ይሖዋ ትሑታንን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
ወደ አምላክ ቅረብ
ይሖዋ ትሑታንን ከፍ አድርጎ ይመለከታል
በዚህ ዓለም ልቀው ለመታየት በሚሯሯጡ ሰዎች ላይ ጎልተው ከሚታዩት ባሕርያት መካከል ኩራት፣ ቅናትና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት ይገኙበታል። ይሁንና እነዚህ ባሕርያት ወደ ይሖዋ አምላክ እንድንቀርብ የሚያደርጉ ናቸው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እሱን የሚያመልኩ ሰዎች ትሑታን እንዲሆኑ ይፈልጋል። የዚህን እውነተኝነት በዘኍልቍ ምዕራፍ 12 ላይ ከሚገኘው ዘገባ ላይ በግልጽ መመልከት ይቻላል። ታሪኩ የተፈጸመው እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ በሲና ምድረ በዳ እያሉ ነበር።
ማርያምና አሮን በታናሽ ወንድማቸው በሙሴ “ላይ ተናገሩ።” (ቁጥር 1 የ1954 ትርጉም) ማርያምና አሮን ሙሴን በቀጥታ ከማናገር ይልቅ በእስራኤላውያን ሰፈር እየዞሩ ስለ እሱ ማውራት ሳይጀምሩ አልቀሩም። ማርያም መጀመሪያ ላይ መጠቀሷ የችግሩ ቆስቋሽ እሷ እንደሆነች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። እንዲያጉረመርሙ ያደረጋቸው የመጀመሪያው ምክንያት ሙሴ ኢትዮጵያዊት ሴት ማግባቱ ነበር። ማርያም፣ የእስራኤል ብሔር ከእሷ ይልቅ እስራኤላዊ ላልሆነች ለሌላ ሴት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ በማሰብ ቅናት አድሮባት ይሆን?
ማርያምና አሮን እንዲያጉረመርሙ ያደረጓቸው ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ። እንዲህ ብለው ነበር፦ “ለመሆኑ እግዚአብሔር የተናገረው በሙሴ አማካይነት ብቻ ነውን? በእኛስ አልተናገረም?” (ቁጥር 2) በዋነኝነት እንዲያጉረመርሙ ያነሳሳቸው ሥልጣንና እውቅና የማግኘት ምኞት ይሆን?
ከዘገባው መመልከት እንደምንችለው ሙሴ እህቱና ወንድሙ ለሰነዘሩት ትችት ምንም ምላሽ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ያደረሱበትን በደል በትዕግሥት ለማለፍ የመረጠ ይመስላል። ሙሴ እንዲህ ማድረጉ መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበር” በማለት ስለ እሱ የሰጠው መግለጫ ትክክል መሆኑን ያሳያል። * (ቁጥር 3) ሙሴ ይሖዋ በእሱ እየተጠቀመ ያለው ለምን እንደሆነ ማብራራት አላስፈለገውም ነበር። ይሖዋ ራሱ ሁኔታውን የተከታተለ ሲሆን የቆመውም ከሙሴ ጎን ነበር።
ይሖዋ ትችቱን በራሱ ላይ እንደተሰነዘረ አድርጎ ተመልክቶታል። ደግሞም ሙሴን የሾመው ይሖዋ ራሱ ነው። አምላክ አጉረምራሚዎቹን በገሠጻቸው ጊዜ “እኔ ከእርሱ ጋር የምነጋገረው ፊት ለፊት ነው” በማለት ከሙሴ ጋር ያለውን ልዩ ዝምድና አስታውሷቸው ነበር። ከዚያም ይሖዋ ማርያምንና አሮንን “ታዲያ እናንተ . . . ሙሴን ትቃወሙ ዘንድ ለምን አልፈራችሁም?” አላቸው። (ቁጥር 8) በሙሴ ላይ መናገራቸው በአምላክ ላይ እንደተናገሩ ያህል ያስጠይቃቸው ነበር። እንዲህ ያለውን ንቀት ማሳየታቸው የይሖዋ ቁጣ በላያቸው ላይ እንዲነድ አድርጓል።
የችግሩ ቆስቋሽ እንደሆነች የምትታሰበው ማርያም በለምጽ ተመታች። ወዲያውኑም አሮን፣ ሙሴ እንዲማልድላት ለመነው። የማርያም መዳን የተመካው በአንድ ወቅት አጉረምርመውበት የነበረው ሙሴ በሚያቀርበው ምልጃ ላይ መሆኑ አያስገርምም! ሙሴ ትሑት በመሆኑ አሮን የጠየቀውን አደረገ። ሙሴ በዚህ ዘገባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ለማርያም ለመማለድ ወደ ይሖዋ በጸለየበት ጊዜ ነበር። ማርያም ከለምጿ የተፈወሰች ቢሆንም ለሰባት ቀን ተገልላ መቆየቷ ያስከተለባትን የኃፍረት ስሜት መቋቋም አስፈልጓት ነበር።
ይህ ዘገባ፣ ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውንም ሆነ የሚጠላቸውን ባሕርያት በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤ እንድናገኝ ይረዳናል። ወደ አምላክ ለመቅረብ ከፈለግን የኩራት፣ የቅናትና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት በውስጣችን ካለ እንዲህ ያለውን ባሕርይ ከሥሩ ነቅለን ለመጣል ጥረት ማድረግ አለብን። ይሖዋ የሚወደው ትሑት ሰዎችን ነው። ይሖዋ በሰጠው ተስፋ መሠረት ትሑታን ወይም ‘ገሮች ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።’—መዝሙር 37:11፤ ያዕቆብ 4:6
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 ትሕትና አንድ ሰው ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ሲፈጸምበት የበቀል ስሜት ሳያድርበት ታግሦ በጽናት እንዲያልፍ የሚያስችለው ጠንካራ ባሕርይ ነው።