በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይመራሉ?

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይመራሉ?

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይመራሉ?

“የራሴ እምነት አለኝ፤ ልለውጠው ደግሞ አልፈልግም። ለነገሩ ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ስለሚመሩ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ብትሆን ለውጥ አያመጣም።”

ሰዎች እንዲህ ብለው ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ብዙ ሰዎች፣ ሁሉም ሃይማኖቶች አምላክን ለማወቅና የሕይወትን ዓላማ ለመረዳት እንደሚያስችሉ ይሰማቸዋል። በተመሳሳይም ‘ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩም መጥፎም ጎን አላቸው’ የሚል በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አመለካከት አለ፤ በመሆኑም ‘ማንኛውም ሰው አምላክን ለማወቅ የሚያስችለውና እውነተኛ የሆነው የራሱ ሃይማኖት ብቻ እንደሆነ ሊሰማው አይገባም’ የሚል አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ ሲንጸባረቅ ይታያል።

የተለያዩ እምነቶች ቢኖሩም ሁሉም ትክክል እንደሆኑ የሚሰማቸውና ተቻችሎ በመኖር እንደሚያምኑ የሚናገሩ ሰዎች ባሉበት በዚህ ዘመን ከላይ የተገለጸው ዓይነት አመለካከት ሰፊ ተቀባይነት አለው። እንዲያውም ከዚህ የተለየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ጠባብ አስተሳሰብ እንዳላቸውና ምክንያታዊ እንዳልሆኑ ተደርገው ይታያሉ። አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን አመለካከት አለህ? ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ እንደሚመሩ ይሰማሃል? አንድ ሰው የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን ለውጥ አያመጣም?

በእርግጥ ልዩነት አላቸው?

አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ 9,900 የሚያህሉ ሃይማኖቶች አሉ፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ በበርካታ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሏቸው። ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶ የሚያክለው የአምስቱ ዋና ዋና ሃይማኖቶች ይኸውም የሂንዱይዝም፣ የቡድሂዝም፣ የአይሁድ እምነት፣ የእስልምና እንዲሁም የክርስትና እምነት ተከታይ እንደሆነ ይገመታል። ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ የሚመሩ ከሆነ እነዚህ አምስት እምነቶች በትምህርቶቻቸው፣ አምላክን በሚገልጹበት መንገድ እንዲሁም ስለ አምላክ ዓላማ በሚሰጡት ማብራሪያ ረገድ በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል ማለት ነው። ታዲያ ሐቁ ምን ያሳያል?

የሮም ካቶሊክ የሃይማኖት ምሑር የሆኑት ሃንስ ኩንግ በዓለም ላይ ያሉት ዋና ዋና ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ከሌሎች ጋር ሊኖራቸው በሚገባው ግንኙነት ረገድ የሚጋሯቸው አንዳንድ መሠረታዊ እምነቶች እንዳሉ ተናግረዋል። ለአብነት ያህል፣ አብዛኞቹ መግደልን፣ መዋሸትን፣ መስረቅን፣ ከቅርብ ዘመድ ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸምን የሚያወግዙ ሲሆን ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩና ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲወዱ ያዝዛሉ። ይሁንና እነዚህ ዋና ዋና ሃይማኖቶች በሌሎች ጉዳዮች ረገድ በተለይ ደግሞ አምላክን በሚገልጹበት መንገድ በጣም ሰፊ ልዩነት አላቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ ሂንዱዎች በጣም ብዙ አማልክት የሚያመልኩ ሲሆን ቡድሂስቶች ደግሞ ‘የራሱ ሕልውና ያለው አምላክ አለ’ በሚለው ሐሳብ አይስማሙም። የእስልምና ሃይማኖት አንድ አምላክ እንዳለ ያስተምራል። ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚናገሩ ሃይማኖቶች ከዚህ ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ቢሆንም አብዛኞቹ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ያስተምራሉ። የክርስትና ሃይማኖቶች በሚያስተምሯቸው መሠረተ ትምህርቶች ይለያያሉ። ካቶሊኮች ለኢየሱስ እናት ለማርያም ትልቅ ቦታ የሚሰጧት ሲሆን ፕሮቴስታንቶች ግን እንዲህ አያደርጉም። በጥቅሉ ሲታይ ካቶሊኮች የወሊድ መከላከያ መጠቀምን የሚከለክሉ ሲሆን በአብዛኞቹ ፕሮቴስታንቶች ዘንድ ግን የወሊድ መከላከያ መጠቀም ይፈቀዳል። በተጨማሪም ፕሮቴስታንቶች ግብረ ሰዶምን በተመለከተ የተለያየ አቋም አላቸው።

ታዲያ እንዲህ ያሉ የተለያዩ ትምህርቶች ያሏቸው ሃይማኖቶች በሙሉ የሚያመልኩት አንድ አምላክ ነው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይሆናል? በፍጹም። ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ስለ አምላክ ማንነት እንዲሁም ከአምላኪዎቹ ስለሚጠብቃቸው ነገሮች ግራ እንዲጋቡ ከማድረግ ያለፈ የሚፈይዱት ነገር የለም።

ሃይማኖቶች አንድነት ይፈጥራሉ? ወይስ ይከፋፍላሉ?

ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ የሚመሩ ከሆነ እያንዳንዱ ሃይማኖት የሰው ዘር ሰላምና አንድነት እንዲኖረው ለማድረግ ሲጥር መታየት ይኖርበታል። ታዲያ ሐቁ ይህን እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ነው? ታሪክ እንደሚያሳየው ሃይማኖት የሰው ልጆች አንድነት እንዲኖራቸው ከማድረግ ይልቅ እየከፋፈላቸውና እርስ በርስ እንዲጋጩ እያደረገ ነው። እስቲ የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ከ11ኛው እስከ ከ13ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱት የመስቀል ጦርነቶች፣ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብሔራት የእስልምና ተከታይ ከሆኑ ብሔራት ጋር ተዋግተዋል። በ17ኛው መቶ ዘመን ደግሞ በአውሮፓ ውስጥ በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል ለሠላሳ ዓመታት የዘለቀ ውጊያ ተካሂዷል። በ1947 የሕንድ ክፍለ አህጉር ከታላቋ ብሪታንያ ነፃ ከወጣ ብዙም ሳይቆይ በሂንዱ እምነት ተከታዮችና በሙስሊሞች መካከል ጦርነት ተነስቶ ነበር። በቅርብ ጊዜ ደግሞ በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ለዓመታት ተዋግተዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት አይሁዶችና ሙስሊሞችም እስካሁን ድረስ እየተዋጉ ነው። ከእነዚህ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው ምሳሌ ደግሞ የአምስቱም ዋና ዋና ሃይማኖቶች አባላት የተካፈሉበት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ነው፤ በዚህ ጦርነት ላይ የአንድ ሃይማኖት አባላት እንኳ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው እርስ በርስ ተዋግተዋል።

ከእነዚህ ምሳሌዎች በግልጽ መመልከት እንደምንችለው በዓለም ላይ ያሉት ሃይማኖቶች ሰላምና አንድነት ማምጣትም ሆነ የሰው ልጆችን ወደ አንድ አምላክ መምራት አልቻሉም። በተቃራኒው የሰው ልጆችን ከፋፍለዋል፤ እንዲሁም አምላክ ማን እንደሆነ ብሎም እንዴት ሊመለክ እንደሚገባ ሰዎች ግራ እንዲጋቡ አድርገዋል። በመሆኑም እውነተኛውን አምላክ ማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚከተለውን ጎዳና በጥንቃቄ መምረጥ አለበት። ይህም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የሃይማኖት መጻሕፍት አንዱ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር ይስማማል።

የምታመልኩትን ምረጡ

ወደ እውነተኛው አምላክ የሚመራንን መንገድ ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ነገሮችን በጥንቃቄ አመዛዝነን መምረጥ እንደሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። የይሖዋ አምላክ አገልጋይ የሆነው ኢያሱ በጥንት ዘመን ለነበረው የእስራኤል ብሔር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የቀድሞ አባቶቻችሁ ከወንዙ ማዶ ካመለኳቸው አማልክት ወይም በምድራቸው የምትኖሩባቸው አሞራውያን ከሚያመልኳቸው አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ የምታመልኩትን ዛሬውኑ ምረጡ፤ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ከብዙ ዓመታት በኋላም ነቢዩ ኤልያስ ለእስራኤል ሕዝብ ተመሳሳይ ምርጫ አቅርቦላቸዋል፦ “በሁለት ሐሳብ የምትዋልሉት እስከ መቼ ድረስ ነው? አምላክ እግዚአብሔር ከሆነ እግዚአብሔርን ተከተሉ፤ በኣል [የከነዓናውያን ጣዖት] አምላክ ከሆነም በኣልን ተከተሉ።”—ኢያሱ 24:15, 16፤ 1 ነገሥት 18:21

እነዚህም ሆኑ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጎላ አድርገው እንደሚገልጹት እውነተኛውን አምላክ ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ጥንቃቄ የተሞላበት ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እኛም እውነተኛውን አምላክ ማምለክና ማገልገል ከፈለግን ትክክለኛውን ምርጫ ማድረግ ይኖርብናል። ይሁንና በአምልኮ ረገድ ትክክለኛ የሆነውን ምርጫ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን እንዴት መለየት እንችላለን?

እውነተኛ አምላኪዎች በፍሬያቸው ተለይተው ይታወቃሉ

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እውነተኛ ስለሆኑና ስላልሆኑ የአምላክ አገልጋዮች ለተከታዮቹ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ? በተመሳሳይም ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን የማይጠቅም ፍሬ ያፈራል፤ ጥሩ ዛፍ የማይጠቅም ፍሬ ሊያፈራ፣ የበሰበሰ ዛፍ ደግሞ መልካም ፍሬ ሊያፈራ አይችልም። . . . ስለዚህ እነዚህን ሰዎች በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” ከዚህ ለመመልከት እንደሚቻለው እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በፍሬያቸው ማለትም በሥራቸው ተለይተው ይታወቃሉ። እነዚህ ሰዎች የሚያፈሩት ፍሬ ምንድን ነው?—ማቴዎስ 7:16-20

በመጀመሪያ ደረጃ፣ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እርስ በርስ ያላቸው ፍቅር አንድነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እየሰጠኋችሁ ነው፤ ልክ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች እርስ በርስ መዋደድ አለባቸው፤ በመካከላቸው ያለው ይህ ፍቅር እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።—ዮሐንስ 13:34, 35

በዚህም ምክንያት እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት ወቅት እርስ በርስ መዋጋት ፈጽሞ የማያስቡት ነገር ነው። የሕዝበ ክርስትና አባላት እንዲህ ያለውን ብቃት ያሟላሉ? በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከዋና ዋና ሃይማኖቶች መካከል ጦርነቱን በምንም መንገድ ያልደገፉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስከትለው መዘዝ ሳይበግራቸው ምንጊዜም በአቋማቸው ጸንተዋል። በሃኖቨር፣ ጀርመን ያለው የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ የነበሩት ዶክተር ሃንስ ሊልዬ ስለ የይሖዋ ምሥክሮች ሲጽፉ ከዋና ዋናዎቹ ሃይማኖቶች መካከል “የሂትለርን ሦስተኛ ራይክ አገዛዝ እንደተቃወሙ በትክክል መናገር የሚችሉት እነሱ ብቻ ናቸው” ብለዋል። በዚያ ወቅት በብዙ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጦርነቱን ከመደገፍ ይልቅ ይህን ባለማድረጋቸው የሚደርስባቸውን ቅጣት ለመቀበል መርጠዋል።

እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የሚታወቁባቸው ሌሎች ፍሬዎችስ የትኞቹ ናቸው? ኢየሱስ፣ በተለምዶ አቡነ ዘበሰማያት ተብሎ በሚታወቀው ጸሎት መጀመሪያ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” ኢየሱስ ቅድሚያ የሰጠው ይሖዋ ለሚለው የአምላክ ስም መቀደስ ነው። እንዲሁም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ ፈቃድ በምድር እንዲፈጸም ያለውን ምኞት ገልጿል። የይሖዋን ስም በማሳወቅ እንዲሁም በምድር ላይ ሰላም ሊያሰፍን የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ በማወጅ ረገድ የታወቀው የትኛው ሃይማኖት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ከ470 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችን በማሠራጨት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በ236 አገሮችና ትንንሽ ግዛቶች ያውጃሉ።—ማቴዎስ 6:9, 10

ከዚህም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውዝግቦች ውስጥ ጣልቃ ከመግባት በመቆጠብ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል [አይደሉም]” ብሏል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው የሚቀበሉት ሲሆን በሚከተለው ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ያምናሉ፦ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመምከር ይጠቅማል፤ ይኸውም የአምላክ ሰው ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”—ዮሐንስ 17:14, 17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

እውነተኛው ሃይማኖት ከሌሎች የተለየ ነው

ከላይ የተመለከትናቸው ነጥቦች ይኸውም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር፣ የይሖዋን ስም ለመቀደስ መፈለግ፣ ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ፣ ከዓለም መለየት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርጎ መቀበል እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ተለይተው የሚታወቁባቸው ፍሬዎች ናቸው። ከዚህም ሌላ እነዚህ ፍሬዎች እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮችን ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለዩ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ስትወያይ የቆየች አንዲት ሴት እንዲህ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሳለች፦ “ብዙ ሃይማኖቶችን አውቃለሁ፤ ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው። ከሌሎች ሃይማኖቶች ፈጽሞ የምትለዩት እናንተ ብቻ ናችሁ።”

በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አንድ አምላክ ይመራሉ የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው። ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የተለዩ ናቸው፤ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ። የአምላክ ቃል ስለሆነው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመስበክና ትምህርቱን በመከተል ማንኛውም ቡድን ወይም ድርጅት ሊያደርግ ያልቻለውን ነገር ማከናወን ችለዋል፤ ይኸውም የተለያየ ዜግነት፣ ቋንቋ፣ ጎሳና ዘር ያላቸው ሰዎች ብቻውን እውነተኛ አምላክ በሆነው በይሖዋ አምልኮ አንድ እንዲሆኑ ማድረግ ችለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን አምላክ እንድታውቅ፣ ከአንተ ምን እንደሚፈልግ እንድትገነዘብ እንዲሁም አምላክን እሱ በሚቀበለው መንገድ ማምለክ የሚያስገኘውን ሰላምና የደኅንነት ስሜት እንድታገኝ ለመርዳት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። እንዲህ ያለ እውቀት ለማግኘት እቅድ ማውጣት ጠቃሚ አይመስልህም?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2004 አንድ የኦርቶዶክስ ቄስ በዩክሬን አዲስ የተመረቁ ሠራዊቶችን ሲባርክ

[የሥዕል ምንጭ]

GENIA SAVILOV/AFP/Getty Images

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችን ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ ያስተምራሉ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 12፦ የቡድሂዝም እምነት ተከታይ የሆነች ሴት፦ © Yan Liao/Alamy; የሂንዱ እምነት ቅዱስ ሰው፦ © imagebroker/Alamy; ገጽ 13፦ ቁራን የሚያነበው ሰው፦ Mohamed Amin/Camerapix; አይሁዳዊ፦ Todd Bolen/Bible Places.com