዓላማ ነበራቸው። ከዚህም በላይ አፖሎጂስቶች አሳዳጆቻቸው የሚያቀርቡትን ውንጀላ በማስተባበልና ስለ ክርስቲያኖች በጎ ነገሮችን በመጻፍ ይደርስባቸው የነበረውን ተቃውሞ ተቋቁመዋል።
አፖሎጂስቶችን በዋነኝነት ያሳስቧቸው ከነበሩት ነገሮች አንዱ ክርስቲያኖች የንጉሠ ነገሥቱም ሆነ የአፄያዊ መንግሥት ጠላቶች አለመሆናቸውን ለፖለቲካ ባለሥልጣናት ማሳመን ነበር። ተርቱሊያን ንጉሠ ነገሥቱን በሚመለከት “አምላካችን ሾሞታል” ብሎ ተናግሯል፤ አቴናጎረስ ደግሞ ዙፋን በዘር ሐረግ መተላለፉ ተገቢ ነው ብሎ ተከራክሯል። በዚህ መንገድ ሁለቱም በዘመኑ በነበረው ፖለቲካ ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል። እንዲህ ያለ አቋም በመውሰድ ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ችላ ብለዋል።—ዮሐንስ 18:36
በተጨማሪም አፖሎጂስቶች በሮምና በክርስትና እምነት መካከል የጠበቀ ትስስር እንዲኖር ሐሳብ አቅርበዋል። ሜለቶ እነዚህ ሁለቱ ወገኖች መቀናጀታቸው ለአፄያዊው መንግሥት ደኅንነት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግሯል። ዚ ኢፕስል ቱ ዲዮግነትስ የተባለውን መጽሐፍ የጻፈው ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ክርስቲያኖችን ‘ዓለምን አስተሳስሮ የያዘ’ ነፍስ ብሏቸዋል። ተርቱሊያን ክርስቲያኖች ለአፄያዊው መንግሥት ብልጽግና እንዲሁም የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ቶሎ እንዳይመጣ እንደሚጸልዩ ጽፏል። ይህም የአምላክ መንግሥት መምጣት ያን ያህል አስፈላጊ ነገር እንዳልሆነ እንዲታይ አድርጓል።—“ክርስትና” ፍልስፍና ሆነ
ሴልሰስ የተባለው ፈላስፋ ክርስቲያኖች “የጉልበት ሠራተኞች፣ ጫማ ሠሪዎች፣ ገበሬዎች፣ ያልተማሩና ጅላጅሎች ናቸው” በማለት በፌዝ ተናግሯል። አፖሎጂስቶች እንዲህ ያለውን ፌዝ ችሎ ማለፍ አልሆነላቸውም። አዲስ ስልት በመፍጠር የሕዝቡን አመለካከት ለመለወጥ ቆርጠው ተነሱ። በአንድ ወቅት ተቀባይነት ያልነበረው ዓለማዊ ጥበብ “የክርስትናን” ዓላማ የሚያራምድ መሣሪያ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ለምሳሌ የእስክንድሪያው ክሌመንት፣ ፍልስፍና “እውነተኛ የሥነ መለኮት ትምህርት” ነው የሚል አመለካከት ነበረው። ጀስቲን ደግሞ አረማዊ ፍልስፍናን እንደማይቀበል ቢናገርም እንዲህ ያለው ፍልስፍና “ጉዳት እንደሌለውና ጠቃሚ እንደሆነ” ያምን ነበር፤ በመሆኑም “ክርስቲያናዊ” አመለካከቶችንና ጽንሰ ሐሳቦችን ለማብራራት ፍልስፍና የሚንጸባረቅበት የአነጋገር ዘይቤ ለመጠቀም የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የተጠቀሙበት ስልት ፍልስፍናን መቃወም ሳይሆን ክርስቲያናዊ አስተሳሰቦች እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሐሳቦች ከአረማውያን የበለጡ ፍልስፍናዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነበር። ጀስቲን እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “በአንዳንድ ነጥቦች ረገድ የምናስተምራቸው ነገሮች ከፍተኛ ከበሬታ የምትሰጧቸው ባለቅኔዎችና ፈላስፎች ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር ይመሳሰላሉ፤ በሌላ በኩል ግን እኛ የምናስተምረው ትምህርት ይበልጥ የተሟላና መለኮታዊ ይዘት ያለው ነው።” “የክርስትና” አስተሳሰብ አዲሱን የፍልስፍና ጌጥ ተላብሶ ራሱን ጥንታዊ ክብር ያለው አስተሳሰብ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ጀመረ። አፖሎጂስቶች የክርስትና መጻሕፍት ከግሪካውያን መጻሕፍት የበለጠ ዕድሜ እንዳላቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት የግሪክ ፈላስፎች ከኖሩበት ከብዙ ዘመን በፊት እንደነበሩ አመልክተዋል። አንዳንድ አፖሎጂስቶች፣ ፈላስፎች አንዳንድ ነገሮችን ከነቢያት ቀድተዋል የሚል አመለካከት ነበራቸው። እንዲያውም ፕላቶ የሙሴ ደቀ መዝሙር እንደነበረ እስከ መናገር ደርሰዋል!
የክርስትና ትምህርት ተበረዘ
ይህ አዲስ ስልት ክርስትና እና አረማዊ ፍልስፍና እንዲቀላቀል አደረገ። የግሪካውያንን አማልክት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር ማመሳሰል ተጀመረ። ኢየሱስ
ከፐርሲየስ ጋር እንደሚመሳሰል እንዲሁም የማርያም መፀነስ ድንግል እንደነበረች ከሚነገርላት ከፐርሲየስ እናት ከዳኒ መፀነስ ጋር እንደሚመሳሰል ይነገር ጀመር።አንዳንዶቹ ትምህርቶች በጣም ተበርዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ “ሎጎስ” ተብሎ ተጠርቷል፤ ሎጎስ የአምላክ “ቃል” ወይም ቃል አቀባይ የሚል ትርጉም አለው። (ዮሐንስ 1:1-3, 14-18፤ ራእይ 19:11-13) በዚያን ዘመን እንኳ፣ እንደ ፈላስፋ የሚያደርገው ጀስቲን ሎጎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል በሁለት መንገዶች ይኸውም “ቃል” እና “ምክንያት” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል በመግለጽ እውነተኛውን ትምህርት አጣሟል። እሱ እንደሚናገረው ከሆነ ክርስቲያኖች ክርስቶስን በመቀበል ቃልን ተቀብለዋል። ይሁን እንጂ ሎጎስ፣ ምክንያት በሚለው ትርጉሙ ሲታይ በሁሉም ሰው ሌላው ቀርቶ በአረማውያን ውስጥ እንኳ ይገኛል። ከዚህ በመነሳት አምላክ የለሾች እንደሆኑ የሚናገሩ ወይም እንደ አምላክ የለሽ ይታዩ የነበሩ እንደ ሶቅራጥስ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ክርስቲያኖች ናቸው በማለት ደምድሟል።
ከዚህም በላይ ተርቱሊያንን ጨምሮ አፖሎጂስቶች በኢየሱስና የግሪክ ፍልስፍና በወለደው በሎጎስ (ከአምላክ ጋር የቅርብ ትስስር እንዳለው ይታመናል) መካከል ያለውን ዝምድና መሠረት በማድረግ የኋላ ኋላ በክርስትና እምነት ውስጥ የሥላሴ ትምህርት እንዲፈጠር ያደረገውን አካሄድ መከተል ጀመሩ። *
“ነፍስ” የሚለው ቃል በግሪክኛ ከ100 ጊዜ በላይ የተጠቀሰውን ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ850 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። መሠረታዊ ትርጉሙ ሰዎችንና እንስሳትን ጨምሮ ሟች የሆኑ ሕያዋን ፍጥረታትን ያመለክታል። (1 ቆሮንቶስ 15:45፤ ያዕቆብ 5:20፤ ራእይ 16:3) ይሁን እንጂ አፖሎጂስቶች ይህን ሐሳብ ነፍስ ከሥጋ የተለየች፣ የማትታይና የማትሞት ነገር ነች ከሚለው የፕላቶ ፍልስፍና ጋር በማዛመድ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት አጣመዋል። እንዲያውም ሚኑኪየስ ፌሊክስ፣ የትንሣኤ ትምህርት መነሻው ፓይታጎረስ ነፍስ ከሞተው አካል ወጥታ ወደ ሌላ እንደምትሸጋገር ያስተማረው ትምህርት ነው እስከ ማለት ደርሷል። በእርግጥም የግሪካውያን ፍልስፍና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በእጅጉ እንዲርቁ አድርጓቸዋል።
የተሳሳተ ምርጫ
አንዳንድ አፖሎጂስቶች ፍልስፍና በክርስትና እምነት ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ ፈላስፋዎቹን ቢተቹም ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን ማድነቃቸው አልቀረም። ለምሳሌ፣ ቴሸን ፈላስፎችን ምንም ፋይዳ እንደሌላቸው በመግለጽ ቢያወግዛቸውም የክርስትናን ሃይማኖት “ፍልስፍናችን” ብሎ ከመጥራት አልፎ በፍልስፍና መላምቶች ውስጥ ተዘፍቋል። ተርቱሊያን በአንድ በኩል የአረማውያን ፍልስፍና በክርስትና አስተሳሰብ ላይ እያስከተለ የነበረውን ተጽዕኖ ነቅፏል። በሌላ በኩል ግን “ፈላስፋና ሰማዕት የነበረውን የጀስቲንና የአብያተ ክርስቲያናት ሊቅ የነበረውን የሚልታየዲዝን” አርዓያ መከተል እንደሚፈልግ ተናግሯል። አቴናጎረስ ራሱን “የአቴና የክርስትና ፈላስፋ” ብሎ ጠርቷል። ክሌመንት ደግሞ “ክርስቲያኖች ፍልስፍናን ጥበብ ለማግኘትና ለእምነታቸው ለመሟገት በማስተዋል ሊጠቀሙበት ይችላሉ” የሚል ስሜት እንዳለው ተናግሯል።
እነዚህ አፖሎጂስቶች ለእምነታቸው በመሟገት ረገድ ምንም ያህል የተሳካ ውጤት ቢያገኙም እምነታቸውን ለመከላከል ሲሉ በወሰዱት እርምጃ ከባድ ስህተት ፈጽመዋል። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊጠቀሙባቸው ከሚችሉት መንፈሳዊ መሣሪያዎች መካከል “ሕያውና ኃይለኛ” ዕብራውያን 4:12፤ 2 ቆሮንቶስ 10:4, 5፤ ኤፌሶን 6:17
ከሆነው ‘ከአምላክ ቃል’ የተሻለ መሣሪያ እንደማይኖር አሳስቧል። ጳውሎስ አክሎ ሲናገር በአምላክ ቃል አማካኝነት “የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ይህን እውቀት ለማገድ የሚገነባውን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን” ብሏል።—ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለደቀ መዛሙርቱ “አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 16:33) ከዓለም ደርሶበት የነበረው ፈተናና መከራ በአባቱ ላይ የነበረውን እምነት እንዲያጣም ሆነ ታማኝነቱን እንዲያጎድፍ አላደረገውም። ከሐዋርያት መካከል በመጨረሻ የሞተው ዮሐንስም “በዚህ ድል ይኸውም በእምነታችን ዓለምን አሸንፈናል” ብሏል። (1 ዮሐንስ 5:4) አፖሎጂስቶች ለክርስትና እምነት ጠበቃ መሆን ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም የዓለምን የፍልስፍና አመለካከት እንዲሁም አስተሳሰብ መቀበላቸው ስህተት ነበር። ይህን በማድረጋቸው እንዲህ ባሉ ፍልስፍናዎች የተታለሉ ከመሆኑም በላይ እነሱም ሆኑ የእነሱ ክርስትና በዓለም ድል እንዲነሳ ፈቅደዋል። ስለዚህ የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን አፖሎጂስቶች፣ የእውነተኛው ክርስትና እምነት ጠበቆች ከመሆን ይልቅ ሳይታወቃቸው “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን” የሚለውጠው ሰይጣን ባዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ ገብተዋል።—2 ቆሮንቶስ 11:14
የዘመናችን የሥነ መለኮት አስተማሪዎችና ቀሳውስትም በአብዛኛው ይህንኑ አካሄድ ተከትለዋል። የአምላክን ቃል ተጠቅመው ለእውነተኛው ክርስትና ከመሟገት ይልቅ የሕዝቡንና የባለሥልጣናቱን ቀልብ ለመማረክ ሲሉ መጽሐፍ ቅዱስን አቃልለው በትምህርቶቻቸው ውስጥ ዓለማዊ ፍልስፍናዎችን መጠቀም መርጠዋል። እነዚህ ሰዎች በዓለም ላይ የሚታየው ከቅዱሳን መጻሕፍት ተቃራኒ የሆነ ነገር የማድረግ ዝንባሌ አደገኛ መሆኑን ከማስጠንቀቅ ይልቅ ተከታዮችን ለማፍራት ሲሉ የአድማጮቻቸውን ‘ጆሮ የሚኮረኩሩ’ መምህራን ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) የሚያሳዝነው ግን እነዚህ መምህራን እንደ ጥንቶቹ አፖሎጂስቶች “በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም አጥምዶ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚለውን ሐዋርያት የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለዋል። ለእኛም ቢሆን “ፍጻሜያቸው እንደ ሥራቸው ይሆናል” የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል።—ቆላስይስ 2:8፤ 2 ቆሮንቶስ 11:15
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 በተጨማሪም ኳድራተስ፣ አሪስታይዲዝ፣ ቴሸን፣ አፖሊናሪስ፣ አቴናጎረስ፣ ቴኦፍሎስ፣ ሜለቶ፣ ሚኑኪየስ ፌሊክስ እና ሌሎች ብዙ እውቅና ያላገኙ ፀሐፊዎች ነበሩ። የግንቦት 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 27-29 እንዲሁም የመጋቢት 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 28-30 ተመልከት።
^ አን.14 ተርቱሊያን ስለሚያምንባቸው ትምህርቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 15, 2002ን መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 29-31 ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ይህን እውቀት ለማገድ የሚገነባውን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን።”—2 ቆሮንቶስ 10:5
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጀስቲን፣ ፍልስፍና መከተልን ‘ምንም ጉዳት እንደሌለው’ እንዲያውም ‘ጠቃሚ’ እንደሆነ አድርጎ ይመለከት ነበር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክሌመንት ፍልስፍናን “እውነተኛ የሥነ መለኮት ትምህርት” እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተርቱሊያን ፍልስፍና ለሥላሴ ትምህርት ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቴሸን የክርስትናን ሃይማኖት “ፍልስፍናችን” ብሎ ጠርቶታል
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዘመናችን ቀሳውስትና የሥነ መለኮት አስተማሪዎች የአፖሎጂስቶችን አካሄድ ተከትለዋል
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ ከፍልስፍና እንዲሁም ከሰዎች የማታለያ ሐሳብ እንድንጠበቅ አስጠንቅቋል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Clement: Historical Pictures Service; Tertullian: © Bibliothèque nationale de France